በአማራ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 27 ሺሕ ተፈናቃዮች ለወራት ያለ እርዳታ ቆይተዋል ተባለ

0
570

በአማራ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያሉ ከ27 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ምግብን ጨምሮ ምንም ዓይነት ድጋፍ ሳያገኙ ለወራት መቆየታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) ኅዳር 7/2012 ይፋ ባደረገው ሪፖርት አስታወቀ።

በሪፖርቱ ላይ እንደተመለከተው፣ ተፈናቃዮቹ ድጋፍ እንዳያገኙ የኹለቱ ክልልች አመራሮች ጥረት ያለማድረጋቸው እና ተፈናቃዮቹን ወደ ተፈናቀሉበት ቦታ እንዲመለሱ ጫና እንደሚያደርጉባቸው አስታውቋል። የኦቻ ባልደረቦች በኹለቱም ክልሎች ተዘዋውረው ባጠናቀሩት መረጃ፣ በአዊ እና መተከል ዞኖች በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ምግብን ጨምሮ ምንም ዓይነት ድጋፍ ሳያገኙ በመጠለያ ካምፖች ውስጥ መኖራቸውን አስታውቋል።

ለዘመናት በመተከል ዞን የኖሩ 17 ሺሕ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከመጋቢት 2011 ጀምሮ ወደ ቻግኒ እና ጃዊ ወረዳዎች መፈናቀላቸውን፣ እንዲሁም ዐስር ሺሕ የጉሙዝ ብሔር ተወላጆች ደግሞ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መፈናቀላቸውን ማረጋገጡን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ክንፍ ይፋ አድርጓል። ይህንን የመስክ ውጤት ለኹለቱም የክልል መንግሥታት ቢያስታውቅም፣ በተለይ የአማራ ክልል መንግሥት የተፈናቃዮቹን መኖር ማስተባበሉን እንዲሁም ከመጋቢት ጀምሮ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳይደረግላቸው ማድረጉን አንስቷል።

‹‹ክልሉ አዲስ የተፈናቀሉ ሰዎችን በይፋ ያልተቀበለ ሲሆን ወደ መጡበት ቦታ ተመልሰው እንዲሔዱም ፍላጎት አሳይቷል›› ሲል በሪፖርቱ ላይ ገልጿል። ‹‹ተፈናቃዮች የነፍስ ወከፍ ድጋፍ እንዳያገኙ ከመደረጉ ባሻገር ጥለውት የመጡት አካባቢም ፈራርሶባቸዋል። ወደ መጡበት አካባቢ ለመመለስ ፈቃደኛ የሆኑት ተፈናቃዮች ብቻ የተወሰነ ድጋፍ እያገኙ ነው›› ሲል አስታውቋል።

የአዊ ዞን የሥራ ኀላፊዎች በበኩላቸው፣ የተፈናቃዮቹን መኖር አምኖ በመቀበል የልማት አጋሮች እንዲደግፏቸው ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ የክልሉ መንግሥት እውቅና ባለመስጠቱ ምክንያት ሀብት አሰባስቦ ዜጎቹን ለመርዳት ባለማስቻሉ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል ሲል ሪፖርቱ አጽንኦት ሰጥቷል።

በመተከል ያለው የተፈናቃዮች ሁኔታ እጅ አስከፊ ነው ያለው ኦቻ፣ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሕጻናት መኖራቸውን እና በተለይም በጉባ ወረዳ ያለው ሁኔታ አስከፊ መሆኑንም ገልጿል። በመተከልም ሆነ በአዊ ወረዳዎች ምንም ዓይነት ሰብአዊ ድጋፍ የሚሰጡ የእርዳታ ድርጅቶች የሉም ሲልም ሪፖርቱ አረጋግጧል።
በግልገል በለስ ከተማ ከአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ የተፈናቀሉ 1200 የጉሙዝ ብሔር ተወላጆች አዲስ በተገነባ አንድ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የክረምቱን ወራት እንዲጠለሉ የተደረገ ሲሆን፣ ተፈናቃዮቹን መልሶ ማቋቋም ባለመቻሉ አሁንም እዛው እንደሚገኙ በአካል ማረጋገጡን ኦቻ አስታውቋል። የየትምህርት ቤቶች መክፈቻ ጊዜ መድረሱን ተከትሎ በትምህርት ቤቱ ሊማሩ የነበሩትን በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በሌላ ትምህርት ቤቶች እንዲማሩ ተደርጓል። ተማሪዎችም ከግልገል በለስ በ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፓዊ በመሔድ እንዲማሩ ተገድደዋል።

ተፈናቃዮችም የጤና እና የንጽህና ጉዳዮች ላይ መቸገራቸውን ለልዑኩ ያስረዱ ሲሆን፣ ወደ ተፈናቀሉበት አካባቢ ተመልሶ የመሔድ ፍላጎት እንደሌላቸው ገልፀዋል። መንግሥት በመተከል ዞን መሬት እንዲያቀርብላቸው ጠይቀዋል ያለው ድርጅቱ፣ የኹለቱ ክልል መንግሥታት ግን በተቀናጀ መልኩ ተፈናቃዮቹን ወደየ ተፈናቀሉበት ቦታ ለመመለስ እየሠሩ ነው ብሏል። የግለሰቦቹን ፍላጎት እና ደኅንነት ከግምት ውስጥ ሳያስገቡ የክልል መንግሥታቱ እየተንቀሳቀሱ ነው ያለው ኦቻ፣ በአካባቢው እርቅ እና ሰላም ለማምጣትም ጊዜ ይወስዳል ሲል አጽንኦት ሰጥቷል።

በጉዳዩ ላይ የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የስራ ኃላፊዎችን በስልክ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here