‘‘የጦርነቱ ተራራ እንኳን አስከፍቶኝ አያውቅም፣ ጦርነት ላይ ቁጭ ብዬም እስቅ ነበር”

0
1185

የመጀመሪያ የትውልድ ሥማቸው በጂጋ ገመዳ ነበር፤ በኋላ ትምህርት ቤት ሲገቡ ምናሴ በሚል ተቀይሯል። በኋላ አባዱላ በሚል ጸንቶ ከዚሁ ሥማቸው በፊትም ጄኔራልን ጨምሮ የተለያዩ ወታደራዊ እና የሲቪል ኀላፊነቶች ተጠርተዋል፤ አገልግለውማል። በጥቅምት ወር ታትሞ ለንባብ የበቃው ‹‹ስልሳ ዓመታት›› የተሰኘ መጽሐፋቸው ከአያቶቻቸው ታሪክ ጀምሮ እስከ ራሳቸው፣ ልጆቻቸው እና አገራቸው ያለፈ እና ነባራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ መጪው ጊዜ ያላቸውን እይታ ጭምር ከትበውበታል።

በተለይም የኢህዴን፣ ኦህዴድ እንዲሁም የኢሕአዴግ ወታደራዊ እና የፖለቲካ ትግሎች መጋረጃ በስተጀርባ ያሉ ታሪኮችን ዳስሰውበታል። ከወራት በፊት የታተመው እና በልጃቸው ዲቦራ ሥም የተሰየመው መጽሐፋቸው፣ በአዕምሮ ዝግመት (ዳውን ሲንደሮም) የተጠቃች የ10 ዓመት ሴት ልጃቸውን ሕይወት እና በዚህ ውስጥ ቤተሰባቸው እና የቅርብ ጓደኞቻቸው ያሳለፉትን ውጣ ውረድ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው።

በይፋ ጡረታ ከወጡ በኋላ ሙሉ ጊዜአቸውን ስለሰጡት የዲቦራ ፋውንዴሽን በሰፊው ሐሳባቸውን ያካፈሉበት ይህ ቃለ ምልልስ፣ በተለይ ስለ ዳውን ሲንደሮም እና በአገራችን በዚህ ችግር ዙሪያ ስላለው የተለያዩ ችግሮች ሐሳባቸውን በሰፊው ያካፈሉበት ነው። ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በኢትዮጵያ ለታየው የፖለቲካ የለውጥ ሒደት መሃንዲስ ናቸው በሚል በቅርብ በሚያውቋቸው ሰዎች ዘንድ የሚነገርላቸው አባዱላ፣ ከአዲስ ማለዳዋ ሐይማኖት አሸናፊ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በኢትዮጵያ ውስጥ እየታዩ ስላሉ ቀውሶችም የግል አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያውያን አባቶች በልጆች አስተዳደግ ተሳታፊ አይደሉም። በሥራ ክፍፍል ልጅን መንከባከብ ለእናት የተሰጠ ነው። እርስዎ ደግሞ ከልጆችዎ ጋር እና ቤት ውስጥ በጣም ቅርብ እንደሆኑ በዲቦራ መጽሃፎት ላይ ጠቅሰዋል፤ ይህን ከማን ወረሱት?
እኔ ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ነው ተወልጄ ያደግኩት። እኔ ራሴ ደግሞ ቤተሰብ የፈጠርኩት ደግሞ ከሰፊ ጦርነት በኋላ ነው። ብዙ ጓደኞቻችን ተሰውተውና አልፈው በአጋጣሚ የተረፍን ነን ሰላም ተፈጥሮ ሰላማዊ ቤተሰብ ለመፍጠር ዕድል ያገኘነው። ስለዚህ ልጅ በጣም እወዳለሁ። የመጀመሪያው ልጄ ከተወለደ ጀምሮ አልተለየሁትም። ገጠር እሔዳለሁ፣ እዞራለሁ፤ ግን ደግሞ የተለየ የሚያቆይ ስብሰባ አልያም ሌላ የመንግሥት ወይም የድርጅት ሥራ ከሌለኝ በቀር፤ ኹለት ሰዓት ገብቼ እስኪተኙ በትንሹ ለአንድ ሰዓት ከእነርሱ ጋር እቆያለሁ።

እርግጥ እንደዛም ሆኖ የእናት ሚና በጣም ትልቅ ነው። ባለቤቴ ሙሉ ጊዜዋን ለእነርሱ ነው የሰጠችው። ትምህርት ቤት ትወስዳቸዋለች፣ ትመልሳቸዋለች አብራ ትሆናለች፤ ሁሉንም። እንዳልኩት ኹለት ሰዓት ላይ ገብቼ ከእነሱ ጋር ካልተጫወትኩ ደስ አይለኝም። የሆነ ነገር የጎደለብኝ ዓይነት ስሜት ይሰማኛል። እነርሱም እንደዛው ናቸው። ውጭ አገር ሄጄ ደውዬ ሁሉንም ካላነጋገርኩ ደስ አይለኝም። በዚያ ዓይነት ጉዞ ላይ የማገኘው አበል በስልክ ነው የሚያልቀው። እኔ ልጆቼን ‹የት አባ’ክ› ብዬ ተሳድቤ አላውቅም። የመጨረሻው የኔ ቁጣ ‹አኮርፍሃለሁ…አኮርፍሻለሁ›ነው። አኮርፍሃለሁ ካልኩ ሦስት ቀን ራሱ እያለቀሰ ያኮርፋል። (ትንሽ ሳቅ)
ግንኙነታችን ትንሽ ጠበቅ ያለ ስለሆነ ነው። እንደዛ ማድረግ በጣም ይጠቅማል። ከተፈራሩ ምስጢር የሚያደርጓቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ። ምስጢር ከኖረ ደግሞ ለመገንባት አይመችም። ስለዚህ የኔ ልጆች ከሁሉ በላይ ለእናታቸው ምስጢር የላቸውም። ቀጥሎ ለእኔ ብዙ የሚደብቁት ነገር የለም። ደንግጠው የሚደብቁኝ ነገር ካለ ዐይናቸውን ሳይ አውቅባቸዋለሁ።

ልጆችን መገንባት አለብን፤ ምክንያቱም ትውልድ መቀጠል አለበት። መንገዳቸውን የሚወስኑት ራሳቸው ናቸው፤ ግን የተሳሳተ እንዳይሆን ደግሞ መርዳት ያስፈልጋል። የሚማሩትና የተማሩት እዚሁ ነው። ያለኝን አጋጣሚ ተጠቅሜ ብዙ ልጆችን ውጭ አገር አስተምሬአለሁ፤ ለፒ.ኤች.ዲ ያደረስኳቸው፤ ለህክምና ዶክትሬት ያደረስኳቸውም አሉ። አሁንም አሜሪካ እና ቻይና የላኳቸው ልጆች አሉ። ተቸግሬ ከገጠር አምጥቼ አስተምሬ የውጪ የትምህርት እድል አፈላልጌ እልካለሁ።

በአብዛኛው ባለሥልጣናት የትምህርት ሚኒስትር ሆነውም፣ ልጆቻቸው አገር ውስጥ ከሚያስተምሩት የማያስተምሩት ይበልጣል ይባላል፤ እርስዎ እንዴት አገር ውስጥ ለማስተማር ወስኑ?
ልጆች ወደ ውጭ ሲሔዱ ኹለት ነገር ይጎድላቸዋል ብዬ አምናለሁ። ይሄን ሌላው ላያምንበት ይችላል። ልጆችን ልጅ የሚያደርገው የቤተሰብ ፍቅር ነው። ማንነታቸውን የሚገልጸው ቤተሰባቸው ነው። ማንም ሰው ለትምህርት በሔደበት አገር በሙያ የሚጨምረው ትንሽ ነው፤ ይዞት የሚያድገው ዋናው ባህሪ ቤተሰቡ ጋር የፈጠረው ነው።

ስለዚህ ከአገር በተለዩ ቁጥር ከቤተሰብ ፍቅራቸውና ከቤተሰብ ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ ከሰውም ጋር ያላቸው አጠቃላይ ነገር ይዘበራረቃል። ይሄን በጽኑ አምንበታለው። ብዙ ዕድል ነበር፣ ትንሽ ደግሞ በራሴ አይቻለሁ። የመጀመሪያ ልጄን ልኬ አይቼዋለሁ፤ መልሼዋለሁ። በትንሹ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገር ውስጥ መጨረስ አለባቸው።

ኹለተኛው አገርን ይረሳሉ። የኔ ልጆች አገርን ዕወቅ ፕሮግራም ነበራቸው። አሁን ትንሽ የጸጥታ ችግር ስለሆነ ነው ያቆሙት። አንድ ክረምት ጎጃም፣ ጎንደር ሔደዋል፤ አይተዋል። ማንም የሚቀበላቸው የለም። እናታቸው ናት ይዛቸው የምትሔደው። በራሳቸው ሆቴል ይይዛሉ፣ ታክሲ ይዘው ይንቀሳቀሳሉ፤ ይመጣሉ፣ ይሔዳሉ፣ ያያሉ። ደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢም ብዙ አይተዋል፤ ሐዋሳም ሌሎችንም። ለመዝናኛ አይደለም፤ ማወቅ ስላለባቸው ነው። ትግራይ ሔደዋል፤ በደንብም አይተውታል። አሁን መጨረሻ ጅግጅጋ ሊሔዱ ሲሉ ነው የጸጥታ ችግር የተፈጠረው።

ይሄ ለምንድነው፤ አገር ውስጥ ስለኖርሽ ብቻ አገርን አታውቂም። እዚህ ሆኖ ሰዉ በጣም ያወቀው ስለአሜሪካ ነው። ይሄ ጥሩ ነው፤ ስለአሜሪካም ስለጃፓንም ማወቅ አለብን። ከሁሉ በፊት ግን አገራችንን ማወቅ አለብን። እኔ ደግሞ በጣም አምንበታለሁ። መጽሐፌን አይተሸ ከሆነ ስለእኔ ከሚገልጸው በላይ ስለ አገሪቱ ይገልጻል። ስለዚህ አገርን ሕዝብን እንደማወቅ ትልቅ ነገር የለም።

ለእኔ ‹የእዚህ አካባቢ ሕዝብ እንዲህ ሆኗል› ሲሉ አይገባኝም፤ ምክንያቱም እኔ የማውቀው ሕዝብ ሌላ ስለሆነ ነው። ፖለቲከኛው ሊያብድ ይችላል፤ ሕዝብ ግን ሕዝብ ነው። የእኔም ልጆች እንደዛው ናቸው። ኦሮሚያ ገጠሮች ይሔዳሉ ማንም ዘመድ በሌለበት ሦስት አራት ቀን ያድራሉ። ወደ ወለጋና ጅማም ሔደዋል፣ ሌሎች ቦታዎች እንደዛው።

እና ያ ውጪ የሚባል ነገር አገራቸውን፣ ሕዝባቸውን እንዳያውቁ ያደርጋቸዋል። ባዕድ ይሆናሉ። ኢትዮጵያውያን ሆነው ግን ባዕድ እንዳይሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል። በዋናነት እነዚህ ኹለት ነገሮች መሠረታዊ ናቸው ብዬ ስለማምን ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ጨርሰው በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው መወሰን ከቻሉ ወደ ፈለጉበት አገር መሔድ ይችላሉ። ግን በእኔ እምነት ተምረው ይመለሳሉ እንጂ ቢሔዱም እዛ ይኖራሉ ብዬ አልገምትም።

ስለ ዩኒቨርስቲ ካነሳን፣ እንደ አባትም እንደዜጋም ይሰጋሉ ብዬ አስባለሁ። መጽሐፍዎ ላይ እንደጠቀሱት ገጠሩን ከተማውንም በደንብ ያውቁታልና፤ ስለዚህስ ምን ያስባሉ?
እውነት ነው ያሳስባል። እኔ እንዴት ነው የማየው፤ አንድ ዩኒቨርሲቲ ካምፓስ ውስጥ ያለ ተማሪ እንደ አንድ ቤተሰብ ነው ብዬ ነው የምወስደው። ቤተሰብ ከየትም ይምጣ፤ ከሱማሌ ይምጣ ከትግራይ፣ የቋንቋ መነሻው የፈለገው ይሁን፣ ግን አንድ ካምፓስ ውስጥ ከገባ በኋላ አንድ ቤተሰብ ሆኗል። እዛ እህቱም፣ ወንድሙም፣ ጓደኛውም፣ ሲታመም የሚደርስለት፣ የሚተጋገዝ፣ አንዱ ጠንከር ሲል የሚያስጠና ሌላው የሚያጠና ቤተሰብ ናቸው ብዬ አምናለሁ። ይሄ ቤተሰብ ለምን ይጋጫል? አንድ ቤተሰብ ከሆነ ምንድን ነው የሚያጋጨው? ምክንያቱም እዛ ከትንሿ ኢትዮጵያም በላይ ቤተሰብ ሆኖ ነው። ይህን ቤተሰብ ምንድን ነው የሚያጋጨው ብዬ ሳስብ ከግራና ከቀኝ ይህን የተማረ ትውልድ ለመበከል የሚፈልጉ የሚጫወቱት ጨዋታ ነው።

ማንም ቤተሰብ ሔደህ እዛ ተጣላ ብሎ ልጁን ዩኒቨርሲቲ አይልክም። ማንም ልጅ ሊጣላ አይሔድም። ማንም ልጅ እንደዛ አይደለም። በአንድ በኩል ልጆቹ ጊዜ አላቸው ለፖለቲካው። ጊዜ አላቸው ማለት፣ የመጀመሪያ ተልዕኮአቸው ትምህርት ማጠናቀቀቅ ነው። ከዛ በኋላ ወደ ፈለጉት የፈለጉትን ዓይነት ፖለቲከኛ መሆን ይችላሉ። ለፈለጉትና ያገባናል፣ ለመብቱ መከራከር አለብን ላሉት የብሔር መብት ሊሆን ይችላል፣ ለጾታ መብት ሊሆን ይችላል ወይም ለሙያ መብት መከበር ሊሆን ይችላል፤ መከራከር ይችላሉ። ስለዚህም ተማሪዎቹም ራሳቸውን ከዚህ ነጻ ማድረግ።

ኹለተኛ ደግሞ በጋራ ሆኖ መተጋገዛ፣ ችግር ሲያጋጥማቸው ቁጭ ብሎ ‹ይሄ ጉዳይ እኛን ይመለከተናል› ብሎ በጋራ መወያየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ተማሪ ሞተ ሲባል ተማሪ ተማሪን ገደለ ብዬ ለማመን እቸገራለሁ። ምን መሣሪያ ይዞ ገብቶ ነው ተማሪ ተማሪን የሚገድለው? ምንስ አስቦ ነው ተማሪ ተማሪን የሚገድለው? ለዛ መነሻ የሚሆነው ሌሎች ነገሮች አሉና እነዛን መንግሥትም ቤተሰብ ራሱ ተማሪው መፍትሔ ማድረግ አለበት።

እኔ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ሠርቻለሁ። ጅማ፤ ወለጋ፤ አንቦ ዩኒቨርሲቲዎች የቦርድ ሰብሳቢ ነበርኩ። በቅርበት ተማሪዎችን ሳያቸው ሁሉም ጉጉት አለው፤ አንድ ነገር ላይ፣ የሆነ ቦታ ላይ ለመድረስ። ሁሉም ከደሃ ቤተሰብ የወጣ፣ መከራቸውን አይተው ያስተማሩዋቸው ናቸው። እና ሁሉም የሆነ ርዕይ አለው፤ የሆነ ቦታ ደርሼ እናቴን ረድቼ፣ አባቴን ረድቼ፣ ቤተሰቤን ረድቼ፣ እኔም እንደዚህ ዓይነት ሰው ሆኜ የሚል። ሁሉም የራሱ ፍላጎትና ጉጉት አለው።

ያ ጉጉት እንዲደናቀፍበት የሚፈልግ የለም። ግን የወጣትነት ዕድሜ በራሱ የራሱ ችግር አለውና ትናንሽ ነገሮች ያሳስባሉ። ከሁሉ በፊት ተማሪው እራሱ ይመለከተኛል ብሎ ማሰብ ነው። ለሁሉም ጊዜ አለኝ፣ በምፈልገው የትምህርት መስክ ትምህርቴን ጨርሼ፣ የራሴን አስተዋጽኦ ያገባኛል፤ ልሳተፍበት ይገባኛል ብዬ የማምንበትን ማድረግም አለብኝ ማለት ያለበት ይመስለኛል።

የኔ ሦስተኛ ልጅ የህግ ተማሪ ናት ሁሌም ጊዜ አነሰኝ ነው የምትለኝ። ጥናት፣ አሳይመንት ይሰጣትና ስትጨነቅ ነው የማያት። እኔም በሷ ተጨናንቄ አላውቅም፤ ዶርም ነው ስታጠና የምታድረው። ስለዚህ ተማሪው ጊዜ የለውም፤ ጊዜ ያለው ነው የሚበጠብጠው። ቤተሰብም ከሁሉ በላይ ደግሞ ራሳቸው ወጣቶች ወደፊት ጊዜ አለን፣ የራሳችን የሆነ ጊዜ፤ አሁን ግን ዋናው ተልዕኮችን ይሄ ነው ብለው መሔድ ያለባቸው ይመስለኛል።

እንደው በዚሁ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አስተያየት አልሰጥም ብለዋል። አሁን ያለውን እንዲሁም ያለፈውን ከእርሶ በላይ የሚያውቅ የለም። ለምን ዝምታን መረጡ?
እኔ አሁን ፖለቲካ ውስጥ የለሁም። ፖለቲካ ውስጥ ያሉት አክትቲቭ ፖለቲከኞች የሚሰሩትን ስራ አከብራለሁ፣ እና እዛ ላይ ይሄ ያ እያለኩ መናገር ብዙም አልፈልግም። ነገር ግን በመጽሃፌ ላይ ማለት ያለብኝን ያህል ብያለው፣ ሰው አንብቦ መረዳት የሚችለውን ያህል ይወስዳል ብዬ አስባለሁ።

ወደ ዲቦራ ፋውንዴሽን እንምጣ፤ ፋውንዴሽኑ ከተጀመረ በኋላ ምን እየሠራችሁ ነው?
የዲቦራ ፋውንዴሽን ዓላማ ኹለት ነው። አንደኛው ግንዛቤ መፍጠር ነው። የአዕምሮ ዝግመት በአገራችን በስፋት በመኖሩና ህብረተሰቡ ደግሞ እንደ አንድ ቁጣ ስለሚቆጥረው፤ ያ ቁጣ አለመሆኑን አውቆና ተረድቶ፤ ችግሩ ያለባቸውን ወገኖች ከቤት እንዲያወጣቸው፣ እንዲያስተምራቸው፣ የሚረዱበትን ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን እንዲፈጥር መሥራት ነው። ኹለተኛው ደግሞ የአቅም ግንባታ ጉዳይ ነው። በዚህ ላይ የሚሠሩ ሙያተኞችን የማፍራት፣ ዕውቀቱን ወደ አገር ውስጥ የማምጣት ተግባር ነው።

የመጀመሪያውን ዓላማ ከማሳካት አንፃር መጽሐፉ ከታተመ ጊዜ ጀምሮ በጣም ብዙ ኅብረተሰብ ጋር ደርሷል። በመጽሐፍ ቁጥር ብዛት ብቻ ሳይሆን ዜናውን ሚዲያዎችም በጣም ተቀባብለውታል፤ በሚዲያዎቹ ምክንያት በጣም ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይህን ለማየት ችለዋል።

ሁሉም ቤተሰቡ ወይም ጎረቤቱ ጋር እንዲህ ዓይነት ችግሮች አሉ፤ ወይ ደግሞ በማኅበረሰብ ውስጥ እንደነዚህ አይነት ሕጻናት አሉ። እኛ ሥራ ከጀመርን ጀምሮ ስናየው ሰምቶ ይሄ ችግር አለን የሚለው፣ የሚደውለውና ወደዚህ የሚመጣው ብዙ ነው። ስለዚህ የዲቦራ ፋውንዴሽን ግንዛቤን ከመፍጠርና የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳልሆነ ከማሳወቅ በዘለለ ሁኔታው ሲፈጠር ተቀብሎ የሚደረገውን ድጋፍ አድርጎ ሕጻናቱ የሚቀጥሉበትን ሁኔታና እንደ ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ራሳቸውን ችለው የሚኖሩበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚቻል ማሳወቅ ነው። ከዚህ አኳያ ጥሩ ርቀት ሄዷል ብዬ እገምታለሁ።

በዚህ አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የአዕምሮ ዝግመት ላይ ከሚሠሩ ማኅበራት ጋር ግንኙነት ጀምረናል። ለምሳሌ እንግሊዝ እና አሜሪካን ማንሳት ይቻላል፣ ከአፍሪካ አገራትም ይህን ጉዳይ በቅርብ ከሚከታተሉና ከሚረዱት ጋር ግንኙነት አለን። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ዕውቀቱ ስለሚያስፈልገን እና እነዚህ አካላት እንድናገኘው ስለሚረዱን ነው።

ኹለተኛው የአቅም ግንባታ ዓላማችንን አስመልክቶ ሰዎች እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸው ሕጻናትን የሚደብቁት አንደኛ ከእውቀት ማነስ ነው። ቤተሰብ ሥልጠና ስለማያገኝ ችግሩን የእግዚአብሔር ቁጣ አድርገው ከመውሰድ በተጨማሪ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም። ትምህርት ቤቶች እንደዚህ ዓይነት ሕጻናት እንዲቀበሉ ከመደበኛው ተማሪ ውጪ የሚደግፉበት ትምህርት የላቸውም። እድገታቸውን የሚከታተል ሐኪምም የለም፣ ነገር ግን ከጸባያቸው ጋር የተያያዙትን ነገሮች የሚከታተሉበት አግባብ መኖር አለበት።

ቀጣይነት ያለው ስርዓትም ያስፈልጋቸዋል። የማያቋርጥ የንግግር ህክምና (Speech Therapy) ከንግግር ጋር የተያያዘውን ችግር እንዲፈቱ ያስችላቸዋል። በመጀመሪያውም እንደ አንድ ንዑስ የትምህርት ጥናት ክፍል (Subspecialty) የህክምና ትምህርት ውስጥ የለም። ሌሎች አገራት የባህሪ ዕድገት ጥናትን (Behavioral Development) እንደ አንድ የህክምና ጥናት አካል አድርገው ይወስዱታል።

ኹለተኛው ትምህርት ቤቶች ይህን ዓይነት ችግር ላለባቸው ሕጻናት ደጋፊ መምህራን (Supportive Teachers) መመደብ ቢያስፈልጋቸውም እኛ አገር እንዲህ ያለው ነገርም የለም። ዝም ብለው ከሥነ-አዕምሮ ትምህርት ቤት የወጡ ተማሪዎችን እንዲረዷቸው ያደርጋሉ። ሥነ-አዕምሮ አጠቃላይ ዕውቀት ከመስጠት ውጪ የልጆቹን ችግር በቀጥታ ቀርቦ አይዳስስም። በተጨባጭ እዚህ ላይ ያለው እውቀት ምንድን ነው ብሎ እሱን መለየትና ማስተማር ያስፈልጋል።

ሦስተኛ የቴራፒ ነገር ያስፈልጋል። እዚህ የተለመደው ቴራፒ ወገብ ሲሰበር፣ እግር ሲሰበር ወይም ደግሞ ከፍ ያሉ ነገሮች ሲከሰቱ እንጂ ከእነዚህ ሕጻናት ጋር በተያያዘ አይደለም። ስለዚህ አሁን ይህንን ለመሥራት የሚያስችል የትምህርት ስርዓት እያሠራን ነው። ዕውቀቱ ያላቸው ጋር ግንኙነት አድርገናል። ምንአልባትም በአጭር ጊዜ እዚሁ ተቀምጠው፤ ለአንድና ለኹለት ዓመት በቀጣይነት ሥልጠና የሚሰጡ፤ በዚህ ላይ ዕውቀት ያላቸው የውጭ ዜጎች እናገኛለን። ስለዚህ የዐቅም ግንባታውን ሥራ ቢበዛ በኹለት ወይ በሦስት ወር ውሰጥ እንጀምራለን ማለት ነው። ይሄ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው።

የዲቦራ ፋውንዴሽን ሕጻናትን መሰብሰብ ዓላማው አይደለም፤ ሕጻናትን መሰብሰብም የለበትም። መሰብሰብም በራሱ ስህተት ነው። ሕጻናቶቹ ከሌሎች ተማሪዎች መለየት የለባቸውም። ነገር ግን እዛው ውስጥ ድጋፍ ማግኘት አለባቸው። እድገታቸውንና ባህሪያቸውንም መከታተል ያስፈልጋል። ትምህርት ላይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ድጋፍ ሲባል እንዴት እንደሚጽፉ መደገፍ ማለት ሳይሆን ፍላጎታቸውን መለየት ማለት ነው።

አንድ ነገር በዝርዝር ይማራሉ፣ ያውቃሉ። ያችን የሚያውቋትንና ሊያውቋት የፈለጓትን ነገር ምን እንደሆነች አውቆ እዛ ላይ ማዳበር ነው። አንዳንዶቹ የሒሳብ ሰዎች ይሆናሉ። አንዳንዶቹ አትሌት፤ አንዳንዶቹ ሙዚቀኛ መሆን ይችላሉ። ግን አንድ ነገር ነው፤ የተለየ ብቃት የሚያሳዩበት። ያን ፍላጎታቸውን ለይቶ እዛ ላይ ሥልጠና መስጠትና እዛ ላይ ማጠናከርን የሚመለከት ጉዳይ ነው፤ ድጋፍ።

ቤተሰብ ጠዋት ቀርስ፣ ማታ እራት አብልቶ የሚያኖር ቢሆንም ቀኑን ሙሉ አብሮ ስለማይውል ሊለይ አይችልም። ሙሉ ቀን አብሮ የሚውል/የምትውል ያስፈልጋል ማለት ነው። ይህን ለማድረግ የሚመለመሉ ሰዎችም ባህሪ ወሳኝ ነው። እነዚህ ሕጻናት በባህሪያቸው ፍቅርን ይወዳሉ። ዲቦራ እንደዛ ነች፤ ሁሉም እንደዛ ናቸው። በሚገኙበት ማዕከል ሔዳችሁ ብታዩዋቸው ሕጻናቶቹ ፍቅር ናቸው። ከሰው ጋር መጫወት፣ አቅፎ መሳም፣ ሰላም ማለት፣ መጠጋት ይፈልጋሉ።

የሚመለመሉት ደጋፊ መምህራን ወይም የዕድገት ሃኪሞች ሥራ ፈላጊዎች መሆን የለባቸውም። ሥራ ፈልገው ከገቡ ጉዳት ነው። ሥራ ለመፈለግ ሳይሆን ትዕግስት ኖሯቸው፤ ‹ይሄን መለወጥ አለብኝ› የሚል ፍላጎት አድሮባቸው ከገቡ ብቻ ነው ውጤታማ መሆን የሚችሉት። ኃላፊነታቸው ትዕግስት ይፈልጋል፤ አብሮ መጫወት ይፈልጋል፣ አብሮ መቆየት ይፈልጋል። ለምሳሌ ዲቦራ በነበረችበት ትምህርት ቤት ደጋፊዋ ስትቀየር ትምህርት ቤት ሁሉ አልሔድም ነበር የምትለው። በመሆኑም መቀራረባቸው በጣም ትልቅ ነው።

እንደነዚህ አይነት መቀራረብ ሲኖር ቤተሰብም መቀራረባቸውን መቀበል አለበት። ቤተሰብ መሆን የሚችል ነው የሚያስፈልገው ማለት እንጂ፤ ዝም ብሎ ጠጋ ጠጋ ብሎ የሚሮጥ፣ በየቀኑ ዐስር ብር ጭማሪ ባገኘ ቁጥር ሥራዉን የሚቀይር፤ ለነሱ አይስማማም። ፍላጎት ያላቸው ‹እኔ መደገፍ አለብኝ! መሥራት አለብኝ!› የሚሉትን የመምረጥ ጉዳይ ነው። እስከ አሁን እነዚህ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የመጀመሪያው ‹ዲቦራ› የሚለው መጽሐፍ አንድ ቤተሰብ ላቋቋመውና የኢትዮጵያ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር ለሚባለው ማኅበር ነው የተሰጠው።

‹ዲቦራ› የሚለው የመጀመሪያው መጽሐፍ ምን ያህል ኮፒ ተሸጠ?
‹ዲቦራ› ከዐስር ሺሕ በላይ ኮፒ ይሆናል የተሸጠው፤ ገቢውም ለማህበሩ ነው የተደረገው። የአሁኑ መጽሐፍ ደግሞ የመጀመሪያ ዙር በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ወደ ኻያ ሺሕ ነው የታተመው። የእሱ ገቢ ደግሞ ለዲቦራ ፋውንዴሽን ነው የተሰጠው። በአብዛኛው ስላለቀ እንደገና ልናሳትም ነው።

ከመጀመሪያው መጽሐፍ ሽያጭ በተገኘው ገንዘብ የዲቦራ ፋውንዴሽን ቦርድ ወስኖ፣ ለማኅበሩ [የቆየ ማህበር ነው፣ ቢያንስ 26 ዓመት የቆየ ነው] ሕጻናት የሚመላለሱባቸው ኹለት የተማሪዎች ማመላለሻ መለስተኛ አውቶቡሶችን ገዝቶ ሰጥቷል። ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት አገልግሎትና ድጋፍ የሌላቸው ቢሆንም ከአስራ አምስት/ኻያ ቀን በፊት ይፋዊ በሆነ መንገድ ሥራ ጀምረዋል።

ስለዚህ ቅድም እንዳልኩት ዓላማው ሕጻናት መሰብሰብ አይደለም፤ አቅም መፍጠር ነው። ሥራችን ባገኘነው አቅም ሌሎችን መደገፍ እና እነዛን ድጋፎች ይዞ ሌላው ሕዝብ በስፋት እንዲሠራ ማስቻል ነው። ምክንያቱም ችግሩ ያለው አዲስ አበባ ብቻ አይደለም፣ በሁሉም የክልል ከተሞች አለ። እነዚህን ሁሉ ለመደገፍና ለመርዳት ነው ድርጅታችን የተቋቋው፤ በዚህ አግባብም እየሠራ ነው።

ከአዲስ አበባ ውጭ መደገፍ የጀመራችሁበት እና ልትሔዱበት የምታስቡት አካባቢ አለ?
ገና ነው። ዋናው አሁን ትኩረት የምናደርግው አቅም የመፍጠር ሥልጠናውን መጀመር ላይ ነው። ሥልጠናውን ከጳውሎስና ሀያት ሆስፒታል ጋር እንጀምራለን። እንደዚሁ ደግሞ የደጋፊ አስተማሪዎችን ሥልጠና ከግሪክ ስኩል ጋር እንጀምራልን። ስለዚህ የመጀመሪያው ተግባር አቅሙ ራሱን ችሎ እንዲኖር ማድረግ ነው። አቅሙ ከሌለ ድጋፍ የሚባለው ነገር የለም።

ከዚያ በተጨማሪ የቤተሰብ ትስስር መፈጠር አለበት። በአካል የሚገናኘው በአካል እየተገናኘ ‹ያንተ ልጅ…ያንቺ ልጅ እንደዚህ ነው› መባባል መደጋገፍ አለበት። በአካል የማይገናኘው በስልክ፣ ካልሆነ ደግሞ በኢንተርኔት እንዲገናኝ ያስፈልጋል። ብቻ አሁን ይህን ትስስር ጀምረነዋል። የቤተሰብ ትስስር በጣም ይጠቅማል። አንድ እናት የዚህ ዓይነት ችግር ያለው ሕጻን ቤቷ ሲኖር በጣም ትቸገራለች፤ በጣም ትጨነቃለች። ሌላ እናት ስታገኝ ግን ትጽናናለች። ‹እኔ እኮ እንዲህ አድርጌያለው! ልጄን እንደዚህ ነው የምረዳት› የሚለው መነጋገር በራሱ፤ የአንዱን ልምድ ወደ ሌላው ማሳለፍ፤ ተነጋግሮ ‹እኔ እንዲህ አድርጊያለሁ አንቺ እንዲህ አድርጊ› መባባል ይጠቅማል። እናት እያልኩ እያወራሁ ያለሁት አባቶች የሚጨነቁ ቢሆንም ትልቁ ሸክም የእናቶች ስለሆነ ነው። ስለዚህ የትስስሩን ሥራ ጀምረነዋል።

ሌላው ነገር ደግሞ አባላት ይኖሩናል። አባል ማለት በዋነኛነት መዋጮ የሚያዋጣ ወይም የሆነ ነገር የሚያደርግ ማለት አይደለም። አባል እንዲህ እናድርግ ሲባል ያለውን ሊያዋጣ ይችላል። ከሁሉ በላይ ግን የአባል ሚና መረጃ ማድረስ ነው። ለምሳሌ በሚኖርበት ቀበሌ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ሕጻን ሲኖር ዝም ብሎ የሚያልፍ ሳይሆን ‹ይህ እኮ እንዲህ መፍትሔ አለው› ብሎ ሌላውን መደገፍ፣ መርዳት፣ መናገር፣ ማስተላለፍ ነው። ስለዚህ የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የአባላት ጥምረት ይኖራል ማለት ነው።

ጥምረቱ ድረ ገጽ አድራሻ (ኢ-ሜይል) ይኖረዋል። አባላት በጉዳዩ ዙሪያ እየተገኙ አዳዲስ መረጃዎችን፣ ዕውቀትንና ጥናቶችን በማሰራጨት መረዳዳት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ጠቃሚ ናቸው። የበጎነት ተግባር ስለሆነ፣ በጎነት ያሳድጋል፣ ይረዳል ዝም ብሎ አያልፍም ያጠናክራል።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ዕውቀቱ ካላቸው፣ በሥራው ላይ ከቆዩ ይሄን ጉዳይ እየፈቱ ከመጡ አካላት ጋርም እንሠራለን። ችግሩ በእኛ [አገር] ግምትም አልተሰጠውም፤ ነገር ግን ሌላው ጋር ሳይንቲስት የሆኑ አሉ። መንግሥታትም ግምት ይሰጡታል፤ ስለዚህ በዛ ደረጃ አንዲታይ እንጥራለን። በተጨማሪ ዜጎች ናቸውና የዜግነት መብቱ ሊኖራቸው ይገባል። ትምህርት ቤቶች ሊቀበሏቸው እንዲሁም የህክምና አገልግሎት ሊኖራቸው ይገባል። ሌሎች የዜግነት መብቶችም አብሮ መኖር አለባቸው ማለት ነው።

ዲቦራ ሥራውን እንድታይ ወደዚህ ፋውንዴሽን ያመጥዋታል? ምንስ ትላለች?
ዲቦራ ትምህርት ሳይኖራት ትመጣለች። የምትውለው ትምህርት ቤት ስለሆነ ትምህርት የሌላት ጊዜ መጥታ ክዋኔዎች ላይ ትገኛለች። አሁን ከስድስት ወር በፊት በሂልተን ሆቴል መጽሐፉ ሲመረቅ ንግግር አድርጋ ነበር። አሁን ዐስር ዓመትዋ ነው፤ ያኔ ዘጠኝ ዓመት ከስድስት ወር አካባቢ ነበረች። ንግግር ካላደረኩ ብላ ንግግር አድርጋ ታዳሚውን አመሰገነች። በቅርቡም የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ንግግር ማድረግ አለብኝ ብላ ለመጣው ሰው ምስጋናዋን አቅርባ ነበር። ለማህበሩ መኪናው ሲሰጥም እዛው ነበረች። መናገር ትፈልጋለች፣ ማመስገን ትወዳለች፤ እና ትመጣለች።

እሷም ተሳታፎ አላት ማለት ነው?
አዎ፤ መበረታታት ይፈልጋሉ። እንደ እነዚህ ዓይነት ሕጻናት ባበረታታሻቸው ቁጥር አቅማቸው ይጨምራል።
እንደው በአጠቃላይ እንደ ማኅበረሰብ አካላዊ እና አዕምሮአዊ ንቃተ ሕሊና ላይ ያለንን አስተሳሰብ እና መረዳት እርስዎ በግልዎ እንዴት ያዩታል?
እኔ ብዙ ይቀረናል ብዬ አምናለሁ። አፈጣጠራችን ለእንቅስቃሴ እንጂ እንድንተኛ ዓይነት አይደለም። ኹለት እግር ሰጥቶ ኹለቱን እግር መረማመጃ አድርጎ ነው የፈጠረን። ሰው ራሱን ሲያይ ወይም ቆሞ ሲታይ ለእንቅስቃሴ የተፈጠረ ነው። አገራችን ውስጥ ተሽከርካሪ ባልበዛበትና ሁሉም ሰው በእግሩ በሚንቀሳቀስበት፤ ለምሳሌ በገጠር የስኳር በሽታ የሚባለው ነገር ብዙም አይታይም፤ የካንሰር በሽታ ወይም ኮሌስትሮል የሚባለውም እንደዛው።

እኔ በተወለድኩበት አርሲ ጭላሎ አካባቢ ወንድሞቼ፣ አባቶቼ አጎቶቼ አንድ መቶ ዐስር እና አንድ መቶ ኻያ ዓመት በፊት የሞተ የለም፤ ታሞ የሞተ ብዙም አላጋጠመኝም። በቅሎና ፈረስ እንደጋለቡ፣ የቀን ሥራቸውን እንደሠሩ ነው መጨረሻቸው የሚሆነው። የዚህ ውጤት መነሻ ተፈጥሮና ኑሮ በራሱ ያንቀሳቅሳቸው ስለነበር ነው። አሁን ዕድገት ነውና እየተለወጠ ነው ያለው። ሁላችን ከቤት ወደ ተሸከርካሪ፣ ከተሽከርካሪ ወደ ቢሮ መቀመጥ ነው የምንሸጋገረው። ይሄ ሲኖር አመጋገብና እንቅስቃሴ ካልተጨመረበት ሃኪም ቤት ስናጣብብ እንኖራለን ማለት ነው። ስለዚህ ግንዛቤው በጣም ያስፈልጋል።

እኔ ልጆቼን ወደ ማሠልጠኛ ያስገባሁት ለአካል ብቃት ብቻ አይደለም። እኔ ሥራዬን የጀመርኩት በውትድርና ነው። በሙያውም የጄኔራልነት ማዕረግ ደረስኩ። ከዛ በኋላ ነው ወደ ሲቪል ሥራ የመጣሁት። ውትድርና በሰው አዕምሮ ላይ የሚፈጥረው ነገር አለ። ሰዎች በጎ ነገርን ብቻ እያዩ መሔድ የለባቸውም፤ የሕይወትን ሌላኛውን ገጽታን ማወቅ አለባቸው። ሕይወት በጎ ነገር ብቻ የላትም።

ኹለተኛ በውትድርና ማለፍ የአካል ብቃት ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ብቃትንም ይፈጥራል። ስለ አገር፤ ስለ ሕገመንግሥት፤ ስለ ሕዝቦች የሚሰጡ ትምህርቶች የሰው ልጅ ሚዛናዊና ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲኖረው ያደርጋሉ። በውትድርና ማለፍ በሦስተኛ ደረጃ ለችግሮች እንዳይበገር ያደርጋል። በባህሪ ሰዎች ዝም ብለው አይኖሩም፤ ያለ ችግር የሚኖር ማንም የለም። ተመችቶች ችግር ሳይገጥመው ይኖራል የሚባል ሰው የለም። በውትድርና ሲታለፍ ችግሮች ሁሉ ትንሽ ይሆናሉ። የማይታለፍ ነገር እንደሌለ ያሳያል። የአካል ብቃት ተጨማሪ ነገር ነው።

እኔ በየቀኑ ጂም ካልሠራሁ ወይም የእግር እርምጃ ካላደረግሁ አልኖርም። በቀን የግድ መሥራት አለብኝ። በቀን የምሠራበት ኹለት ጉዳይ አለኝ። አንደኛ ሃኪም ቤት መመላለስ አልፈልግም፤ ራሴ የምቆጣጠራቸውና ልቆጣጠራቸው የሚገቡ ብዙ ነገሮች ስላሉ ነው። ኹለተኛው ሙሉ ቀን አቅሜን ተጠቅሜ መሥራት እፈልጋለሁ እንጂ ሥራ ላይ ላንቀላፋ አልፈልግም። ስለዚህ በእነዚህ ኹለት ምክንያቶች አመጋገቤን እከታተላለሁ።

ሰዎች ‹ጊዜ አጠረን› ይላሉ። የሚያጥር ጊዜ የለም፤ ጊዜ ለሁሉም እኩል ነው የተሰጠው። ለአንዱ ሰፍቶ የተሰጠ፣ ለአንዱ አጥሮ የተሰጠ አይደለም ጊዜ። በአንድ ቀን 24 ሰዓት ከሆነ 24 ለሁሉም ተሰጥቷል። 24 ሰዓቱን እንዴት ሊጠቀመው ነው የሚለው ነው ጥያቄው። እኔ ከ24 ሰዓት ውስጥ የአንድ ሰዓት የስፖርት ጊዜ ‹ጊዜ ስለጠበበኝ› ብዬ ብተው ስድስት ወይም ስምንት ሰዓት ውጤታማ ሥራ መሥራት ይኖርብኝ ከነበረው አጎድልና የአራትና የአምስት ሰዓት ሥራ ብቻ ነው የምሠራው። ከዛም ኮሌስትሮል፣ ራስ ምታትና የመሳሰለው ይመጣል። ስለዚህ ጊዜ አጠረኝ፤ ጊዜ አነሰኝ የሚባል ነገር የለም። ሰው ማወቅ ያለበት እንዴት አድርጎ ሕይወቱን ማቀድ እንዳለበት ነው። በመሆኑም በማያቋርጥ መንገድ የዚህ ግንዛቤው ተፈጥሮ ሰው መንቀሳቀስ አለበት ማለት ነው።

ስለ ሳቅዎ ሳልጠይቅ ብሔድ አንባቢዎች ይቀየሙኛል፤ በእርግጥ መጽሐፍዎ ላይ መቼ በደንብ መሳቅ እንደጀመሩ ይናገራል። ግን እንደው በዚህም ትንሽ ነገር ቢነግሩን? ሳቄ ጥሩ ነው? (ትንሽ ሳቅ)
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስለ ሕይወት ያልዎትን አመለካከት በጥቂቱ እንዲያካፍሉን ነው?
ሳቅ የውስጣዊ ደስታ ውጤት ነው። መጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው ትልቅ ከሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው የወጣሁት። ይሄም ራሱ አንድ ነገር ይፈጥራል። ከዛ በኋላም የሚያጋጥሙ ነገሮች ስለነበሩ ሕይወት ምን ልትሆን እንደምትችል እየገባኝ የመጣው ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ዘመን ነው። መጽሐፉ ላይ አይተሽ ከሆነ አንድ ነገር አስቀምጫለሁ፤ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ልደት (ስንተኛ ዓመት አንደሆነ አላስታውስም) ሐምሌ 16 ስናከብር፣ ያን ጊዜ የትምህርት ቤታችን ዳይሬክተር ስለ እርሳቸው ብዙ ነገር ተናገሩ። በጣም ደጉ ንጉሣችን አሉ።

መስከረም 18 ትምህርት ቤት ሲከፈት በ1966 ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከሥልጣን ወርደው ነበርና፤ ደርግ እያለ ያው አስተማሪ ነው ‹ሌባው ንጉሣችን› ያለው። እና ሥልጣንን ባላውቀውም ከጊዜ ጋር ሁሉ ነገር የሚሔድ መሆኑ ነበር የገባኝ። ሥልጣንን አላውቀውም ሕጻን ነኝ፣ የገጠር ልጅ ነኝ።

ከዛም በኋላ ሌሎች በቤተሰብም ሆነ በሌላ መንገድ የሚያጋጥሙኝ ችግሮች ነበሩ። ትንሽ ከፍ ስል ደስታን ከውስጤ መፈለግ ጀመርኩ። ከውጭ መፈለግን አላምንመበትም፤ ሲጋራ አላጨስኩም፣ ጫት አልቃምኩም። እንደ ማንኛውም ገጠር እንዳደገ ልጅ ለወባ መከላከያ አረቄ እንጠጣ ነበር። ግን ከዛ በኋላ ባሉ ጊዜያት ደስታን ከውጭ ለማግኘት ብዬ ያደረኳቸው ብዙ ነገሮች የሉኝም። ውስጥ ሲደሰት ብቻ ነው ደስታ የሚፈጠረው።

ውስጥ መደሰት የሚችለው ደግሞ የምትሔጅበትን መንገድ በደንብ ስትረጂ ብቻ ነው፤ የት መድረስ እንደምትፈልጊና አምነሽ ‹እኔ እዚህ መድረስ አለብኝ› ስትይ። እና ያ የጦርነት ተራራ በሙሉ ምንም አስከፍቶኝ አያውቅም። ጦርነት ላይ ቁጭ ብዬም እስቅ ነበር። የኔ ምርጫ ነው፤ መረጥኩትና ገባሁ። ስለዚህም አንድ ቀን አንድ ቦታ እደርሳለሁ፤ እኔ ባልደርስ፣ እኔ ብሰዋም እንኳን ከኔ የሚከተሉት ይደርሳሉ ብዬ አምን ነበር።

እናም በአስቸጋሪ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ እንኳን መፍትሔ መፈለግ እንጂ ያን ያህል ጭንቅ አልነበረኝም። ይህም ቀስ እያለ ነው ባህሌ የሆነው። ብዙዎች ይገርማቸዋል። አብረን የነበርን የፓርላማ አባላት መጽሐፉ ከወጣና ይሄ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ ቀርበው የነገሩኝ ብዙዎች አሉ። ‹የዲቦራ ይሄ ሁሉ ችግር እያለብህ ነበር እንደዛ እየሳቅህ የምትሠራው› ይሉኛል። ባዝን ምን ላመጣላት ነው? ባዝን እኮ ምንም አላመጣላትም፤ ምናልባትም ውስጤን ጎድቼ እሷንም የማልረዳ ሰው ነው የምሆነው።
ችግር ይመጣል፤ ይታለፋል። ችግር የሌለበት ሕይወት አንዳንዴ መጥፎ ነው። ችግር ወደ ፊት እንድትራመጂ ያደርጋል። እኔ ሕይወቴ በሙሉ ሳቅ ነው። ቤቴ ብትመጪም ልጆቼ በሙሉ የሳቅ ልጆች ናቸው። በተለይ አርብ ከሰባት እስከ ስምንት ሰዓት ድረስ ቤት ውስጥ እንቆያለን። ዐስር እና ከዐስር ዓመት በታች አምስት ልጆች አሉኝ፤ እንደገና ትላልቆች አሉ።

የሚያሳድጓቸው ናቸው?
ልጆቼና የልጅ ልጆቼ ናቸው። የሌሎች ወንደሞቼና የእህቴ ልጆች ስላሉ ሁሉም ይመጡና እንስቃለን። ምንም እኮ የሚያጨናንቅ ነገር የለም። ጥለሽ የምትሔጂው ዓለም ነው። መጠንቀቅ የሚያስፈልገው ሳቁ ሥራሽን የሚያስረሳሽ እንዳይሆን ነው። ሳቁ ከዓላማሽ የሚመልስሽ እንዳይሆን፣ የሳቁ ምንጭ ቡና ቤት እንዳይሆን፣ የሳቁ ምንጭ ጫት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። እሱ ሳቅ ሳይሆን ማጥፋት ነው። ስለዚህ እኔ ሥራዬን ለቅሜ ነው የምሠራው። በጣም ለቅሜ። በጦርነት ውስጥም ሆነ በሰላም የተቀጣሁበት ጊዜ የለም። ከጓደኞቼ ጋር በጣም ጥሩ የሆነ ማኅበራዊ ግንኙነት አለኝ። በአካባቢዬ ያሉ ሰዎችን በሙሉ አውቃቸዋለሁም።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here