የኢሕአዴግ ውህደትና የሕወሓት ማፈንገጥ

0
411

በአራት እህትማማች ድርጅቶች ጥምረት ተገንብቶ ኢትዮጵያን ላለፉት 28 ዓመታት ሲያስተዳድር ቆየው ግንባር ኢሕአዴግ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ‹ግንባርነቴ ይብቃኝ ወደ ፓርቲነት መሸጋገር እፈልጋለሁ› ያለ ይመስላል። በዚህም ሒደት ታዲያ ገዢው ግንባር ኢሕአዴግ ፓርቲ የመሆን ህልሙን በአራቱ እህትማማች ድርጅቶች ውህደት በመጀመር አጋር ተብለው የተሰየሙትን አራቱን አጋር ፓርቲዎችንም በማቀፍ ‹ብልጽግና ፓርቲ› በሚል ብቅ ሊል መሆኑ የሰሞኑ መነጋገሪያ ርዕስ ነበር።

በተለይ ደግሞ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውህደቱን ተመርኩዞ የሦስት ቀናት ውይይት ባደረገበት ወቅት፣ በርካታ ራሳቸውን የሚቃረኑ በኹለት ጎራ ተከፍለው ሲያስተጋቡ ሰንብተዋል። የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን ውይይት የመሩት ግንባሩ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ነበሩ። ታዲያ በእያንዳንዱ የውይይት ቀናት ማጠቃለያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር እና ፌስ ቡክ ገጻቸው ብቅ ብለው፣ ውሎው አስደሳችና አመራሮችን ያቀራረበ እንደነበር ሲገልፁ ተስተውሏል።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በተለይ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር የሰነበተውን አንድ ፎቶ በመመርኮዝ፣ በርካቶች ሕወሓት በውይይቱ መከፋቱን የሚያመለክት ነው ሲሉ ተደምጠዋል። በግንባሩ ላዕላይ አመራሮች ደብረፂዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እና አዲስዓለም ባሌማ (ዶ/ር) ፊት አውራሪነት፣ ፊት መስመር ላይ የተሰለፈው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ውሕደቱን በተለመከተ ተቃውሞውን ማሰማቱን በርካቶች ተስማምተውበታል።

ስድስት የተቃውሞ ድምጽ የተሰማበት የውህደቱ መተዳደሪያ ደንብ ታዲያ በአብዛኞች ዘንድ ተቃውሞው የተሰማው ከሕወሓት ወገን ነው በሚል እርግጠኝነት ደምጸት ሲያራግቡትም ሰንብተዋል። በተለይ ደግሞ ከቢቢሲ አማራኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሕወሓት ነባር ታገይ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አስመላሽ ወልደሥላሴ፣ ከሕወሓት አባላት ውስጥ ‹ደምጽ በሚሰጥበት ወቅት መውጣት መግባት ስለነበር ደብረፂዮን እና ኬሪያ ድምጽ አሰጣጥ ሒደቱ አምልጧቸዋል› ሲሉ ተናግረዋል።

በዚሁ ሳይበቃ፤ ኅዳር 11/2012 ውህደቱን በሚመለከት ለመወያየትና ከሥራ አስረፈጻሚ ኮሚቴ የተላለፈለትን ለማጽደቅ 180 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት የጠራውን ስበሰባ ሕወሓት ከአንድ ቀን አስቀድሞ በጻፈው ደብዳቤ እንደማይሳተፍ አስታውቋል። ይህም በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ትስስር ገጾች በርካቶችን ኹለት ቦታ በመክፈል ቃላት ሲያወራውርና ትንታኔዎችም ሲሰጥበት ሰንብቷል። ሕወሓትን ‹አበጀህ፤ ከቆረጡ አይቀር እንዲህ ነው እንጂ!› በሚል ማሞካሸት ድምጻቸውን ያሰሙትን ያህል፤ ‹በቃ ሕወሓት አበቃላት፣ ግብዓተ መሬቷ እየተቃረበ ነው!› ያሉም ቁጥራቸው በርካታ ነበር። ሳምንቱ በኢሕአዴግ ውህደትና በሕወሓት ማፈንገጥ ውጥረት የተስተናገደበት ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here