ማን ተጠያቂ ይሁን?

0
845

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት እና ሕግ የሌለ እስኪመስል ድረስ ሥርዓት አልበኝነት የተንሰራፋው መንግሥት ሕግ የማስከበር ኀላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ነው የሚሉት ሚኒልክ አሰፋ፣ ይህም የሆነበት ጠንካራ የፍትሕ ስርዓት እንዲሁም የፖሊስ አቅም አለመኖር መሆንም በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። የወንጀሉን ዋና አድራጊዎች ለይቶ ለፍርድ የማቅረቡ ሒደት በራሱ የወንጀሉን አነሳሾች እና አቀነባባሪዎች የማጋለጥ አቅም ስለሚኖረው የመንግሥት ዋና ትኩረትም እዚሁ ላይ መሆን ይገባዋል ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከሰቱትን ጨምሮ በቅርቡ የተስተዋሉትን ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች በዘላቂነት እንዳይታረሙ ከሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶቸ ውስጥ ጥፋተኞች ተጠያቂ ሳይሆኑ መታለፋቸው የፈጠረው የማናለብኝነት ስሜት ነው። ግጭቶቹን ከማነሳሳት አንስቶ ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ንብረት በማውደም፣ አካላዊ ጥቃትን በማድረስ እና ነብስ ማጥፋት ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች ለሕግ ቀርበው አለመቀጣታቸው ሥርዓት አልበኝነት እንድንላመደው አድርጎናል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በሁኔታዎቹ ለተከሰቱት ጥፋቶች ሁሉ የተወሰኑ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞች እና ቡድኖችን በጅምላ ተጠያቂዎቸ እንዲሆኑ ግፊት የማሳደር አዝማሚያዎች በመደበኛ እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ተስተውለዋል።

በሕግ መሰረት ወንጀለኛ ሊባሉ የሚችሉትን ለይቶ ለፍርድ ማቅረብ የመንግሥት፣ በቀረቡ ማስረጃዎች መሰረት የግለሰቦችን ጥፋተኝነት አረጋግጦ ቅጣትን መወሰን ደግሞ የፍርድ ቤት ኀላፊነት ቢሆንም፤ የሕግ ሥርዓቱ ተዓማኒነት ከማጣት አልፎ አቅመ ቢስ በሆነበት በዚህ ሰዓት ወንጀልን መጠቆምም ሆነ ሕግ እንዲከበር መወትወት ከዜጎች የሚጠበቅ ተገቢ ተግባር መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።

ሆኖም ያገባኛል በሚሉ ዜጎች እና ፖለቲከኞች ሕግ እንዲከበር የሚደረጉ ጥቆማዎች፣ ጥሪዎች እና ዘመቻዎች ተጨባጭነት ሊኖራቸው ይገባል። ተጨባጭነት ከሕግ አንጻር ወንጀል ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶችን ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መለየትን የሚያመላክት ሲሆን ከግል ፍላጎት እና ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ ድርጊቶቹን መመልከትን ይጠይቃል። ለዚህም ተመሳሳይ ኹነቶች እና ግጭቶች ሲከሰቱ የትኞቹ ዓይነት ድርጊቶች በሕግ መሰረት ወንጀል ሊባሉ ይችላሉ? የትኞቹ አካላት በወንጀሉ ውስጥ ምን ዓይነት ተሳትፎ ነበራቸው፤ ተጠያቂነታቸውስ ምን ድረስ መሆን አለበት? የሚለው ላይ መሰረታዊ ግንዘቤ ያስፈልጋል።

አንድ ወንጀል በወንጀልነት የሚያስጠይቀው ሦስት ሁኔታዎች ሲሟሉ መሆኑ ይታወቃል። የመጀመሪያው ድርጊቱን ማድረግ (አልፎ አልፎም አለማድረግ) እንደሚያስቀጣ በሕግ መደንገጉ (ሕጋዊነት)፤ ኹለተኛው ድርጊቱ እንደተፈፀመ መረጋገጡ (ድርጊት) ሲሆን ሦስተኛው እና የመጨረሻው ደግሞ አድራጊው ሰው ድርጊቱን የፈፀመው አስቦ ወይም በቸልተኝነት መሆኑ (የወንጀል ሐሳብ መኖሩ) ነው።

የመጨረሻው ሁኔታ በሕግ ባለሙያዎች ዘንድ የወንጀል የሐሳብ ክፍል ተብሎ የሚጠቀስ ሲሆን አንድ ሰው ፈፀመ የተባለውን ድርጊት ሙሉ በሙሉ የመፈፀም ፍላጎት የነበረው መሆኑን ወይም በተወሰኑ ሁኔታዎች በቸልተኝነት ነበረበት የሚለውን የማረጋገጥ ግዴታን ይጥላል። ከዚህ አንፃር በአገራችን በተለያየ ወቅት በተለያየ አከባቢ የፀጥታ መደፍረሶች ሲከሰቱ በሰው እና በንብረት ላይ ያጋጠሙ አደጋዎች አብዛኞቹ በወንጀል የሚያስጠይቁ ቢሆኑም የተለያዩ አካላት በወንጀሉ ውስጥ የነበራቸው ተሳትፎ ግን የሚለያይ ነው።

አንድን ድርጊት በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር የፈፀመ ሰው የወንጀሉ ዋና አድራጊ ሆኖ እንደሚቀጣ የወንጀል ሕጉ ያስቀምጣል። በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰቱ ግጭቶች ውስጥ በቀጥታ የተሳተፉ ሰዎችን ከላይ ካስመጥናቸው ሦስቱ የወንጀል ተጠያቂነትን ከሚያስከትሉ ሁኔታዎች አንጻር ወንጀለኝነታቸውን አረጋግጦ ለፍርድ ማቅረብ ከሕግ አስከባሪ አካላት የሚጠበቅ እጅግ ቀላሉ ተግባር ነው። ምክንያቱም በመሰል ግጭቶች ውስጥ በቀጥታ የተሳተፉ ሰዎች የወንጀል ድርጊቱን እንደፈፀሙት የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ማግኘት፤ በግጭቶቹ ውስጥ ‹ስውር እጅ አላቸው› የተባሉትን ሰዎች በወንጀሎቹ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ የማረጋገጥን ያህል ከባድ አይሆንም።

ስለሆነም የሕግ የበላይነት እንዲከበር እና መሰል ግጭቶች ውስጥ የሚከሰቱ ጥፋቶችን በዘላቂነት ለማስቀረት መደረግ ካለባቸው ሕጋዊ ተግባራት መካከል ቀዳሚ የሚሆነው በግጭቶቹ ውስጥ በነፍስ ማጥፋት፣ ዘረፋ፣ ንብረት ማውደም፣ አካል ላይ ጉዳት ማድረስ እና በተለያዩ ወንጀሎች በቀጥታ የተሳተፉ ግለሰቦች ለፍርድ ማቅረብ ነው። ይህ መሰረታዊ የሚባል የሕግ ማስከበር ሥራ በአግባቡ ባልተከናወነበት ሁኔታ ‹ከወንጀሉ ጀርባ የእነ እገሌ እጅ አለበት› ወይም ‹ወንጀሉን ያነሳሳው እገሌ ነው› ብሎ በፍርድ ፊት ለማረጋገጥ እጅግ ከባድ ወደሚሆኑት፤ በአነሳሽት እና በወንጀል አቀነባባሪነት ሊጠየቁ ወደሚችሉ ቡድኖች እና ግለሰቦች መጠቆም በወንጀል ፍትሕ ሥርዓታችን ከመሳለቅ አይተናነስም።

ነገር ግን ይህ ማለት በወንጀል አነሳሽነት እና አቀነባባሪነት የተሳተፉ ሰዎች ቸል ሊባሉ ይገባል የሚል ትርጓሜን መስጠት አይኖርበትም። አንድ ሰው ወንጀሉን በአካል ተገኝቶ ባይፈፅመውም ከበስተጀርባ ሆኖ ወንጀሉን ጊዜና ሁኔታ በማቀድ፣ ወንጀል ፈፃሚዎችን በመመልመል፣ ወንጀሉ የሚፈፀምበትን መሣሪያ በማዘጋጀት እና ስልት በመንደፍ ተሳተፊ ከሆነ የወንጀሉ ዋና አድራጊ ተብሎ እንደሚቆጠር የወንጀል ሕጉ ደንግጓል።

እነዚህ ዓይነት ወንጀለኞች ተለምዶ የሞራል ወንጀለኞች በመባል የሚታወቁ ሲሆን የወንጀሉን ሐሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ወንጀሉ የሚፈፀምበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ወንጅሉ የሚፈፀምበትን የሰው ኀይል እና የመሣሪያ አቅም በማደራጀት ሙሉ ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው። በዚህ መሰረት በተለያዩ ግጭቶች ውስጥ በነብስ ማጥፋት፣ ንብረት ማጥፋት፣ አካል ማጉደል እና መሰል ወንጀሎችን በቀጥታ የፈፀሙት እንደሚቀጡ ሁሉ የወንጀል ድርጊቱን በመጠንሰስ እና በማቀነባበር የተሳተፉ ሰዎች ካሉ የሞራል ወንጀለኞች ተብለው በዋና ወንጀል አድራጊነት መጠየቅ ይኖርባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ወንጀልን ያነሳሱ ሰዎች በኹለተኛ ደረጃ የወንጀል ተሳትፎ ሊጠየቁ ይችላሉ። የእነዚህ ዓይነት ወንጀለኞች ወንጀሉ በዋናነት ያቀነባበሩ እና የፈፀሙ ሳይሆኑ ሌላ ሰው ወንጀሉን እንዲፈፅም በተለያየ መንገድ የቀሰቀሱ ናቸው። ይህም ቅስቀሳ በገንዘብ፣ በስጦታ፣ በማስፈራራት አልያም በመጎትጎት እና ተስፋ በመስጠት ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ አንድ ሰው ወንጀሉን እንዲፈፅም ማግባባትን ይጨምራል።

የወንጀል አነሳሾች ከላይ ካነሳናቸው (የሞራል ወንጀለኞች ተብለው ከሚታወቁት) ዋና የወንጀል አድራጊዎች የሚለዩት ወንጀሉን አስበው ሌላ ሰው እንዲፈፅመው ግፊት ከማሳደር ያለፈ ወንጀሉን በማቀድ እና በማቀነባበር ተሳትፎ ስለሌላቸው ነው። ወንጀሉ እንዲፈፀም አስቦ ቅስቀሳ ያደረገ ሰው የወንጀል አነሳሽ ተብሎ ሲቀጣ፤ ወንጀሉ እንዲፈፀም አስቦ እቅድ ያወጣ፣ ሰዎችን የመለመለ፣ መሣሪያ ያቀረበ እና ሁኔታውን ያቀነባበረ ሰው ከአነሳሽነት አለፍ ብሎ በዋና ወንጀል አድራጊነት ይቀጣል። በተጨማሪም ወንጀል እንዲፈፀም በአደባባይ መገፋፋት ራሱን የቻለ ወንጀል ሆኖ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 470 ላይ ተቀምጧል።

ነገር ግን ወንጀሉን ከበስተጀርባ በማቀነባበር ወይም በአነሳሽነት የሚጠረጠሩ ሰዎች በወንጀሉ ውስጥ የነበራቸውን ተሳትፎ ማረጋገጥ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ወንጀልን አነሳስቷል ወይም አቀነባብሯል ተብሎ የሚጠረጠር ሰው ወንጀሉ እንዲፈፀም ፍላጎት (ሐሳብ) እንደነበረው በግልፅ ወይም በተዘዋዋሪ ማስረዳት እስካልተቻለ ድረስ፤ ወንጀሉን አነሳስቷል ወይም እጁ አለበት ተብሎ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ይህም የወንጀል አነሳሽ የተባለው ግለሰብ ወንጀሉ እንዲፈፀም ከማሰብ ባለፈ፤ የወንጀሉ ፈስፃሚዎቹ ወንጀሉን እንዲፈፅሙ በቀጥታ ማግባባቱን ወይም ግፊት ማሳዳሩን ማረጋገጥ ይጠይቃል።

ወንጀሎቹን በቀጥታ የፈፀሙት ሰዎች፤ ወንጀሉን እንዲፈፅሙ ያደረጋቸው ግለሰቡ ያደረገው ቅስቀሳ፣ ማግባባት ወይም ግፊት መሆኑን በግልፅ የሚያመላክት ማስረጃ ባልተገኝበት ሁኔታ ሰዎችን በአነሳሽነት ወንጀል ተጠያቂ ማድረግ አዳጋች ነው። ወንጀልክን ከጀርባ ሆኖ በማቀነባባር የሚጠረጠር ግለሰብን ተጠያቂ ማድረግ ደግሞ ግለሰቡ ወንጀሉ እንዲፈፀም ለወንጀል ፈጻሚዎቹ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ትዕዛዝ መስጠቱን በተገቢ ሁኔታ ማረጋገጥን ይጠይቃል።

ይህንን ሁሉ አጣርቶ እና ለይቶ ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ ማቅረብ በዋናነት የመንግሥት ኀላፊነት እንደሆነ እሙን ነው። ነገር ግን መንግሥት ይህን ኀላፊነቱ እንዲወጣ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ፖለቲከኞች እና የሚዲያ አካላት የሚደረጉ ጥሪዎች እና ዘመቻዎች ስልታዊ ሆነው ይህን የሕግ አረዳድ የማይከተሉ ከሆነ መሬት ጠብ የሚል በጎ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም አይኖራቸውም። በፖለቲካ አቋም ከእኛ በተጻራሪ የቆመን አካል ሁሉ ለተፈጠሩት ነገሮች ተጠያቂ እንዲሆን ግፊት ማሳደር ሕግ እንዲከበር አስተዋፅዖ ከማሳደር ይልቅ ጥላቻን የበለጠ በማጠናከር ሥርዓት አልበኝነቱን የሚያስቀጥል ሆኖ ሊገኝ ይችላል።

በአገራችን በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው የፖለቲካ ውጥረት እና የደኅንነት ስጋት ‹የወያኔ እጅ አለበት› ወይም ‹ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ጃዋር ነው› በሚል ቀላል ትንታኔ መፍትሔ የሚያገኝ አለመሆኑም ሊሰመርበት ይገባል። ለውስብስብ ችግሮቻችን ‹እነ እገሌ ይታሰሩ› የሚል ተራ መፍትሔን ማቅረብ ቀላል ቢመስልም፤ ወንጀልን በቀጥታ የፈፀሙ ሰዎችን እንኳን ለፍርድ ማቅረብ ያዳገተው የፍትሕ ሥርዓታችን ፖለቲካዊ መልክ የሚኖራቸውን ወንጀሎች ለመመርመር በሚያደርገው ጥረት የሚፈፅማቸውን ስህተቶች መገመት ከባድ አይሆንም።

በቅርቡ እንኳን ከሰኔ 15ቱ የባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የ‹አዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት› አባላት ያለ ክስ ለወራት በእስር እንዲቆዩ መደረጋቸው ተሻሽሏል ተብሎ በሚጠቀሰው የመንግሥት የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ብዙዎች ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓል።

ቀዳሚው ተግባር
በአገሪቱ ላይ መንግሥት እና ሕግ የሌለ እስኪመስል ድረስ ሥርዓት አልበኝነት የተንሰራፋው መንግሥት ሕግ የማስከበር ኀላፊነቱን ባለመወጣቱ እንደሆነ አጠያያቂ አይደለም። ይህ የሆነበት ምክንያት የመንግሥት አቅም መዳከም ወይም በዚህ ረገድ ካለ የመንግሥት የቁርጠኝነት መጉደል ሊሆን ይችላል። ሆኖም አገራችን ላለችበት የፖለቲካ ውጥረት እና የደኅንነት ሥጋት ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው መሰረታዊው ጉዳይ ግን ይህ ሕግን የማስከበር ተግባር መሆኑ ሊታመንበት ይገባል።

በዘመናዊውም ሆነ ቀደም ባለው የመንግሥታት ጽንሰ ሐሳብ መሰረት የማንኛውም መንግሥት ቀዳሚ ተግባር አቅመቢሶችን ከጉልበተኞች መከላከል ነው። ብሔር ተኮር ግጭቶችም ይሁኑ ማንኛውም ዓይነት ሕዝባዊ አለመረጋጋቶች ሲፈጠሩ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ በዋነኝነት ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ጉዳይ የተለያዩ ወንጀሎችን በቀጥታ የፈፀሙ ግለሰቦችን ለይቶ በቁጥጥር ሥር ማዋል እና ለፍርድ ማቅረብ ነው። ይህ ተግባር ጥፋተኞችን ለፍርድ አቅርቦ ፍትሕን ከማረጋገጥ ባለፈ በቀጣይ መሰል የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ ማስተማሪያ እና ማስጠንቀቂያ መሆኑ ግልፅ ነው። የሕግ ማስከበር ሀ-ሁ ይሄ ነው!
ሌላኛው መሰረታዊ ጉዳይ የግጭት እና ያለመረጋጋት ምልክቶች በሚታዩባቸው አካባቢዎች ላይ የሕግ አስከባሪ አካላት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገው ጥፋቶች ከመድረሳቸው በፊት የወንጀል መከላከልን ሥራ መስራት መቻላቸው ነው። በቅርብ ጊዜያት የተስተዋሉ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት ይፋ የሆኑ ቅስቅሳዎች እና የጥፋት ቀጠሮዎች የነበሩ ቢሆንም፤ ፖሊስ ምንም ዓይነት የቅድመ መከላከል ሥራ ሳይሠራ ቆይቶ ግጭቶቹ ቀናትን ካስቆጥሩ በኋላ እሳት ለማጥፋት ያህል ወደ ቦታዎቹ መዝለቁ አሳፋሪ አቅመ ቢስነት አልያም ቸልተኝነት ከመባል ውጪ ከዘመናዊ መንግሥት የሚጠበቅ አይደለም።

ከዚህ በመቀጠል ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ደግሞ በግጭቶቹ ውስጥ የተለያየ ዓይነት ተሳትፎ ያላቸውን (ወንጀልን በማነሳሳት እና በማቀነባበር የሚጠረጠሩ) ግለሰቦችን ለፍርድ ማቅረብ ነው። ነገር ግን በዚህ ደረጃ ያሉ ወንጀለኞችን የመለየት እና ለፍርድ የማቅረብ ተግባር የተለየ ትኩረትን እና ልዩ አቅም የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት አንድም እነዚህን ዓይነት ወንጀሎች ለማጣራት እና ለመመርመር ላቅ ያለ የፍትሕ ሥርዓት እና የፖሊስ አቅም ማስፈለጉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የማይጣስ መሆኑን የሚያረጋገጥ ጠንካራ ሥርዓት ማስፈለጉ ነው።

ለምሳሌ ያህል በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው የጥላቻ ንግግር እና የሀሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ በሕዝቦች መሀል የሚነሱ ግጭቶችን ለመከላከል የሚኖረው አስፈላጊነት ያለማጠያየቁን ያህል፤ የዜጎችን ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በሚጋፋ ደረጃ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩ የሚታወቅ ነው። በመሆኑም በሥራ ላይ ባለው የወንጀል ሕግም ሆነ በቅርቡ ይፀድቃሉ ተብለው በሚጠበቁ ተያያዥ ሕጎች አማካኝነት የዜጎችን መብት ለድርድር በማያቀርብ መልኩ የወንጀል አነሳሾችን እና አቀናባሪዎችን መከላከል እና መቅጣት ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው።

ከሁሉም በላይ ግን የወንጀሉን ዋና አድራጊዎች ለይቶ ለፍርድ የማቅረቡ ሒደት በራሱ የወንጀሉን አነሳሾች እና አቀነባባሪዎች የማጋለጥ አቅም ስለሚኖረው የመንግሥት ዋና ትኩረት ዋና የወንጀል ፈፃሚዎችን ተከታትሎ ለፍርድ ማቅረብ መሆን ይገባዋል። ከዚህም ባለፈ ቀጥተኛ የወንጀል ፈጻሚዎችን ለፍርድ ማቅረብ ላይ ጠንካራ ሥራ ከተሠራ፤ ግጭትን የሚያነሳሱ እና የሚያቀነባብሩ ቢኖሩ እንኳን በግጭቶቹ እና በወንጀሎቹ መሳተፍ የሚያስከትለው ሕጋዊ ውጤት መኖሩን የሚያውቅ ዜጋ ደፍሮ በወንጀል የመሣተፍ እድሉ አናሳ ይሆናል።

ሚኒሊክ አሰፋ የሕግ ባለሙያና ተመራማሪ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው minilikassefa@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here