ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በእስራኤል እና በፍልስጤም ሃማስ መካከል የተቀሰቀሰውን ከፍተኛ ጦርነት ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱ እየተዘገበ ይገኛል።
በዚህም እስራኤል በጋዛ ያለው ኹኔታ ከመካከለኛው ምስራቅ የሚነሳውን የነዳጅ አቅርቦት ሊያስተጓጉል ይችላል በሚል ስጋት፤ ዛሬ ሰኞ የአንድ በርሜል ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ላይ በ 4 በመቶ ጭማሪ መታየቱ ተነግሯል።
ባለፉት ሳምንታት ወደ 96 ዶላር ደርሶ የነበረው የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ባለፉት ቀናት ጥሩ የሚባል ቅናሽ አሳይቶ የነበረ ሲሆን፤ ነገር ግን ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኃላ የነዳጅ ዋጋ ዛሬ በ4 ነጥብ 53 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ፤ 88 ነጥብ 41 ዶላር መድረሱን ሲኤንቢሲ ዘግቧል።
የአሜሪካን የነዳጅ ዋጋ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው ዌስት ቴክሳስ ኢንትርሚዲየት የተሰኘው ተቋም አንድ በርሜል ነዳጅ በ4 ነጥብ 69 በመቶ ጨምሮ ወደ 88 ነጥብ 67 ዶላር ከፍ ማድረጉም ተነግሯል።
በእስራዔልና በፍልስጤሙ ሃማስ መካከል የሚካሄደው ጦርነት ወደ ሙሉ ውጊያ ከተቀየረ ኹለተኛ ቀኑንያያዘ ሲሆን፤ ጦርነቱ በደቡባዊ እስራዔል ሦስት ሥፍራዎች ተፋፍሞ መቀጠሉ ተገልጿል፡፡
ጦርነቱ እስካሁን ቢያንስ የ1 ሺህ 113 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉየተገለጸም ሲሆን፤ ሕይወታቸውን ካጡት መካከል 413ቱ ፍልስጤማውያን ሲሆኑ፤ 700ዎቹ ደግሞ እስራዔላውያን መሆናቸው ተነግሯል፡፡



