በሶስት ወራት ከ 62 ሺህ በላይ ሕገወጥ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

0
524

ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ለወንጀል መፈጸሚያነት ለማዋል የታሰቡ ልዩ ልዩ ጠመንጃዎች ፤ ጥይቶች ፤ ሽጉጦች ፤ ቦንቦች እንዲሁም የቡድን መሳሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡

ከተያዙት የጦር መሳሪያዎችም ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው የጥይት ብዛት ሲሆን 52 ሺህ እንድ መቶ 29 ልዩ ልዩ ጥይቶችን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን የፌደራል ፖሊስ ለአዲስ ማለዳ የላከው ሪፖርት ያሳያል፡፡ በተጨማሪም 74 ልዩ ልዩ ጠመንጃ፣ 115 ልዩ ልዩ የተለያየ ሃገር ስሪት የሆኑ ሽጉጦች እና አንድ ቦንብ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ከቡድን መሳሪያዎች ውስጥም 1570 የብሬን ጥይትና 8484 ኤም 14 ጥይቶች መያዛቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡

የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ የጠናቀረው አጠቃላይ የጦር መሳሪያ ቁጥርም በጠቅላላ 62 ሺህ 373 ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
ባለፈው ዓመት ኅዳር 10/ 2011 በጀት ዓመት ሦስት ወራት ውስጥ ፌደራል ፖሊስ 2 ሺሕ 516 የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ መያዙን ገልጾ ነበር። በወቅቱ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሕገ ወጥ መሣሪያ ዝውውሩ ለንጹሐን ዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ በየአካባቢው ለሚከሰቱ የማኅበረሰብ ግጭቶች ማባባሻ፣ በተለያዩ ቦታዎች ለሚፈጸሙ ዘረፋዎች፣ ስርቆቶች፣ ለሕገ ወጥ ንግድ ኮንትሮባንድ ማስፈጸሚያ መሆኑን አሳውቆም ነበር፡፡

የሩብ አመቱ አፈጻጸም ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የብሬን ጥይትና ኤም 14 የተሰኙ ጥይቶች የቡድን መሳሪያዎች በብዛት መገኘታቸውን መረጃው ያሳያል፡፡
በአገር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተ የሰላም እጦት ምክንያት የጦር መሳሪያ ስርጭት ሊጨምር መቻሉን የፌደራል ፖሊስ ኮምሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዲ ገልጸዋል፡፡ የነፍስ ወከፍ ብቻ ሳይሆን የቡድን መሳሪያዎች ጥይቶች የተያዙበት ሁኔታ ለጦርነት የተዘጋጀ ኃይል ያለ ያስመስለዋል፤አገሪቱ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ያልተረጋጋ መሆኑ እንደአባባሽ ምክንያት ሆኖም ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

በየዕለቱ ከሚወጡት ዘገባዎች አንጻር በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ እንቅስቃሴ እንዳለ አመልካቾች ናቸው። በፀጥታ ኃይሎች የተያዙት የጦር መሣሪያዎች መጠን ከፍተኛ ቢሆንም፤ ሳይያዙ ወደ ተለያዩ ሰዎች እጅ የገቡት ቁጥር ምን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አለመታወቁ በርካቶችን ሥጋት ላይ ጥሏል።

ኮሚሽኑ ከ2009 እስከ 2011 አንድ ሺ 9 መቶ 17 ልዩ ልዩ ጠመንጃዎች ፣ 196 ሺ 474 ልዩ ልዩ ጥይቶች፣ አምስት ሺ 9 መቶ 54 ልዩ ልዩ ሽጉጦች፣ 117 ቦንቦች፤ እንዲሁም አንድ ብሬን፣ አንድ ኤም 14 እና አንድ ላውንቸር የቡድን መሳሪያዎች እንደተያዙ የፌደራል ፖሊስ የሶስት አመታት ሪፖርት ያመላክታል፡፡

የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ ያለውን ዝቅተኛ የቅጣት እርከን ከፍ በማድረግ ወንጀሉን ለመካለከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል የተባለለት የጦር መሳሪያ ቁጥጥር አዋጅ ዝውውሩን በተወሰነ መጠን ይገታዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መግለጹ ይታወሳል፡፡ አዋጁ የጦር መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን መንገድ፣ የሚሸጡበትን እና የሚዘዋወሩበትን እንዲሁም የሚጠገኑበትን መንገድ ለመጀመሪያ ግዜ የደነገገ ሆኖ መረቀቁንም መግለፁ ይታወሳል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here