ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የባሮ ወንዝ ዳግም ሞልቶ በመፍሰሱ በውሃ ሸሽ እርሻ ሰብል እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጋትሉዋክ ጋች፤ የባሮ ወንዝ ለኹለተኛ ጊዜ ሞልቶ ባስከተለው የውሃ መጥለቅለቅ በተዘሩ ሰብሎችና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
ወንዙን ተከትለው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ከ 4 መቶ ሄክተር መሬት በላይ የተለያዩ ሰብልና አትክልት የማሳ ዝግጅት አድርገው እንደነበር የገለጹት ከንቲባው፤ ነገር ግን ወንዙ ለኹለተኛ ዙር በመሙላቱ በሰብል የተሸፈነ 190 ሄክታርን ጨምሮ በዝግጅት ላይ ያለው ማሳ ሙሉ በሙሉ በወንዙ መዋጡን አብራርተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ከክልሉ ጋር በመሆን ጉዳት የደረሰባቸው አርሶ አደሮችን ለመደገፍ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመው፤ በሰሞኑ በነበረው ከፍተኛ ዝናብ ጉዳት የደረሰበትን የዊቡር ትምህርት ቤት ቀጣይ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰትበት አካባቢውን በአፈር የመደልደል ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።
የዊቡር 1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር በድሉ ጉግሳ በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በጋምቤላ ከተማ የዘነበው ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ አራት የመማሪያ ክፍሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
የመማር ማስተማር ሥራው እንዳይስተጓጎል ጊዜያዊ መፍትሄ በማፈላለግ ባዶ ክፍሎችን እየፈለጉ የመማር ማስተማር ሥራውን እያከናወኑ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የጎርፍ አደጋው በየዓመቱ እንደሚከሰት የጠቆሙት ርዕሰ መምህሩ፤ የሚመለከታቸው አካለት ዘላቂ መፍትሔ ሊያበጁለት እንደሚገባ አብራርተዋል።
በጎርፍ አደጋው ጉዳት የደረሰባቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ የጎርፍ አደጋው ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ በዘሩት ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን አመልክተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በባሮ ዳር እርጥበታማ አፈርን በመጠቀም በቆሎ፣ አሙላ፣ ቲማቲም እና ቃሪያ ዘርተው እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ሰዓት የዘሩት ሰብል ሙሉ በሙሉ መውደሙን ማስረዳታቸውን ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።



