በአምቦ ውሃ እና ኮካ ኮላ ላይ ተጥሎ የነበረው ቅጣት ውድቅ ተደረገ

0
836

የሸማቾች ጥበቃ እና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት አምቦ ውሃ እና ኮካ ኮላ ውህደት ፈፅመዋል በማለት ከዓመታዊ ገቢያቸው ላይ አምስት በመቶ እንዲቀጡ አስተላልፎት የነበረውን ወሳኔ ውድቅ በማድረግ ድርጀቶቹን በነፃ አሰናበተ።

የባለሥልጣኑ ዐቃቤያን ሕግ ከጥር 2009 ጀምሮ የኹለቱ ድርጅቶች የሥራ አመራሮች እና ሠራተኞች በተገኙበት በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) አዳራሽ ውስጥ ውህደት በመፈፀም በጋራ እንሠራለን የሚል መልእክት አስተላልፈዋል በሚል ሰኔ 2010 ካነሱት ጉዳይ በኋላ ክስ መመሥረቱ ይታወሳል። ምርቶቹ በሚከፋፈሉባቸው ተሽከርካሪዎች ላይ የኹለቱን ምርቶች ምልክት ተጠቅመዋል፣ የአንዱ ምርት አከፋፋይ የሌላውን ምርት እንዲይዝ አድርገዋል፤ ይህም ድርጅቶቹ በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን እና መቀላቀላቸውን የሚያሳይ ነው ሲል ባለሥልጣኑ ያካሔደውን ምርመራ ዋቢ በማድረግ ለኹለት ዓመት ሲከራከሩ ቆይተዋል።

ድርጅቶቹ በበኩላቸው በመካከላችን የተፈፀመ ምንም ዓይነት ውል የለም ሲሉ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ሲከራከሩ ቆይተዋል። የኹለቱም እናት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ውጪ የመቀላቀል ስምምነት ማድረጋቸውን ዋቢ በማድረግ ለምሥራቃዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ማሳወቃቸው በጋራ የሚያከናውኑትን ሥራ ለማካሔድ በቂ መሆኑን ገልፀው ተከራክረዋል። በተጨማሪም ምርቶቻቸውን በጋራ ማከፋፈላቸው ውህደትን አያመላክትም በማለት የዐቃቤ ሕግን ክስ ማስተባበላቸው ይታወሳል።

የባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ማንኛውም ዓመታዊ ሽያጩ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የንግድ ድርጅት ውህደት ከመፈፀሙ በፊት ለባለሥልጣኑ በማስታወቅ ባለሥልጣኑ በሸማቾች መብት እንዲሁም በፍትኀዊ ገበያ ውድድር ላይ ያለውን ጫና በማጥናት ፈቃድ እንደሚሰጥ ይደነግጋል።

ዐቃቤያን ሕጉም ይህ ፈቃድ ባልተሰጠበት ሁኔታ መዋሀድ ሕገወጥ ነው በማለት በመሠረቱት ክስ፣ የባለሥልጣኑ የስር አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የኮካ ኮላ በኢትዮጵያ አምራች ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግስ እና አምቦ የማአድን ውሃ ክሱ በተመሠረተበት 2010 ከሰበሰቡት አጠቃላይ ገቢ አምስት በመቶ እንዲከፍሉ እንዲሁም ውህደቱ እንዲቆም እና ምንም ዓይነት ሥራ በጋራ እንዳያከናውኑ ብይን አስተላልፎ ነበር።

የባለሥልጣኑ የስር አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ለይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ተከሳሾች ባቀረቡት ይግባኝ መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያየው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ይህንንም ተከትሎ የስር ፍርድ ቤቱ በተነሱት ነጥቦች ላይ በድጋሚ አከራክሮ ሰኔ 20/ 2011 በዋለው ችሎት የኩባንያዎቹ ውህደት ሕገወጥ በመሆኑ እንዲቆም እንዲሁም ክሱ ከመጀመሩ አንድ ዓመት በፊት ባለው አጠቃላይ ገቢያቸው ላይ 5 በመቶ የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልባቸው መወሰኑ ይታወሳል።

ጉዳዩን በድጋሚ ለባለሥልጣኑ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሐምሌ 18/ 2011 ይግባኝ ያሉት ተከሳሾች፣ ለክስ የሚያበቃ ጥፋት አልፈጸሙም ሲል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ ኅዳር 11/2012 ወስኖላቸዋል። ድርጅቶቹ ያደረጉት ውህደት ካለለባለሥልጣኑ ማሳወቅ ነበረባቸው ያለ ሲሆን፣ በባለሥልጣኑ ክስ ላይ የተዘረዘሩት ምክንያቶች ግን ለክስ የሚያበቁ አይደሉም ሲል ችሎቱ ፈርዷል።

‹‹ምልክቶችን በጋራ መጠቀሙም ይሁን ስለ ውህደቱ በቃል መነገሩ ውህደቱን አያረጋግጥም›› ያለው ችሎቱ፣ የኹለቱን እናት ድርጅቶች ከአገር ውጪ መዋሀድ እና ለኮሜሳ ማሳወቅ ከግምት ወስጥ በማስገባት በኹለቱ ድርጅቶች ላይ በስር ፍርድ ቤቱ ተጥሎ የነበረውን ከዓመታዊ ገቢያቸው ላይ አምስት በመቶ እንዲቀጡ የሚለውን ወሳኔ በመሻር በነፃ አሰናብቷቸዋል።

የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ጠበቃ የሆኑት ፍቃዱ ጴጥሮስ፣ ውሳኔው ተገቢ ነው ያሉ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ገለልተኛ በመሆን ጉዳዩን በመመልከቱ ደስተኛ ነን ብለዋል። በዋናነትም የድርጅቶቹ አለመዋሀድ መረጋገጡ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው ብለዋል። ክርክሩ ለሦስት ዓመታት የዘለቀ እንደነበር እና ድርጅቶቹ የውጪ አልሚዎች በመሆናቸው በሥራዎቻቸው ላይ እንዳያተኩሩ አድርጓቸዋልም ብለዋል። ቅጣቱም ድርጅቶቹ በፍራንቻይዝ የሚሠሩ በመሆናቸው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር እና ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ ውሳኔው ከተላለፈበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይግባኝ የማለት መብት ያለው ሲሆን አዲስ ማለዳ ይህንን ዜና እስካጠናቀረችበት ዕለት ድረስ በውሳኔው ላይ ይግባኝ አልተጠየቀም።

አምቦ የማዕድን ውሃ በ1922 የተመሠረተ ኩባንያ ሲሆን መንግሥት ወደ ግል ባለቤትነት በተለያዩ ደረጃዎች ያስተላለፈው ሲሆን፣ በመጨረሻም ሳብ ሚለር ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ ያስተዳድረዋል። ሳብ ሚለር በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የኮካ ኮላ ሳብኮ ጋር ባደረገው ውህደትም ኮካ ኮላ ቤቭሬጅስ አፍሪካን በደቡብ አፍሪካ በጋራ ከአምስት ዓመታት በፊት መመሥረታቸው ይታወቃል። ሳብኮ የኢስት አፍሪካን ቦትልሊንግስን ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ የያዘ ድርጅት ሲሆን፣ በተመሳሳይ በ1950ዎቹ በመንግሥት ከተቋቋመ በኋላ ወደ ግል ይዞታ መዘዋወሩ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here