ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ ፀድቆ ሥራ ላይ መዋሉን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው አስታውቀዋል፡፡
አገልግሎቱ ዜጎች በሚያጋጥሟቸው የሕግ ጉዳዮች የሕግ ድጋፍ ለማግኘት የገንዘብ አቅም ስለሌላቸው ወይም ለጉዳት ተጋላጭ ስለሆኑ ብቻ ፍትህ የማግኘትና በሕግ ፊት እኩል የመዳኘት መብታቸው እንዳይጓደል ታስቦ መዘጋጀቱ ተጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ ሕገ – መንግሥትም እነዚህ መብቶች እውቅና የተሰጣቸው ቢሆኑም፤ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ባልተደራጀና ግልጽ የሆነ ስትራቴጅክ አቅጣጫ ሳይቀመጥለት በተለያዩ አካላት አማካኝነት አገልግሎቱ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንደገለጹት ሚኒስቴሩ በተሰጠው ነጻ የሕግ ድጋፍ ስትራቴጂ የመቅረጽ፣ አፈጻጸሙን የመከታተልና በመስኩ የተሰማሩ አካላትን የማስተባበር ተግባርና ኃላፊነትን መነሻ በማድረግ ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ብሄራዊ ነጻ የሕግ ስትራቴጂን ቀርጾና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ በማፀደቅ ከጥቅምት 13 ቀን 2016 ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡



