ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በ2015 የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ 845 ሺሕ 099 ተማሪዎች ውስጥ፤ 817 ሺሕ 838 ተማሪዎች ከ50 በመቶ በታች የሆነ ውጤት ማምጣታቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በዚህም ከአጠቃላይ 845 ሺሕ 099 ተፈታኞች ውስጥ 27 ሺሕ 267 ተማሪዎች ወይንም (ሦስት ነጥብ ኹለት በመቶ ብቻ) 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ውጤት ማምጣታቸውን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታውቀዋል፡፡
ከነዚህም በተፈጥሮ ሳይንስ ከተፈተኑ 356 ሺሕ 878 ተማሪዎች ውስጥ 19 ሺሕ 017 ተማሪዎች 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ውጤት ያመጡ ሲሆን፤ በማህበራዊ ሳይንስ ከተፈተኑ 488 ሺሕ 221 ተማሪዎች ውስጥ 7 ሺሕ 250 ተማሪዎች ብቻ 50 በመቶ እና ከዛ በላይ ውጤት ማምጣታቸው ተነግሯል፡፡
በዚህም በአጠቃላይ ከማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ከ500 በላይ ያስመዘገቡ ተማሪዎች 10 ብቻ ሲሆኑ፤ ከተፈጥሮ ሳይንስ ደግሞ 263 ተማሪዎች ከ600 በላይ ውጤት ማስመዝገባቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም በማታ የተፈተኑ 16 ሺሕ 541 ተማሪዎች ውስጥ ያለፉት 12 ተማሪዎች ብቻ ሲሆኑ፤ በግል የተፈተኑ 169 ሺሕ 502 ተማሪዎች ውስጥ ያለፉ 498 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በመደበኛ ከተፈተኑ 659 ሺሕ 056 ተማሪዎች ውስጥ ያለፉ 26 ሺሕ 757 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም የ12ኛ ክፍል ፈተና ካስፈተኑ 3 ሺሕ 106 ት/ቤቶች ውስጥ 1 ሺሕ 328 ትምህርት ቤቶች ወይንም 42 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት አንድም ተማሪ አለማሳለፋቸው ተነግሯል፡፡
በከተማ ደረጃ አዲስ አበባ፣ ሀረሪ እና ድሬዳዋ የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ ከተሞች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
በዚህም መሰረት 27 ሺሕ 267 ተማሪዎች በያዝነው ዓመት በቀጥታ “ፍሬሽ ማን” ሆነው ወደ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ የተባለ ሲሆን፤ 160 ሺሕ ገደማ ተማሪዎች በሬሜዲያል እንደሚገቡ ተነግሯል፡፡
ከ2014 በትምህርት ዘመኑ ለፈተና ከተቀመጡ 896 ሺሕ 520 ተማሪዎች፣ ወደ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት ወይም ከ50 በመቶ በላይ ያስመዘገቡት 29 ሺሕ 909 እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፤ የዘንድሮ ውጤት በ0.01 በመቶ ከአምናው ዝቅ ማለቱ ተስተውሏል፡፡



