በአማራ ክልል መጠለያ ጣቢያ  በሚገኙ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጾታዊ ጥቃት እየተፈጸባቸው መሆኑ ተገለጸ

0
552

ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል በመጠለያ ጣቢያዎች በሚገኙ ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑ ተገልጿል።

በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች ከተለያዩ ቦታዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሸሽተው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ መጠለያ ጣቢያዎች የገቡ ቢሆንም፤ በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ከአምስት እስከ 30 የማይተዋወቁ ሴቶችና ወንዶች አብረው በሚያድሩበት ወቅት በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንደሚፈጸም ነው የተጠቆመው።

በአማራ ክልል ከሚገኙ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ መካከል አንደኛው በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በጎንደር ከተማ አቅራቢያ በአዘዞ ክፍለከተማ የሚገኝ ቀበሮ ሜዳ የተሰኘ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ነው።

በካምፑ ወስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች፤ የሰሜኑ የአገራችን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከትግራይ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በሚከሰት የጸጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የተጠለሉ ሰዎች ናቸው። በአሁኑ ወቅት የሱዳን ስደት ተመላሾችም በካምፑ ውስጥ ይገኙበታል።

በአሁኑ ወቅት በቀበሮ ሜዳ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን፤ እነዚሕ ተፈናቃዮች በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ መኖር ከጀመሩ ከሦስት ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። በአንድ ክፍል የሚኖሩ ሰዎች የማይተዋወቁ  አዛውንቶች፤ ወጣቶችና እና ሕጻናት ናቸው።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር እና በቀበሮ ሜዳ መጠለያ ጣቢያ አማካሪ የሆኑት መቅደስ መለሰ፤ “በቀበሮ ሜዳ መጠለያ ካምፕ ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸው የመጡ አራት ሴቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንደኛዋ ከ18 ዓመት በታች የሆነች ወጣት ነች፡፡” ሲሉ ስለሁኔታው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ወጣቷ የተደፈረችው እዛው በመጠለያ ካምፕ ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች መሆኑን የገለጹት መምህሯ፤ “በመጠለያ ጣቢያው መደፈሯን ለማንም ሳትናገር ደብቃ ቆይታ የህመም ስሜት ሲሰማት የማማከር አገልግሎት ፈልጋ ወደ እኔ መጥታለች” ሲሉ ስለሁኔታው አስረድተዋል።

ወጣቷ ከመደፈሯ በተጨማሪ “በደፈራት ሰው ለማንም ብትናገሪ እገልሻለሁ የሚል ማስፈራሪያ እንደሚደርሳት መናገሯን” ገልጸዋል። የሚያስፈራራትን ሰው እንድትጠቁማቸውና ተገቢውን የህግ ከለላ እንድታገኝ ሲባል ወጣቷን ከህግ ባለሙያ ጋር እንዳገናኟት ጠቁመዋል።

ለሴት ልጆች መደፈር ዋና ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል ተብሎ ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄ የመጠለያ ጣቢያ  መጣበብን እና ተዳብሎ መተኛትን እንደምክንያት አቅርበዋል።

“በመጠለያ ጣቢያው የተለያየ ቤተሰብ በአንድ ቤት ውስጥ ይኖራሉ፤ ሴት ሕጻናቶችን በምግብ እና በአንዳንድ ጥቅማጥቅም አታሎ ሌላ ቦታ ወስዶ ጾታዊ ጥቃት የሚያደርሱም አሉ” ያሉት መቅደስ፤ “ይህን የሚያደርጉት በመጠለያ ጣቢያው የምግብ እጥረት በመኖሩ ደካማ ጎናቸውን ተጠቅመው ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

በአካባቢው ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ሴት ልጆች ከተደፈሩ በኋላ መናገር እንደነውር የሚቆጠር በመሆኑ በርካታ ሴቶች ከተደፈሩ በኋላ ለማንም ሳይናገሩ ደብቀው የሚቆዩ ብዙ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።

ሕጻኗ ወደ እኔ ዘግይታም ቢሆን በመምጣቷ በፒቲሲዲ(PTSD) የተሰኘ የአዕምሮ ሕመም ተጋላጭ የመሆን እድሏ ቀንሷል ሲሉም አስረድተዋል።

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመቀነስ እና ጥቃት አድራሾቹ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የሕግ ባለሙያዎች በደንብ መስራት እንዳለባቸው እና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶችም ሪፖርት የሚያደርጉበት አሰራር ሊዘረጋ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስቀምጠዋል።የቀበሮ ሜዳ መጠለያ ጣቢያ ዋና አስተባባሪ እና ተጠሪ መላኩ ገብሬ “በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ጾታዊ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ወይ?” በሚል ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “በመጠለያ ጣቢያው በርካታ የማይተዋወቁ ሰዎች በአንድ ላይ የሚውሉ እና የሚያድሩ በመሆናቸው ጾታዊ ጥቃት አይፈጸምም ብሎ መደምደም አይቻልም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

“ጾታዊ ጥቃት የሚፈጸምባቸውን ሴቶች ሚስጥራዊ በሆነ መልኩ እንዲያጠኑ የሴቶች ኮሚቴ አዋቅረናል። እነሱ እያጣሩት ነው። ነገር ግን  ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እንዳሉ መረጃ ሰምቻለሁ” ሲሉ ነው ያብራሩት።

በቀበሮ ሜዳ መጠለያ ጣቢያ ከ20 እስከ 30 አባወራ እና እማወራ በአንድ ላይ እንደሚኖሩ ጠቁመው፤ መጠለያው እንዲሁም መጸዳጃ ቤቶቹ የወንድ እና የሴት ተብሎ ስላልተለየ ጾታዊ ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

አክለውም “ሴቶቹ ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸው እንኳ ደብቀው እንደሚቆዩና ለማንም የማያወሩ በመሆናቸው ምን ያክል ሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃት እንደተፈጸመ ማወቅ አልቻልንም” ብለዋል።

የቀበሮ ሜዳ መጠለያ ጣቢያን የሚከታተለው የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ሕጻናት ማሕበራዊ ጉዳይ መምሪያ የሴቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ባለሙያ ጣኢር ኡስማን በበኩላቸው፤ በመጠለያ ጣቢያ እና በከተማው የሚፈጸመው ጾታዊ ጥቃት መባባሱን ጠቁመው፤ ለጥቃቱ መባባስ ፍርድቤቶች በጥቃት አድራሾቹ ላይ ተገቢውን ቅጣት አለመስጠትና ፍትሃዊ አለመሆን እንደምክንያት አንስተዋል።

“ጥቃት አድራሾችን ተከታትለው ከያዙ በኋላ በሕግ ፊት ሲቀርቡ የሚፈረድባቸው የእስራት ቅጣት ከሦስት ዓመት ያልበለጠ መሆኑ ሌሎች ሰዎች ጥቃት እንዳይፈጽሙ አያደርግም” ሲሉም አብራርተዋል።

ለአብነትም ከአጠቃላይ ጾታዊ ጥቃት ጋር አያይዘው ሲገልጹ፤  በጎንደር ከተማ በ2014 እና 2015 ብቻ ከ57 በላይ አስገድዶ መደፈር ተፈጽመዋል ያሉ ሲሆን፤ በከተማዋ ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ኹለት ወንድ ሕጻናቶች ጾታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል፡፡

መኖሪያቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የሕግ ባለሙያ የሆኑት እየሩሳሌም ካሳ በበኩላቸው፤ ቀበሮ ሜዳ ከተሰኘው መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ተሰብስበው የሚገኙ ተፈናቃዮች በሰሜኑ ጦርነት አማካኝነት የተፈናቀሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ናቸው በማለት፤ “በሴቶች እና በወንድ ሕጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጾታዊ ጥቃት ትኩረት ሲሰጠው አይታይም” ብለዋል።

በመሆኑም ጥቃት አድራሽዎቹ የሚገባውን ቅጣት ማግኘት እንደሚገባቸውና ተጠቂዎቹም የሕግ ከለላ ያገኙ ዘንድ አበክረን መስራት ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ከቀበሮ ሜዳ መጠለያ ጣቢያ  በተጨማሪ በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ሽመላኮ በተሰኘ ቦታ በርካታ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን፤ የመጠለያ ጣቢያዎች ጥበት ለጾታዊ ጥቃት መጋለጥ እንደ ምክንያት ሲነሳ ይስተዋላል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here