23 ኢትጵያዊያንን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውር የተገኘው ኬኒያዊ ክስ ተመሰረተበት

0
196

አርብ ጥቅምት 9 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኬኒያ ናይሮቢ ከተማ በሚገኝ አንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከ23 ኢትዮጵያውያን ዜጎች ጋር የተገኘው ኬኒያዊ ግለሰብ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ክስ ተመስርቶበታል።

ሞሃመድ ኢሳክ የተባለው ግለሰብ፤ “የውጭ አገራት ዜጎችን በመበዝበዝ እና በማታለል ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ አሳልፏል ወይም ተቀብሏል በሚል በአገሪቱ ሕግ መከሰሱን” ዘ ኢስት አፍሪካ ዘግቧል፡፡

የአገሪቷ ፖሊስ “በአካባቢው በሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሕገወጥ ሰዎች አሉ” በሚል የደረሰውን ጥቆማ መሰረት አድርጎ ባደረገው ምርመራ፤ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የገለጸ ሲሆን፤ በምርመራውም ኢትዮጵያዊያኑን ወደ ታንዛኒያ በመጓዝ ላይ እንደነበረ ማረጋገጡን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡23ቱ ኢትዮጵያዊያን በአንድ ክፍል ውስጥ ታጭቀው እንደተገኙም የገለጸው ፖሊስ፤ በተገኙበት ወቅት ምንም አይነት መታወቂያም ሆነ የጉዞ ሰነድ እንዳልነበራቸውና ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ኬንያ መግባታቸውን ማረጋገጡን አብራርቷል፡፡

በዚህም መሰረት ግለሰቡ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል መከሰሱ በፍርድ ቤቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ተጠርጣሪው በፍርድ ቤቱ የቀረበበትን ክስ ውድቅ በማድረግ በጠበቃው በኩል የዋስትና ጥያቄ አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱም ለተጠርጣሪው 300 ሺሕ የኬኒያ ሽልንግ ዋስትና የፈቀደ ሲሆን፤ ጉዳዩን የፊታችን ጥቅምት23/2016 ለማየት ቀጠሮ መስጠቱን ዘገባው አመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here