በሶማሌ ክልል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ 24 ሰዎች ሲሞቱ 23 ሺሕ አባወራዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

0
65

ረቡዕ ጥቅምት 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በሶማሌ ክልል በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ 24 ሰዎች ሲሞቱ፣ 23 ሺሕ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ ጎርፍ በሰው፣ በእንሰሳት እና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ነው የክልሉ ባለሥልጣንት ያስታወቁት።

በሶማሌ ክልል የአደጋ መከላከል ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አስተባባሪ የሆኑት በሽር አረብ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ የጎርፍ አደጋው በአጠቃላይ 10 ሺሕ ሄክታር የሰብል መሬት ያወደመ ሲሆን፣ 3 ሺሕ 600 የቁም እንስሳትም መሞታቸው ተገልጿል።

በክልሉ የተከሰተው ጎርፍ ጉዳት ያስከተለው በአብዛኛው በወንዝ ዳርቻ አካባቢ ባሉ ወረዳዎች እንደሆነም ተናግረዋል።“ሸለሌ ዞን፣ አፍዴሪ እና ሊበን ዞኖች በዋነኛነት ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆኑ፤ እስካሁን በ27 ወረዳዎች፣ በ82 ቀበሌዎች እና በሦስት ትልልቅ ከተሞች ጎርፉ መከሰቱ ተገልጿል።

በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ በአጠቃላይ 42 ሺሕ 301 አባወራዎች የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ ወደ 23 ሺሕ አባወራዎች መፈናቀላቸው ተመላክቷል።

እንዲሁም ዝናቡ ከመስከረም ሦስተኛው ሳምንት አንስቶ መዝነብ ከጀመረ ወዲህ በጎርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ምክንያቶች የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተጠቁሟል።

በጎርፉ ምክንያት በመንገዶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በአርሶ አደር ማሠልጠኛ ጣቢዎች እና በሌሎችም መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ አገልግሎት መስጫ ተቋማት እና የተለያዩ መሠረተ ልማት ያሉባቸው አካባቢዎች በአሁኑ ጊዜ በውሃ መዋጣቸውም ተመላክቷል።

በክልሉ የወንዞች መገናኛ በሆኑ አካባቢዎች የውሃው መጠን በከፍተኛ ኹኔታ በመጨመሩ፤ ወንዝ አቅራቢያ ካሉ አካባቢዎች ተሻግሮም ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተገልጿል።

በጎርፍ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች በሌሎች ውሃ በማይደርስባቸው አካባቢዎች ሰፍረው እንደሚገኙ እና ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ደግሞ ተፈናቃዮች በትምህርት ቤቶች ዉስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here