ጥያቄያችን ዴሞክራሲያዊት አገር ትኑረን ነው!!!

0
664

ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ የሕግ የበላይነት አለመኖር፣ የዘረኝነት ስሜት በሰፊው መንሰራፋት፣ የመንጋነት ባህርይ መብዛት መገለጫዎቹ ናቸው የሚሉት መላኩ አዳል፣ ለአገር ህልውና የሚበጀው የጎሳዎችን አደረጃጀት መለወጥ እንዲሁም የልኂቃንን ተሳትፎ ማዳበር ነው ይላሉ። በዋነኛነትም ዜጎች መብታቸውን ለማስጠበቅ ለዴሞክራሲያዊና ሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄዎች በአንድነት መነሳት ይጠበቅባቸዋል።

የለውጡ ዓላማ መዳረሻው የሕወሓትን የበላይነትን በኦነግ/ኦዴፓ የበላይነት መተካት፣ የጠገቡ ጅቦችን ባልጠገቡት መተካት፣ የሕግ የበላይነትንና ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ሳይሆን ግጭቶችን ማባባስ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ሳይሆን ተረኝነትን ማንገሥ፣ ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን ማጠናከር ሳይሆን የዘውግ ፖለቲካን ለብጥብጥ ማጎልበት መሆናቸውን እያየን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም አምባገነን መሆን ያለበት ለተረኝነቱ ነው እያሉን ነው። ነገር ግን ይህ የሚሆንበት መንገድ እንደሌለ የመረዳት አቅም እንደሌላቸው እያየን ነው። ማንን ነው የሚገዙት? የትናንትናዎቹ የመብት ተሟጋች ኦሮሞዎች፣ አሁን የምን ዴሞክራሲያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ነው? ብዙ ነንና የእኛ ተጠቃሚነት በተረጋገጠበት ሁኔታ እንግዛችሁ እያሉን ነው።

እየሆነ ያለው ዛሬም እንደ 1960ዎቹ የሚካሔድ በጉልበትና ባቋራጭ ሥልጣንን የመያዝ ፍላጎት አባዜ ነው። ከውስጥ መኢሶንን ተክቶ ኦነግ አለ፣ ከውጭ የኦነግ ጊዜያዊ ወዳጅ ሕወሓት ኢሕአፓን ወክሎ አለ። በመሀሉ ምስኪኑ ወጣትና ሌላውም ዜጋ እንደ ትናንቱ ዛሬም ለማይረባ ዓላማ ይሞታል። ኦሕዴድ/ኦነግ ሁላችንም እኩል የምንኖርባት ዴሞክራቲክ አገር ከመገንባት ይልቅ፣ የበላይነትን ወይም መገንጠልን የሚሰብክ ዘረኛ ቡድን ሆኗል።

ሕገ መንግሥቱ ብዙ ችግር ያለበትና መስተካከልም ያለበት ሆኖ እያለ የአይነካምና የሕወሓት ሐሳብ ደጋፊ ሆኖ ተገኝቷልም። መታወቅና መሆን ያለበት፣ ኢትዮጵያ ሁሉን አቃፊ እንድትሆን መሥራት እንጂ፣ ኦሮሞ ብቻ ተጠቃሚ እንዲሆን መሥራትና ኦሮሞ አቃፊ ነው መፈክር አይደለም። ለዚህ ሁሉ ዋናው ችግር የሀሰት ትርክት ነው። የሚያሳዝነው፣ በመላ ታሪካችን በየተራ ሲወር/ሲወረር፣ ሲያሸንፍ/ሲሸነፍ፣ ሲጨፈጭፍ/ሲጨፈጨፍ፣ ሲጋባ/ሲፋታ፣ ሲጣላ/ሲታረቅ፣ የኖረው የተረሳ ይመስል አንዱ ጎጂ፣ ሌላው ተጠቂ ትርክት መስማት ነው። አማራ፣ ኦሮሞና ትግሬ በዚች ምድር ሲጠዛጠዝ የኖረ ነው። በየተራ ጎድቷል፣ ተጎድቷል።

ለተረኝነቱ ያግዝ ዘንድ፣ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሌለን፣ ነገር ግን የዓለም አብዛኛው አገር የሚተዳደርበትን አህዳዊነት (centralized government) እንደ አንድ አስፈሪ ግኡዝ ነገር በመቁጠር የ‹‹መጣብህ!›› ማስፈራሪያ አድርገውታል። ብዝኀነትን በአንድነት ውሰጥ (diversity within unity) መፈለግና ማግኘት ሲገባ፣ ብዝኀነት ውስጥ አንድነትን (unity within diversity) እንፈልገው እያሉ የማይሆነውንና ተሞክሮ የከሰረውን መንገድ እንዲደገም እያደረጉም ነው።
እንዲያውም በባሌ ወጥተው በቦሌ የተመለሱና አንድም የማሸነፍ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች ኮንፌዴሬሽን ሁኑ እያሉም ነው። ለዚህ ሁሉ የዳረጋቸው ደግሞ የዝቅተኝነት ሥነ ልቦናና እሱን ተከትለው የመጡት ተረኝነት፣ ኋላ ቀርነት፣ አክራሪነትና ጎሰኝነት ናቸው። እነዚህ ቡድኖች በዚህ የዝቅተኝነት ሥነ ልቦና ምክንያት አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ገብተውና የጠቅላይና የመከላከያ ሚኒስቴርነትን ቦታ ይዘው ምሩን ይኸው ተብለውም እውነትነቱን አያምኑም። ይህም የመምራት አቅማቸውን ዝቅተኛ፣ የሕዝብን ሰላምንና ኑሮ ችግር ላይ፣ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል።

የለውጡ የፊት መሪዎች ከነበሩት አንዱ ከኦነግ ጋር በማበር የራሳቸውን አንጃ ፈጥረዋል እየተባለ ይወራል። አንጃው ሕገ መንግሥቱን በመጣስ፣ የፌዴራል ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን እንዳይተገበሩ በመከልከል፣ አዲስ አበባ የኛ ናት በማለት፣ ኦሮምኛ አሁኑኑ የፌዴራል ቋንቋ ይሁን ብሎ ማስገደድን፣ የትምህርት ፍኖተ ካርታና ፖሊሲ ትግበራን በማወክ፣ የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ዕጣና ባለቤትነትን ለራሱ ሰዎች አሳልፎ በመስጠት፣ የመንገድ መዘጋትን በማነሳሳትና በመተባበር የአገር ሰላም እንዲጠፋ እያደረጉ ነው።

እንዲያውም ሥልጣንን ለመጠቅለል፣ ግዛትን ለማስፋፋት፣ የበላይነትን ለማንበር፣ ሽብርን እንደ ስትራቴጂ እየተጠቀሙበት ነው። ይህ የአክራሪ የኦሮሞ ቡድኖች የተጋነነ ማን አለብኝነት፣ ለሕዝብ ደኅንነት ችግር፣ ለአገር ህልውና አደጋ እየሆነ ነው። የፍትሕና የጸጥታ ጥበቃ አካላትም የችግሩ መፍትሔ ሳይሆን፣ የችግሩ ፈጣሪዎች፣ ሰዎችን ገዳዮች መሆናቸውን በኦሮሚያና በአዲስ አበባ አሳይተዋል።

የመንጋነት ባህሪ ሲበዛ፣ የእንስሳነቱ፣ የዘረኝነቱና የገዳይነቱ ሁኔታ ይበዛል። በተለይ በአገራችን ይህን መንጋነት የበለጠ የሚያግዝ የዘር ፖለቲካና የጎሳ ፌዴራሊዝም መተዳደሪያችን አድርገናል። እናም የምናየውን የዘር መጠፋፋት እያስከተለ ነው። ይህ በዚህ እንዳለ፣ የኦሮሞ ልኂቅ፣ አገርን ለመምራት የሚያስፈልገው የሥነ ልቦና ዝግጅት የሌላቸው፣ ዴሞክራሲ፣ የመንግሥት አስተዳደርና የፖለቲካ ሥልጣን ምን እንደሆነ ያልተረዱ የተረኞች ስብስብ መሆኑን በተግባሩ እያረጋገጠ ነው።
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የገዳ ስርዓት ልጅ ነኝ የሚለው፣ ተጨቁኛለሁ ይል የነበረው የኦሮሞ ልኂቅ፣ አሁን ግን ተረኛ ነኝ ልግዛችሁ፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር መታወቂያ ኦሮሞ ለሆነ አዳይ፣ ቄሮን ቀላቢና ተከራይቶ አስቀማጭ፣ ሁሉም ‘ኬኛ’ ባይ፣ የከተማ ቤትና ቦታ ወራሪ፣ ባንክ ዘራፊ፣ ዘቅዝቆ ሰቃይ፣ መሣሪያ ደቅኖ ግብር ሰብሳቢ፣ ብሔር እየለዩ አፈናቃይ፣ በአዋሳኝ ድንበሮች ጦርነት ከፋች፣ ቤተ ክርስቲያን ዘራፊና አቃጣይ፣ የአገርን እሴት አጥፊ፣ የጋራ ርዕይ እንዳይኖር አድራጊ፣ አገራዊ ፖሊሲዎች ላለመውጣታቸው ወይም አለመተርጎማቸው ምክንያት፣ ለአንድ ክልል ብለን ሕገ መንግሥት አናሻሽልም ባይ፣ ሰዎችን አፈናቃይና ግድያ ፈጻሚ ሆኗል።
ይህም የሚሆንበት ምክንያት፣ ተረኝነቱን እውን ለማድረግ በእያንዳንዱ ቀን ለሕዝቡ የቤት ሥራ ስጠው፣ ‘በአንዱ ሲጮህ፣ በሌላው ሲተካ’፣ ሥልጣኑን የኛ ማድረጉን፣ የሁሉም ተጠቃሚዎቹ እኛን ማድረጉን፣ ከአስፈለገም መገንጠሉን እውን እናደርጋለን ነው። ብጥብጥና አለመረጋጋትን ለሥልጣን መቆጣጠሪያ መንገድ አድርጎ መጠቀምም ነው።

በሌላ ክልል የተፈፀሙ ግጭቶችን ለማቀጣጠል በሚያስችል መልኩ ባለሥልጣኖችና ሚዲያዎቻቸው ሲያራግቡት፣ በኦሮሚያ አሰቃቂ አረመኔዊ ግድያ ሲፈፀም ሰው ሲፈናቀል ሀብት ንብረቱ ሲዘረፍ ምንም እንዳልተፈጠረ በዝምታ ማለፍ ምርጫቸው እንደሆነ አይተናል። ምክትል ኢታማዦር ሹሙ ጎንደር ላይ የተከሰተውን ግጭት “ሽፍቶች” ብሎ ሲል በደንቢ ደሎ ብቻ 30 የመንግሥት አመራሮች ሲገደሉ ነገሩን ቀለል አርጎ አልፎታል። በአዲስ አበባ ጎዳና በመከላከያ አራት ሰዎች ሲገደሉም “መሣሪያ ሊቀሙ” ሲሉ የሚል መግለጫም በፖሊስ ተሰጥቷል።

ከአንድ ሺሕ 500 በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ጦላይ አስሮም ሥልጠና እየሰጠኋቸው ነው ሲል ተደምጧል። በለገጣፎ፣ በቡራዩ፣ በሰበታ በላያቸው ላይ ቤት የፈረሰባቸው ዛቻ፣ ማስፈራሪያና ግድያ የተፈፀመባቸው መጠለያ አጥተው ጎዳና ላይም የወደቁ አሉ። በሐዋሳ፣ በጌዲዮ፣ በዶዶላ፣ በናዝሬት፣ በደብረ ዘይት፣ በባሌ፣ በአርሲ ኮፈሌ የተፈፀሙ ወንጀሎች እንደተሸፋፈኑ ናቸው። እንግዲህ ይህ እየሆነ ያለው በኦነግ/ኦዴፓ ነው። በ27 ዓመታት ውስጥ ሕወሓት ከሠራችው፣ በአንድ ዓመት በኦነግ/ኦዴፓ የተሠራው የአገር እሴት ማጥፋት በእጅጉ የበለጠ የሆነውም ለዚህ ነው።

ኦነግ/ኦዴፓ የእንገንጠል ጥያቄውን ፊት ለፊት ያቅርብ፣ መንግሥትና ሕዝብም ይህን ጥያቄ በምን መንገድ እንደሚያስተናግደው እንይ፤ ያለዚያ አምነው ለሰላማዊ ትግል ይንቀሳቀሱ። የት እንደቆሙ በማይታወቅበት ሁኔታ የአገርን ሰላም እያጠፉ ነው። ፅንፈኞቹ ዘላለም እያስፈራሩ ሰላማዊው ሕዝብ ደግሞ ለአገር አንድነት እያለ እየተጨነቀ እና በገዛ አገሩ እየተሸማቀቀ የሚኖርበት ሁኔታ አንድ ቦታ ላይ ማቆም ይኖርበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ፣ መከላከያ ሚኒስትር፣ ኢታማዦር ሹም፣ የፍትሕ፣ የፋይናንስ፣ የፖሊስና የደኅንነት ወዘተ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ የሚወሰንባቸው ቁልፍ ቦታዎችን ኦሮሞዎች ይዘው ባለበት ሁኔታና ችግሮች ሁሉ ቀስ በቀስ፣ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ችግር በሚፈታና ተጨማሪ ችግር በማይፈጥር ሁኔታ፣ በጥናትና ፖሊሲ መፈታት ይኖርባቸው ነበር።

በኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ቴሌቪዥን የሚተላለፍ የኦነግ/ኦዴፓ የጥላቻ ንግግሮች፣ ተጋንኖ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄና ያልተፈቱ ናቸው ተብለው የሚነገሩ (የአዲስ አባባ የባለቤትነት ጥያቄ፣ ኦሮምኛ የፌዴራል ቋንቋ ይሁን ጥያቄ፣ የፌዴራል ስርዓቱን ለመናድና አሃዳዊ ስርዓትን ለመመለስ የሚሉ ክሶች) የኦነግ/ኦዴፓ የመገንጠል ጥያቄዎች መሆናቸው የታወቀ ነው። ይህም ሥልጣናቸውንና የሚመሯቸውን ተቋማት የሚፈልጉትን የፖለቲካ ዓላማ ለማስፈጸም እንዳሻቸው እየተጠቀሙባቸው ለመሆኑ ማስረጃ ነው።

ኦነግ/ኦዴፓ የመንግሥት አካል ሆኖ የሕዝብን ጥያቄ ይመልሳል እንጂ፣ እንዴት ጥያቄ በጥያቄ ይሆናል? ጥያቄ አታብዙ ጥያቄውን የምትመልሱት እራሳችሁ ናችሁና። ስርዓት አልበኝነቱን የሚመሩት ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆኑ መሪዎች ናቸው። ይሄ ሁሉ ሲሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩና የገዢው ፓርቲ ሊቀመንበር ዐቢይ አሕመድ ናቸው። ካልቻሉ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቅ ሲገባ፣ ከጽንፈኞቹና ስርዓት አልበኞቹ ጎን ቆመው ወይም እያባበሉ አገሪቱን እያተራመሱ ነው።

ፖለቲካ በአንድ አገር ውስጥ ያለ ሕዝብ የሚፈልገውን ነገር እውን ለማድረግ የሚያስችል የሐሳብና የተግባር የትግል ሒደት ነው። ነገር ግን በደንብ በታሰበበትና ጎጂነትን በሚቀንስ መንገድ ካልተመራ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። የብሔር ፖለቲካ ጎጂነቱን፣ ከፋፋይነቱን፣ ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ማጋጨቱን፣ ለሰላምና ለልማት የማይበጅ እንቅፋት መሆኑን በተግባር ተመልክተናል። የብሔርተኝነት ፖለቲካ የዘረኝነት ፖለቲካ ነውና። ያም ሆኖ አሁን ካለንበት የከፋ ሁኔታ ውስጥ ያልገባነው ውጭ ሆኖ በሚመለከተው መልካም አሳቢ እና ክፉ ተጠያፊ አብዛኛው ሕዝብ የተነሳ ነው።

ፖለቲከኞች የሚሰብኩት በጀነቲክስ ሳይቀር የተለያየን እንደሆንን ነው። የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግሬ ደም የሚባል ነገር የለም። ደም (premordial) የሚለውን የጀነቲክስ የመዛመድን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። መዛመዳችን የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግሬ ደም እንዳንል አድርጎናል። ብሔር የደም ሳይሆን የማኅበራዊ ሒደት (social construct) ውጤት ነውና። ስለዚህ የሌለ ልዩነት እየተፈጠረ ሕዝብ ማጋጨቱ ይበቃል መባል አለበት።

ለአንድ አገር ጠንካራነት ወይም ደካማነት ባህል ወሳኝ ነገር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ሃይማኖት ባህል ነው። ሃይማኖትን ለማፍረስ የሚሞክር ማንም ቡድን ባህልን ለማፍረስ እየሞከረ ነው። ባህልን ለማፍረስ የሚሞከር ደግሞ አገር እያፈረሰ ነው። እናም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ለማፍረስ የሚሞክር ደግሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እቅድ ያለው ነው። ስለዚህ የነኩብንና ለማፍረስ እየሞከሩ ያሉት ሃይማኖታችንን ብቻ አይደለም፤ አገራችንን ጭምር እንጂ።

የሰሜኑን አባታዊና ተዋረዳዊ የሆነው ለአስተዳደር የሚመችውን፣ ግን በተወሰነ የዴሞክራሲያዊ ባህሪያት የሚጎሉትንና የደቡቡን በተለይም የኦሮሞውን አባታዊ ያልሆነውንና ለአስተዳደር የማይመቸውን፣ ግን ደግሞ በተወሰነ ዴሞክራሲያዊ የሆነውን ስርዓት እንዴት አስታርቀን የተሻለና ለሁላችን የሚሆን ስርዓት እንፍጠር የሚለውም ጥያቄ መመለስ አለበት።

ይህ የማሸነፍ፣ መሸነፍ አዙሪት አሁን እንዲቆም፣ የተሻለው የችግሩ መፍትሔ፣ ይህን የጥላቻና የባህል ጦርነት አቁሞ ለዴሞክራሲያዊቲ ኢትዮጵያ ግንባታ መጣር ነው። የኢትዮጵያን አንድነት ለሚፈልግ ሁሉ ጥያቄው ሁሉም ጎሳዎች በአንድነት እንዴት እናደራጅ እና ዳር ተመልካች ልኂቃንን እንዴት አሳታፊ እንዲሆኑ እንድርግ የሚል መሆን አለበት። ለዚህም የአጭርና የረዥም ጊዜ እቅድና ስትራቴጂ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ባለእውቀት፣ የተረጋጉና አስተዋይ መሪዎች ያስፈልጋሉ።

መንግሥትም የመንግሥትነት ኀላፊነቱን ወንጀል እንዳይፈጸም በመከላከል፣ ተፈጽሞ ከተገኘም ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ መወጣት ይኖርበታል። ያለዚያ ግን በ‹‹አከርካሪያቸውን ሰበርናቸው›› በተጀመረው የዘር ጭፍጨፋ ሒደት ማንም ወደማያተርፍበት ወደ ለየለት የእርስ በርስ ጦርነት እንደምንገባ ጥርጥር የለውም። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተገዥና ኹለተኛ ዜጋ መሆንን የሚቀበል ማንም የለምና።

የምንፈልገው ባህላችን፣ ሃይማኖታችን እንዲጠበቅ ነው። የምንፈልገው ከአገሪቱ አጠቃላይ የውጭና የአገር ውስጥ 53 ቢሊዮን ዶላር (27 ቢሊዮን ዶላር ከተለያዩ የውጭ አበዳሪዎች እና 26 ቢሊዮን ዶላር ከአገር ውስጥ የመንግሥት ባንኮች የተገኘ) ዕዳ የሚገላግለን፣ የኑሮ ውድነትን የሚቀርፍ፣ ሥራ ፈጠራን የሚያግዝ፣ የሀብት ክፍፍልን፣ የኢኮኖሚ መጠናከርን የሚያመጣ ስርዓት ነው። የምንፈልገው ምርጥ ኢትዮጵያውያን ወደ መሪነት የሚመጡበትን ስርዓት እንጂ፣ የኦሮሞ አክራሪዎች በተረኝነት አገርን የሚያፈርሱበት ስርዓት አይደለም። ስለዚህም ሕግ የበላይነትና ሕጉን በአጥፊዎች ላይ ያለ አድሎ በመተግበር የሕዝብ ደኅንነትና የአገር ህልውና ይጠበቅ።

ሕዝቡም በሕወሓትና በኦነግ ስርዓተ አልበኝነት፣ በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ፣ በተቋማት ግንባታና ገለልተኝነት እንዲሁም በተገቢ ሕጎች መውጣትና መሻሻል ላይ ጥያቄውን በተደራጀ መልኩ ለፌዴራል መንግሥቱ ማቅረብ አለበት። ሁላችንም ዜጎች ማወቅ ያለብን፣ እየመጣ ያለው ካለፈው የባሰ ነውና መብታችንን ለማስጠበቅ፣ ለዴሞክራሲያዊና ሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄያችን መልስ በአንድነት መነሳትና መጠየቅ ይገባል።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here