ሴት ልጆች በተፈጥሮ ምክንያት ኋላ እንዳይቀሩ አሁንም ብዙ ይጠበቃል

0
996

የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ይልቁንም የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ ምርት የህከምና ቁሳቁስ አካል ሆኖ የመካተቱ ነገር ለበርካታ ሴቶች አስደሳች ዜና ነው። ይህም በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ቤት ለሚቀሩና ቀናቱን በጭንቀት ለሚያሳልፉ ሴቶች እረፍት ሲሆን ጤናማም ነው። አልፎም ለሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግም መንገድ ይከፍታል።

የሴቶች የወር አበባ ተፈጥሮአዊ ቢሆንም በአገራችን በተለያየ አካባቢና በተለያዩ ጊዜያት የሚጸየፉትና ሴቶችም የሚገፉበት ሰበብ ነበር። በተለያዩ ከከተማ ርቀው ባሉ የኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች፤ ጥቂት በማይባሉት ባሕል መሠረት በወር አበባ ጊዜዋ ሴት ልጅ የቤት ዕቃ እንዳትነካና እስክትጸዳም ድረስ ለብቻዋ እንድትቀመጥ ይደረጋል። ወይም በሌላ አነጋገር መገለል ይደርስባታል።

የሚያሳዝነው ደግሞ ይህን ባህል በማስቀጠል ትልቁን ሚና ሲጫወቱ የኖሩትም ሴቶች ራሳቸው መሆናቸው ነው። ልጆቻቸውን የሚቆነጥጡትና የሚያርቁት እናቶች በተቀበሉትና ስርዓት ነው ብለው ባመኑበት ባህል መሠረት ስለሆነ። እናም ታድያ እንዲህ ያሉ ምክንያታዊና አሳማኝ ያልሆኑ እይታዎች ሴቶችን ሲያሳቅቁ ኖረዋል።
ያንን ተሻግሮ በመጣው የተሻለ የተባለ ዘመን ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሔዱና የወር አበባም ሴት ልጅ እንዲጸየፏት የሚያደርግ ስላለመሆኑ ማኅበረሰቡ በከፊል የተረዳበት ጊዜ ነው። ይሁንና ማኅበረሰቡ ከማወቅ ውጪ ያደረገው ነገር አልነበረም። ይህን ጊዜ ደግሞ የንጽህና መጠበቂያን የማግኘት ጉዳይ ለሴቶች ፈታኝ ሆነ። ከከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ቀርቶ መሃል ከተማ ላይ ያሉ ሴት ልጆችም የንጽሕና መጠበቂያዎችን በቀላል አያገኙም።

መረጃዎች እንደሚያሳዩትም አንዲት ታዳጊ ሴት የወር አበባ በምታይበት ጊዜ ላይ ወደ ትምርት ቤት እንደማትሄድ ያሳየሉ፡፡ በአንድ ወር ውስጥም ከዚህ ጋር በተያያዙ ምክኒያቶች ከትምህርት ገበታዋ ላይ ትታጎላለች፡፡ ይህም ሴቶችን ቤት ውስጥ እንዲውሉ በማድረግ ላለ እድሜ ጋብቻ እና መሰል ማህበራዊ ችግሮች ሲዳርጋቸው ይስተዋላል፡፡

ሴት እህቶቻችንም ከንፅህና መጠበቂያዎች እጥረት የተነሳ እንደጨርቅ ያሉ ቁሶችን ሲጠቀሙ ማየት በተለይም የንፅህና መጠበቂያዎች በስፋት ባልተስፋፉበት እና ግንዘቤው ባልዳበረባቸው ገጠራማ የአገራችን ክፍሎች ይስተዋልል፡፡ ይህም ይህም ሴቶችን ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች እና ከንፅህና ጉድለት ጋር ተያዘው ለሚከሰቱ የጤና እክሎች እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡

የንፅህና መጠበቂያው ተመርቶ የሚገባው ከውጪ ሲሆን፣ ይህም በብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሲሰጠው የሚሆን ነው። ይህም በተጓዳኝ ዋጋው ላይ ውድነት እንዲኖር አድርጓል። ቀረጡ ከፍ ማለቱና ዋጋው መጨመሩ የንጽህና መጠበቂያን ቅንጦት አስመስሎት ቆይቷል። አዲስ ማለዳ ባገኘችው መረጃ መሠረት፣ በኢትዮጵያ የንጽህና መጠበቂያ በቅንጦት ዕቃ ዓይነት የሚመደብ ከ 67 እስከ 123 በመቶ ቀረጥ የተጣለበት ነው። አንድ እሽግ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ዋጋም በአማካይ 40 ብር ገደማ እንዲሆን አድርጎታል።

በዚህም ምክንያት በርካታ ሴቶች የወር አበባ በሚያዩባቸው ቀናት ትምህርት ቤት ከመሔድ ይቆጠባሉ። ይህ ከትምህርት የሚያጎድልባቸው ብቻ ሳይሆን በሥነ ልቦናም የሚፈጥረው ጫና አለ ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ለዚህም ነው ከተቻለ በነጻ ካልሆነ በቅናሽ እነዚህ ቁሳቁሶች እንዲቀርቡ የሚለውን ሐሳብ አብዝታ የምትደግፈው።
ይህም ብቻ ሳይሆን እነዚህን የንጽህና መጠበቂዎች መጠቀም እንደሚቻል በሚገባ ያላወቁ፣ በግልጽ ንግግርና ምክክር የማይደረግባቸው የአገራችን ክፍሎች ደግሞ አሁንም አሉ። በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች ደግሞ በኢትዮጵያ ሠላሳ አምስት ሚሊዮን ከሚጠጉ የወር አበባን ከሚያዩ ሴቶች መካከል፤ 70 በመቶ ለሚሆኑት የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ተደራሽ አይደሉም።

ይህ ግን ሊቀርና ሊለወጥ ይገባል። ይህን አጋጣሚም በዚህ አንጻር መጠቀም አስፈላጊ ነው። ነገሩ የጤና ጉዳይም ነውና ግንዛቤ ከመስጠት ጀምሮ ቁሳቁሶቹን ተደራሽ ማድረግም አብረው የሚሠሩ ሊሆኑ ይገባል።

አሁን ላይ በጤና ሚኒስቴር በወጣው መረጃ መሠረት ንጽህና መጠበቂያዎች በዋጋ እስከ ግማሽ በሚደርስ መጠን ሊቀንሱ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ይህ ቀላል አካሔድና ውጤት አይደለም። በርካታ ስለ ሴቶች መብት የሚሟገቱ ሴቶችም በዚህ ላይ ብዙ ብለዋል፤ አንድም ተማሪ በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታዋ መቅረት የለባትም ሲሉም ድምጻቸውን አሰምተዋል። ይህም ለእነርሱ አንዱ ስኬት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። የጋዜጣችን የዝግጅት ክፍልም ይህንን ንቅናቄ ለመሩ እንዲሁም ጥሪውን ተቀብለው ለተሟገቱ በሙሉ ምስጋና ይገባቸዋል ብላ ታምናለች፡፡

እንኳን በሚዲያ ወጥተን ልንሟገት ቀርቶ ስለ የወር አበባ ለመነጋገር በማይደፈርበት ማህበረሰብ ውስጥ ለዚህ መብት ተሟገቱት ሴቶች ለራሳቸው ወይም ለሴት ልጆቻቸው ብለው ሳይሆነ ለትውልድ እና ድምፅ አልባ እህቶቻችን ድምጽ ነው፡፡ ይህ ሴቶች ጩኀኸት ብቻ ሳይሆን ብዙ ወንዶችም የተሳተፉበት ነበር፡፡
አሁንም ግን ገና ነው። በመንግሥት ደረጃ የፖሊሰ ለውጥ ሊመጣ ከተቻለና እነዚህ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አቅም የሌለው የማይጠቀማቸው የቅንጦት እቃ መሆናቸው ከቀረ፣ ቀጥሎ የባለሀብቱና የአስመጪው ድርሻ ይሆናል። ይህም አንዱ ማኅበራዊ ግዴታን የመወጫ መንገድና አጋጣሚ ነው። በዚህም በርካታ ሴቶች ጋር ተደራሽ መሆን፣ ትምህርት ቤት ያለ መሳቀቅና እፍረት እንዲሔዱ ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ የሃገራችን የህዝብ ብዛት ከግማሽ በላይ ለሆኑት ሴቶች እንዲሁም ለወንድ ስራ አጦችም የስራ እድል የሚፈጥር ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ከውጪ ማስገባቱ ቀርቶ አገራችን ውስጥ አምራች ኢንዱስተሪዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ ከውጪ እንዲሁም የአገር ባለሃብቱ እንዲሰማራበት ጥያቄው መቀጠል አለበት፡፡

ይህ ለኢትዮጵያ አርሶ አደርም የሚያመርተው የጥጥ ምርት የአገር ውስጥ ገበያ ላይ በተሸለ ዋጋ እንዲሸጥ እድል የሚከፍት ሲሆን ወደ ሌሎች አገራት በመላክም ኢኮኖሚያችን ትልቅ ሚና የሚጨወት መሆን ይገባዋል፡፡

በኢትዮጵያ ገበያ በሰፊው የሚታየው እና በተለያዩ የአለም አገራት ለማህፀን ካንሰር በማጋለጡ ምክኒያት እየተከለከለ ያለው በፕላስቲክ ምርቶች ሚመረቱ የወር አበባ መጠበቂያዎች በአገራችን በሰፊው ይታያሉ፡፡ መንግስት እነዚህን ምርቶች በማገድ እንደም የሴቶች ጤና ሌላም ለአካባቢ ብክለት የሚያበረክቱትን አሉታዊ ሚና መቀነስ አለበት ብላ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች፡፡

በንጽና መጠበቂያ ምርቶች ላይ ለመጣው ውጤት ሴት ሚኒስቴሮች ያደረጉት ተሳትፎ ቀላል የሚባል አለመሆኑን የምትገነዘበው አዲስ ማለዳ የሴቶች መወከል ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚሳይ ነው ብላ ታምናለች፡፡

ይሁንና ግን ጥራት ከግምት ውጪ ሊሆን አይገባም። እነዚህ ንጽህና መጠበቂያዎች እንደ መድኃኒት ተቆጥረው ሲመጡ፣ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉና ጎጂ እንዳይሆኑም ጥብቅ ቁጥጥር ሊደረግ ይገባል። ጥራታቸው ከዋጋቸው ጋር መዛመድም የለበትም። ጤናን በዋጋ የሚሸምቱት አይደለምና፤ ችላ ሊባል እንደማይገባ አዲስ ማለዳ አጽንኦት ትሰጣለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here