አርብ ጥቅምት 9 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ የዲጅታል ፋይናስ አገልግሎት ላይ የተሰማራው ካቻ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት አክሲዮን ማሕበር፤ በአገሪቱ የመጀመሪያው “የግል የክፍያ ሰነድ አዉጪ” በመሆን በሙሉ አቅሙ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።
ሰኔ 2022 ከብሔራዊ ባንክ የሙከራ ፈቃዱን ያገኘው ካቻ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት፤ በተለያየ ደረጃ እና የአገልግሎት አማራጮች በመጠቀም የሙከራ ትግበራውን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጿል።
በዚህም በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ባንኮች እና የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ሰጪዎች ጋር ያለውን ተናባቢነት በተሳካ ኹኔታ በማጠናቀቅ አገልግሎቶቹን በሙሉ አቅም ለመጀመር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘቱን ተከትሎ፤ በትናንትናው ዕለት የሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩን ይፋ አድርጓል።
ይህን ተከትሎ በካቻና በተለያዩ ባንኮች፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች ስትራቴጂካዊ አጋሮች ጋር በጋራ አብሮ ለመስራት የፊርማ ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።
በተጨማሪም ካቻ ከአለም አቀፍ ሓዋላ አስተላላፊዎች ጋር የፈጠረውን አጋርነት ያሳየው ደህንነቱ የተጠበቀ የውጪ ሓዋላን በማሳለጥ፤ ላኪዎችም ሆኑ ተቀባዮች ለተጨማሪ የፋይናንስ አገልግሎቶች ዕድል የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱን ገልጿል።
ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የአሰራር ስርዓት ዓለም አቀፍ የሐዋላ አስተላላፊዎች ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመናበብ እና ገንዘብ ለማስገባት የሚወስድባቸውን ከፍተኛ ወጪ ለማስቀረት፤ ከካቻ ጋር በሚፈጥሩት የሥራ አጋርነት ወደ ኹሉም የባንክ እና የሞባይል ገንዘብ ሂሳቦች ገንዘብ ማስተላለፍ የሚችሉበት ስርዓት ነው።
የዚህ አገልገሎት ወደ ሥራ መግባት የካቻ አጋር ባንኮች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ በር የሚከፍት መሆኑ ተመላክቷል።
ካቻ የገንዘብ ዝውውሮች፣ የዲጂታል ብድሮችን፣ ያለ ካርድ በኢቲኤም ማሽኖች እንዲሁም በወኪል አማካኝነት ገንዘብ የማውጣት፣ የአየር ሰዓት መሙላት እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ ኹለንተናዊ አገልግሎት ይሰጣል።



