የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የአዋሽ-ወልዲያ-ሀራ ገበያ ለተዘረጋው የባቡር ሃዲድ የኀይል ማቅረቢያ መስመሮች ዝርጋታ ወጪን የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ካልሸፈነ በራሱ ወጪ ኀይል እንደማያቀርብ አስታወቀ።
የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የአዋሽ-ወልዲያ-ሀራ ገበያ 392 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የባቡር መስመር ግንባታ መገባደድ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልገሎት የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታውን እንዲፈፅም በተደጋጋሚ መጠየቁን አገልግሎቱ ገልጿል። በአንጻሩ ግንባታው 40 በመቶ ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በአካል በመገናኘት እንዲሁም ደብዳቤዎችን በመለዋወጥ የገንዘብ ምንጭ እንዲፈልጉ አሳስበናል ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።
ከ2009 ጀምሮ የኀይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታውን እንዲሁም የወሰን ማስከበር ሥራውን ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲፈፅም ጥያቄ እንደቀረበለትም አገልግሎቱ አስታውሷል። የተጠየቀው ሥራ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን እንዲሁም የሚዘረጉት የኀይል ማስተላለፊያ መስመሮች ለባቡር መስመሩ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኮርፖሬሽኑ የገንዘብ ምንጩን አረጋግጦ እና በጀት አስመድቦ እንዲመጣ መግለፁን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሞገስ መኮንን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከ 2009 ጀምሮ አጣዳፊ የኀይል አቅርቦት የሚፈልጉ የኢንዱስተሪ፣ አግሮ ኢንዱስትሪ እና የሲስተም ማስፋፊያ ሥራዎች በመንግሥት እና በግል አጋርነት (ppp) እንዲሠሩ በመንግሥት አቅጣጫ መሰጠቱን ሞገስ ያስታውሳሉ።
‹‹የሚደረጉ ድርድሮች እልባት ላይ ባለመድረሳቸው የአጋርነት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሳይደረጉ መቆየታቸውን በመጥቀስ ሌላ ፋይናንስ ምንጭ እንዲያመቻች ለገንዘብ ሚኒስቴር በማሳወቃችን አሁን በራሳችን ወጪ የኀይል አቅርቦቱን የምናከናውንበት ምክንያት የለም›› ሲሉ ኀላፊው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
የኀይል አቅርቦት ግንባታውን ለማከናወን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ እንዲሁም ረዥም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ፣ በግንባታው እና በኀይል አቅረቦቱ መካከል ለሚፈጠረው አለመጣጣምም ኀላፊነቱን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደማይወስድ እንዲሁም ወጪውን የሚሸፍንበት ገንዘብ አቅም እንደሌለውም ተቋሙ ገልጿል።
የኀይል ማስተላለፊያ መስመሮቹ ዲዛይን እና ሌሎች መሰል ሥራዎች በአገልግሎቱ በኩል የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ችግሩ የገንዘብ ምንጭ ማግኘቱ ላይ እንደሆነ ተገልጿል። አዲስ አባባ ከተማ ቀላል ባቡር ግንባታ በተከናወነበት ወቅት አገልግሎቱ በመንግሥት በተሰጠ አቅጣጫ በብድር የኀይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ዘርግቶ እንደነበር የገለፁት ሞገስ፣ ኮርፖሬሽኑ አሁንም ተመሳሳይ አሠራር እንዲተገበር እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
ከውጪ አገር ባንኮች በተገኛ ብድር የተገነባው የባቡር መስመሩ፣ ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የሚሆነውን ወጪ ኮርፖሬሽኑ ግንባታው ሙሉ በሙሉ እስከሚጠናቅቅ ባለው ጊዜ አፈላልጎ ቢያገባድድ ኖሮ ይህ ክፍተት እንደማይፈጠር እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ገንዘብ ተበድሮ እዳ ውስጥ የሚገባበት ምንም አይነት ምክንያት የለም ሲሉ ሞገስ ተናግረዋል።
ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች፣ የባቡር መስመሩ በኃይል እጦት ምክንያት እስከ አሁን ሙከራ ማድረግ እንኳን አልቻለም ያሉ ሲሆን፣ ከፍተኛ የአገር ሀብት የፈሰሰባቸው መሠረተ ልማቶች ለብልሽት እና ለዝርፊያ እየተዳረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ መረጃ ለማግኘት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሥራ ኀላፊዎችን፤ በተለይም ስንታየሁ ወልደሚካኤልን (ዶ/ር) በአካል እና በስልክ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል። በተጨማሪም ግንባታውን ያከናወነውን የያፒ መርከንዚ የኢትዮጵያ ኀላፊ ‹‹የእኛ ሥራ ግንባታ ነው፣ ፕሮጅክቱ የመንግሥት በመሆኑ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት አንችልም›› ሲሉ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012



