“የዓባይ ግድብ የሲቪል ሥራ በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል” ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

0
174

ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የዓባይ ግድብ የሲቪል ሥራ በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡

የ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተከፍቷል።

የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት በተገኙበት የፌደራል መንግሥቱን ዓመታዊ ዕቅድ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።

በንግግራቸውም ያለፈው ዓመት የዓባይ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት እና ከ90 በመቶ በላይ ግንባታው መጠናቀቁ የተሰማበት ዓመት እንደነበር በማስታወስ፤ በተያዘው ዓመትም የግድቡ የሲቪል ግንባታ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

“ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ የሚያመነጭ ግድብ አይደለም” ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ “የቱሪዝምና የውሃ ሀብት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የሞራል ልዕልና ነው፡፡” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው፤ “ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ አንድነት ብዙ ችግሮችን ተሸጋግራ ሕልውናዋን አስጠብቃለች።” ያሉ ሲሆን፤ “አሁንም ይህንን ታሪክ ለማስጠበቅ ልዩነታችንን በማጥበብ ችግሮቻችንን በጋራ ለመቅረፍ መስራት አለብን” ብለዋል።

“ያሉንን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና መልካ ምድራዊ ሀብቶች ወደ እድገት መለወጥ ይጠበቅብናል” ያሉም ሲሆን፤ “ለሀሳብና ለውይይት ቅድሚያ በመስጠት ሕብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል ይህም የዚህ ትውልድ ሃላፊነት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።ፕሬዝዳንቷ አክለውም፤ ኢትዮጵያ በ2015 በርካታ ፈተናዎችን በማለፍ የሚያኮሩና ይበልጥ ለመስራት የሚያነሳሱ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶችን ማስመዝግቧን ገልጸዋል፡፡

ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በተደረገው እንቅስቃሴ በ2015፤ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች የአገር ውስጥ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፤ ለውጭ አገር የሥራ ስምሪትን ሕጋዊ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህም 102 ሺሕ ዜጎች የውጭ አገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ አክለውም፤ መንግሥት በ2016 የፀጥታ ስጋት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሌብትና ብልሹ አሰራር፣ እንዲሁም ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድን በዘላቂነት የሚያስቀር መፍትሔ በማምጣት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

በመጪው ሦስት ዓመታት ውስጥም 9 ነጥብ 15 ሚለዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ባለፋት ሦስት ዓመታት የተመዘገበው አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በዚህ ዓመት 7 ነጥብ 9 በመቶ እንዲሆን በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም በመግለጽ፤ የመንግስት ገቢ አሰባበሰብን በማሳደግ ከታክስ ገቢ 441 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ከውጭ ሀብት በበጀት ዓመቱ 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለማግኘት መታቀዱን አብራርተዋል፡፡

በምክር ቤቱ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት የኹለቱ ምክር ቤቶች አባላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች፣ የክልል ርእሰ መሥተዳድሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በመከናወን ላይ ይገኛል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here