ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ከሲሚንቶ ግዢ ጋር ተያይዞ በሙስና ወንጀል የተከሰሱት የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የኮንስትራክሽንና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር ተስፋዬ ደሜን ጨምሮ 3 ግለሰቦች ላይ የቅጣት ውሳኔ ተሰጠ።
ፍርድ ቤቱ በሰጠው የቅጣት ውሳኔን በሚመለከት በዐቃቤ ሕግ በኩል ግን ይግባኝ ለማቅረብ የውሳኔ ግልባጭ ተጠይቋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሥም 29 ሺሕ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ከኹለት ፋብሪካዎች ገዝተው፤ ለግለሰቦች በመሸጥ በመንግሥት ላይ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል በማለት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተርን ጨምሮ በአራት ሰራተኞች ላይ ታህሳስ 3/2015 በዋለው ችሎት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸው ነበር።
በአጠቃላይ ተከሳሾች በጥቅም በመመሳጠር ምንም አይነት የግዢ ፍላጎት ሳይኖር በአገልግሎቱ ስም በፃፏቸው ደብዳቤዎች ከዳንጎቴ እና ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድምሩ 29 ሺህ 200 ኩንታል ሲሚንቶ በመግዛት ወደ ተቋሙ ገቢ ሳያደርጉ ገበያ ላይ በመሸጥ 30 ሚሊየን 99 ሺሕ 360 ብር ጥቅም ያገኙ መሆኑን ጠቀሶ ነበር ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበው።
ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸውና በንባብ ከተሰማ በኋላ “ወንጀሉን አልፈጸምንም” ሲሉ የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ፤ ዐቃቤ ሕግ ለወንጀሉ መፈጸም ያስረዱልኛል ያላቸውን ሦስት ምስክሮችን እና በተያያዥ የሰነድ ማስረጃዎችንም አቅርቧል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የምስክር ቃል መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት አንቀጽ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር።
ሆኖም ተከሳሾቹ በተለያዩ ቀናቶች ያቀረቡትን የመከላከያ ማስረጃ የመረመረው ፍርድ ቤቱ 1ኛ ተከሳሽን የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ተቋም የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ም/ዳይሬክተር የሆኑት ተስፋዬ ደሜ፣ በተቋሙ የግዢ ባለሙያ ናቸው የተባሉ ቱጅባ ቀልቤሳ እና ሙስጠፋ ሙሳን በተከሰሱበት ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ጥፋተኛ ብሏቸዋል።
ከተሳሾቹ ጋር ቀደም ብሎ ክስ ቀርቦባቸው የነበረና ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ በችሎቱ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ የነበረው በተቋሙ የኮንስትራክሽን እና ሎጂስቲክስ ግዢ ፋይናንስ ክፍል ኃላፊ አሸናፊ ተስፋዬ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን በተገቢው ተከላክለዋል በማለት በነጻ አሰናብቷቸው ነበር።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት ማቅለያና የቅጣት የማክበጃ አስተያየቶችን መርምሮ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ በተባሉበት አንቀጽ 1ኛ ተከሳሽን በ2 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የወሰነ ሲሆን፤ ቀሪ ተከሳሾችን ደግሞ 1 ዓመት ከ6 ወራት እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።
ዐቃቤ ሕግ ከኹለት ፋብሪካዎች ያለአግባብ በተፈጸመ የ29 ሺሕ 200 ኩንታል ሲሚንቶ ግዢ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ በመንግሥት ላይ ጉዳት ደርሷል ብሎ ክስ ያቀረበ ቢሆንም፤ ችሎቱ ግን ለቅጣት አላማ የወሰደው እያንዳንዳቸው የ700 ሺሕ ብር ጥቅም አግኝተዋል የሚለውን የገንዘብ መጠንን ብቻ ነው።
በዚህ መልኩ በፍርድ ቤቱ በተሰጠው የቅጣት ውሳኔ ላይ እና 2ኛ ተከሳሽ ከተከሰሰበት ክስ ነጻ የተባለበት ብይን በሚመለከት ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ለማቅረብ ግልባጭ መጠየቁም ተገልጿል፡፡



