ረቡዕ ጥቅምት 14 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ፓስታ በዘመናቸው ተወዳጅ ናቸው ያላቸውን ድምፃዊያን በዝርዝር በማስቀመጥ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ ድምፃዊያን በሥማቸው ቴምብር የሚሰይም ስለመሆኑ ገልጿል፡፡
ከወንድ ጥላሁን ገሰሰ፣ አሊ ቢራ ፣መሀሙድ አህመድ እና ኪሮስ አለማየሁ ስማቸው ሲጠቅስ ሜሪ አርምዴ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ አስቴር አወቀ እና እጅጋየሁ ሺባባው ከሴት ድምፃዊያን ዝርዝር ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ማርኬቲንግ ዲፓርትመንት ሃላፊ ስንታየሁ ታደሰ በተለይ ለኤፍ ኤም አዲስ 97.1 እንደገለጹት፤ ምርጫው 7 ቀናትን እንዳስቆጠረና ለ30 ቀን ይቆያል፡፡
የእነዚህን የሙዚቃ ሰዎች ፎቶ በቴምብር መልክ ለማሳተም የተፈለገው ሙዚቀኞችን ለመዘከርና ለዓለም ሕዝብ ለማስተዋወቅ እንደሆነ ነው ስንታየሁ የገለጹት፡፡
ቴምብሮቹ የዓለም የፖስታ ህብረት አባል በሆኑ በ190 አገራት ስለሚበተኑ ለሙዚቀኞቹ የክብር ዶክትሬት የመስጠትን ያህል ክብር አለው ሲሉ ስንታየሁ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም፤ የተመረጡ ሙዚቀኛችን የያዘው ቴምብር በተለያዩ አገራት ሲደርስ ስለሙዚቀኞቹ ሙሉ መረጃ የሚሰጥ ሰነድም አብሮ እንደሚሄድ ተናግረዋል፡፡
ቴምብር ሊታተምላቸው የታሰቡ ሙዚቀኞች ከወንድ 2 ከሴትም 2 በአጠቃላይ አራት ሲሆኑ፤ እነዚህን ሙዚቀኞች ሕዝቡ እንዲመርጥ የኢትዮጵያ ፖስታ 20 ሙዚቀኞችን እጩ አድርጎ አቅርቧል፡፡
ስንታየሁ እንዳሉት ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፖስታ እጩ ያላደረጋቸውና እጩ መሆን አለባቸው ብሎ ያሰበውን ሕዝቡ እንዲጠቁም ዕድል ተሰጥቷል፡፡
ምርጫው ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን፤ በድርጅቱ ቴሌግራም ሕዝቡ ድምጹን መስጠት እንደሚችልም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡



