ያለአግባብ የውጭ አገር ዜጎችን በሚቀጥሩ አምራቾች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ

0
564

በኢንዱስትሪ መንደሮች ውስጥ በአገር ውስጥ ዜጎች መሰራት እየተቻሉ ከህግ ውጪ ያለአግባብ የውጭ ዜጎችን ቀጥረው ለሚያሰሩ አምራቾች ላይ የቅጥርን ሁኔታ በመፈተሽ እርምጃ እንደሚወስድ እና ለዚህም የሚረዳውን ጥናት ማጠናቀቁን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ ሕዳር 10/2012 የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ኮሚሽነሩ አበበ አበባየሁ እንዳሉት የውጪ አገር ዜጎችን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለአግባብ የሚቀጥሩ ድርጅቶች ላይ የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸውን እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

ትርፍ ለማትረፍ ቀላሉ ዘዴ የአገር ውስጥ ሠራተኛን መቅጠር ስለመሆኑ የሚያነሱት አበበ፤ ነገር ግን የውጭ ዜጋ ቅጥሩ አግባብ ያለው መሆኑን ለማጣራት ሥራው በአገር ውስጥ ሠራተኛ ሊሠራ የሚችል መሆን አለመሆኑን ማጣራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በአዳማ የኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ቻይናውያን የውጭ አገር ዜጎች የመጫንና የማውረድ ሥራዎችን ሢሰሩ እንደነበር ባደረኩት ማጣራት ደርሻለሁኝ ያለው የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴው ድርጅቱ የአገር ውስጥ ሠራተኞች እንዲቀጥር ስለመደረጉ ጠቅሷል፡፡

ኮሚሽኑ በተሌም በአዳማ የኢንዱስትሪ ምንደር ተፈጠረ የለተባለው የአሠራር ክፍተት በትክክል እንደነበረና የተከሰተውም የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው ጫኝና አውራጅነት ለመሥራት ባስቀመጡት ዋጋ የተነሳ ከባለሃብቶች ጋር መግባባት ላይ ባለመድረሳቸው እንደነበር አስረድቷል፡፡ የውጭ ዜጎች ይህን ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ሲታወቅ ግን ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አመራሮች ጋር በመነጋገር ኢትዮጵያውያኑ የጫኝና አውራጅ የዋጋ ተመን ወጥቶላቸው እንዲሰማሩ ተርጓል ሲሉ አበበ አብራርተዋል፡፡

ኢንዱስትሪ መንደሩ ሲገነባ ካሳ በበቂ ሁኔታ አልተከፈለንም በሚል የአካባቢው ወጣቶች መንገድ ይዘጉ እንደነበር እና ምርቶች እንዳይወጡ የመከልከል ሁኔታ አሁንም እየተስተዋለ ስለመሆኑ ለቋሚ ኮሚቴው አሳውቀዋል፡፡

በአጠቃላይም በኢንዱስትሪ መንደሮች ውስጥ የውጭ አገር ዜጎች የሥራ ቅጥር ሁኔታን በተመለከተ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ቦርድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መመሪያ መሰረት ዜጎቹ ሥራ ሊቀጠሩ የሚችሉት በሦስት የሥራ መደቦች ስለመሆኑ ተቀምጧል የሚሉት በኢንቬስትመንት ኮሚሽን የኢንዱስትሪያል ፓርኮች የምክትል ኮሚሽነር ረዳት ዳዊት ፈለቀ ናቸው፡፡

በተቆጣጣሪነት ወይንም በአሰልጣኝነት ወይም በሌላ የቴክኒክ ሥራ የውጭ አገር ዜጋን ቀጥሮ ለማሠራት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የሥራ ፈቃድ እንደሚሰጥ ዳዊት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ በአስተዳደር ዘርፎች ላይ ለሚፈጸም የውጭ አገር ሠራተኞች ቅጥር ምንም አይነት ገደብ የማያስቀምጥ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

መመሪያው መሰረት በፓርኮቹ ውስጥ ያሉትን የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያውያን መተካት ያልተቻለበት ምክንያት አንድ ኢትዮጵያዊ በሥራ ገበታ ከሦስት ወር በላይ ባለመቀመጡ ከፍተኛ የሆነ ሰዎችን አሰልጥኖ የማጣት ችግርን እንደምክንያት የሚያስቀምጡ ስለመኖራቸው ዳዊት ይገልጻሉ፡፡

በኮሚሽኑ ፈቃድ የውጭ ዜጋን የሚቀጥሩ ኩባንያዎች አንድ ተቀጣሪን ማቆየት የሚችሉት ለሦስት አመት ብቻ ነው፡፡ ኩባንያዎቹ የውጭ ዜጋው የቅጥር ውል እንዲራዘም ከፈለጉ በኮሚሽኑ ተጣርቶ ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲላክ ብቻ የሚፈጸም ይሆናል፡፡

መንግሥት ይህን የመቆጣጠርና የመከላከል ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ ለእድሳት በሚመጡበት ወቅት በኢትዮጵያውያን እንዲተኳቸው የማስገደድ ሥራ እየተሠራ ስለመሆኑ ኮምሽኑ አስታውቋል፡፡

የሠራተኛና አሠሪ ሕግ በውጭ ዜጎች ቅጥር እንዲሠራ በኢትዮጵያውያን ሊሠሩ የማይችሉ ሥራዎች በሚል መጥቀሱ ተገቢ አይደለም የሚል ትችት በተደጋጋሚ ይነሳበታል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here