የቡና እና ቅመማ ቅመም የወጪ ንግድ የ25 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳየ

0
1202

ኢትዮጵያ በ2012 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ አራት ወራት ወደ 10 ዋና ዋና የቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ተቀባይ አገራት 103 ሺሕ ቶን ምርቷን በመላክ 288 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘች ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ሲነጻጸር የ35 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱ ታወቀ።

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ውስጥ ከተላከው አጠቃላይ ምርት ጀርመን በመጠን 24 ሺሕ ቶን እና በገቢ 57 ሚሊዮን ዶላር በመቀበል ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። ሳውዲ አረቢያ 16 ሺሕ ቶን ምርት በ44 ሚሊዮን ብር በኹለተኛ ደረጃ ላይ ያለችው ጃፓን 12 ሺሕ ቶን ምርት በ32 ሚሊዮን ዶላር ገዝታለች።

የተቀሩት በ2012 በገቢ ቅደም ተከተል ቤልጅየም፣ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጣሊያን፣ ሱዳን፣ ፈረንሣይ እና ታይዋን ከአራት እስከ ዐስር ያለውን ደረጃ በመያዝ፤ በጠቅላላው ዐስሩ አገራት የኢትዮጵያን ቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም በመጠን 85 በመቶ እና በገቢ 83 ከመቶ የያዙ ሆነው ተመዝግበዋል። የእነዚህ ዋና 10 መዳረሻ አገራት ከ2011 አፈፃፀም ጋር ሲወዳደር በመጠን 34 በመቶ እናበ ገቢ 15 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል።

የቡና የወጪ ንግድ 105 ሺሕ ቶን በመሆን ከፍተኛውን መጠን የያዘ ሲሆን፣ ከሐምሌ 2011 እስከ ጥቅምት 2012 ከውጭ ንግዱ 284 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። የተላከው ቡና በመጠን የእቅዱ 104 በመቶ እንዲሁም በገቢ የእቅዱ 84 በመቶ መሆኑን ባለሥልጣኑ ለአዲስ ማለዳ የላከው ሪፖርት ያስረዳል። በ 2011 የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅትም 77 ሺሕ ቶን ቡና ተልኮ 257 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቶ የነበረ ሲሆን፣ ከዘንድሮው ገቢ ጋር ሲነጻጸር በመጠን 31 በመቶ እንዲሁም በገቢ 10 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል።

በ2012 በጀት ዓመት አራት ወራት የተላከዉ ቡና፣ በቡና ዓይነትና በመጠን ሲታይም የሲዳማ 30 በመቶ፣ የነቀምቴ 26 በመቶ እና የጅማ 20 በመቶ በማስመዝገብ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘዋል።

‹‹ከቡና የሚገኘው ገቢ የቀነሰበት ዋነኛው ምክንያት የቡና ዓለማቀፍ ዋጋ ካለፉት 13 ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ማሽቆልቆሉ ነው›› ሲሉ የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ስንታየሁ ግርማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ይህ የዋጋ ቅናሽ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ይህንንም ለመቋቋም የሚላከውን ምርት መጠን የመጨመር፣ የዓለም ዐቀፍ ቡና ክዋኔ እና የባለልዩ ጣዕም የቡና ቅምሻ ውድድርን ማዘጋጀት እንደመፍተሔ ተቀምጧል›› ብለዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ቻይና እና ሩሲያ ካሉ አገራት ጋር የገበያ ትስስርን ለመፍጠር እንዲሁም ከዓለም ዐቀፍ የቡና ድርጅት (ICO) እና ከሌሎች ቡና አምራች አገራት ጋር በጋራ እየሠራች መሆኑ ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here