ወደ መኖሪያ ቀበሌዎች የገቡት አምስት አንበሶች ጉዳት አደረሱ

0
1340

የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን ጉዳዩን አስተባብሏል
ከአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በመውጣት በፓርኩ አካባቢ በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ የገቡት አምስት ጥቁር አንበሶች በቤት እንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን እና የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ እንዲሁም አንበሶቹ ላይም ጉዳት እንዳይደርስ ስጋት አድሮብኛል ሲል ፓርኩ አስታወቀ።

ከኅዳር 07/2012 ጀምሮ አንበሶቹ ከፓርኩ በመውጣት በአካባቢው በሚገኙ ደራራ እና እኛኛ በሚባሉ ቀበሌዎች መግባታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ እስከ አሁን በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም የተለያዩ የቤት እንስሳትን አድነው መመገባቸው ግን ነዋሪዎች ላይ ስጋት መፍጠሩ ተገልጿል። አካባቢው በአሁኑ ወቅት በረጃጅም ሳር በመሸፈኑ እና ይሄም ለአንበሳዎቹ ለመደበቅ እና ለማድባት ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥርላቸው የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ጥንቃቄ ሊያደረጉ እንደሚገባ ተጠቅሷል።
ከ200 በላይ ጥቁር አንበሳዎች በፓርኩ እንደሚኖሩ የተገለፀ ሲሆን፣ በምሥራቅ አፍሪካ በመጥፋት ላይ ከሚገኙት ዝርያዎች ውስጥ የሚመደበው ይህ የጥቁር አንበሳ ዝርያ ስጋት ላይ መውደቁንም ፓርኩ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የፓርኩ አስተዳደር በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ፓርኩን ለእንስሳቱ የሚመች ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ተብሏል። ከዚህም በተጓዳኝ አርብቶ አደሮች እና በአካባቢው የሚኖሩት ፈላታዎች ወደ ፓርኩ እንዳይገቡ ተደርጓል። ሆኖም ከአጎራባቹ እና በሱዳን ከሚገኘው ዲንዲራ ብሔራዊ ፓርክ በኩል ባለው የሰዎች ጫና ምክንያት አንበሳዎች እና ሌሎች የዱር እንስሳት ለስደት እና ከፓርኩም በመውጣት ጉዳት እንዲያደርሱ ምክንያት እየሆነ ነው ተብሏል።

የአካባቢውን ማኅበረሰብ ለማረጋጋት እና የደረሰውን ጉዳት ለመመልከት የፓርኩ ኀላፊዎች የአደጋ ጊዜ ቡድን በማቋቋም በተጨሪም የአካባቢውን የጸጥታ ኀይሎች ወደ አካባቢው መላካቸውን እና ከወረዳው አሰተዳደሮች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን፣ ኅብረተሰቡ እንዳይደናገጥ እና ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክቶች እየተላለፉ እንደሆነ የፓርኩ ኀላፊ ኤፍሬም ወንዴ ገልጸዋል።

ብሔራዊ ፓርኮችን የሚያስተዳድረው የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን በበኩሉ፣ በአካባቢው ላይ ምንም ዓይነት ከዱር እንስሳት ጋር የተያያዘ ችግር የለም በማለት ጉዳዩን አስተባብሏል።

በፓርኩ ላይ እንዲሁም በፓርኩ አካባቢ ማኅበረሰብ እና በነዋሪዎቹ ላይ ከኹለት በላይ ምርምሮችን ያደረጉት እና በጎንደር እና በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ በማስተማር ላይ የሚገኙት ተባባሪ ፕሮፌሰር ገናነው አግተው በበኩላቸው፣ ከ1962 ጀምሮ ከማዕከላዊ አፍሪካ አገራት ድንበር በማቋረጥ በሱዳን ድንበር በኩል ወደ ፓርኩ የሚመጡ አርብቶ አደሮች መኖራቸውን ያነሳሉ። እነዚህ አርብቶ አደሮች ‹ፈላታ› የሚል ስያሜ በማኅበረሰቡ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በፓርኩ የበጋውን ወቅት በማሳለፍ የክረምት ወራት ላይ ወደ መጡበት አካባቢ ይመለሳሉ ሲሉ ይገልፃሉ።

ፈላታዎቹ በአራት ጎሳዎች የተከፋፈሉ ናቸው የሚሉት ገነነው፤ በአጠቃላይ ከ 10 ሺሕ በላይ እንደሚሆኑ ይጠቅሳሉ። ከ 100 ሺሕ በላይ እንስሳትን ይዘው በመንቀሳቀሳቸው የፓርኩ ይዞታ በተደጋጋሚ ለልቅ ግጦሽ በመጋለጡ እንዲሁም መሬቱ በእንስሳት ኮቴ ሲረጋገጥ በመቆየቱ ፓርኩ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል ሲሉም ተናግረዋል። በበጋ ወቅት ሳሩ ስለሚደርቅ ለመኖ የሚሆኑ የዛፍ ዝርያዎች እየተቆረጡ ለከብቶች ይሰጣሉ። በአሁኑ ወቅትም ረዣዥም ሳር ለእንቅስቀሴ የማያመች በመሆኑ በእሳት ያቀጥላሉ። ይህም እንስሳቱ እንዲደናገጡ በማድረግ ወደ ጎረቤት አገራት ፓርኮች እንዲሰደዱ አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል።
ይህም አንበሶቹን በመግፋት ከፓርኩ ክልል እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል ያሉ ሲሆን፣ አንበሳ በባህሪው ቀድሞ የነበረበትን ቦታ የመጎብኘት ባህሪ ያለው መሆኑ እና አንበሶቹ ለኑሮ የሚያመቻቸውን ቦታ የሚመርጡ በመሆናቸው እንዲሁም በእነዚህ ጎሳዎች በሚደርስባቸው መተናኮል እና መገፋት ከፓርኩ ለመውጣታቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

‹‹በጎሳው ዘንድ እንስሳቱን የዓባይን ውሃ የማጠጣት እምነት ስላለ ምዕራብ ጎንደርን እና ቋራን አቋርጠው ጣና ሐይቅ ድረስ ይሔዳሉ›› ሲሉ ተመራማሪው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ይህም ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲጋጩ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በአልጣሽ ውስጥ የሚኖሩ ዝሆኖችን የመግደል እና ጥርሳቸውን ለገበያ የማቅረብ፣ ሕገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውር ላይም እንደሚሳተፉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ›› ብለዋል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ወደ ፓርኩ እንዳይገባ ተከልከሎ ሳለኅ እነዚህ ድንበር ተሻጋሪ አርብቶ አደሮች በፓርኩ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ መፈቀድ የለበትም፤ የአካባቢውን ኅብረተሰብም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያስቆጣ ያለ ጉዳይ ነው በማለትም ያብራራሉ።

‹‹የሰሃራ በረሃን መስፋፋት ለመከላከል እንደ ግርግዳ ሆኖ የሚያገለግለው ፓርኩ በውስጡ በርካታ የእፅዋት ዝርያዎችን የያዘ እና በኢትዮጵያም ድርቅን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ነው›› ሲሉ የፓርኩን ሁኔታ በቅርብ የሚከታተሉት ገናነው አግተው ይናገራሉ። ‹‹ይህ ሲሆን የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን በዝምታ ከመመልከት ውጭ ከውድመት ለመታደግ በተግባር የሰጡት መፍትሔ የለም›› በማለት ወቀሳቸውን ይሰነዝራሉ።

አንበሳዎቹ ካልተተናኮሏቸው ጥቃት የማድረስ ባህሪ የላቸውም ያሉት ባለሞያው፣ ኅብረተሰቡም አንበሳዎቹ በሚያጋጥሙት ወቅት ከመተናኮል እና ጥቃት ከማድረስ መቆጠብ፣ ለፀጥታ ኀይሎች እና ለፓርኩ በፍጥነት ማሳወቅ አለበት ብለዋል።

አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ጎንደር፣ በቋራ ወረዳ የሚገኝ ብሔራዊ ፓርክ ሲሆን፣ 266 ሺሕ 570 ሔክታር ስፋት አለው። የፓርኩ ደቡባዊ ክፍል ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ሰሜኑ የቋራ ወረዳ አራት ቀበሌዎች ያረፉበት ሲሆን፤ በምሥራቅ ገለጎና ባምባሆ፤ በምዕራብ ሱዳን፤ የሱዳኑ ዲንዲር ብሔራዊ ፓርክ ያዋስኑታል።

ፓርኩ ከ130 በላይ የተለያዩ የእጽዋት ዝርያዎች ያሉት፤ አንበሳ፣ አጋዘን፣ ዝሆን አና ከርከሮን ጨምሮ ወደ 37 ዓይነት የተለያዩ አጥቢ የዱር እንስሳት የሚገኙበትም ነው። በአእዋፍ ይዘቱ ከፍተኛ ከሚባሉት ፓርኮች መካከል የሚመደበው አልጣሽ፣ 204 የሚሆኑ የተለያዩ የአእዋፍ ዝርያዎች በውስጡ ተጠልለው ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 55 ኅዳር 13 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here