ረቡዕ ጥቅምት 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች የኮሌራ በሽታ መከሰቱን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል፡፡
የዞኑ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሲስተር ፈለቁ መኮነን በዞኑ በተከሰተ የኮሌራ በሽታ እስካሁን 300 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
በበሽታው የተጠቁት በ25 የጤና ተቋማት ተኝተው ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ኀላፊዋ ገልጸዋል።
የኮሌራ በሽታ ታካሚዎችን ለማከም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በክልሉ አማካኝነት እየቀረቡ መሆኑን የገለጹት ኀላፊዋ በቅርቡም ወደ ጤና ተቋማቱ እንደሚሠራጩ አንስተዋል፡፡
የኮሌራ በሽታን በጤና ተቋም ብቻ በማከም መከላከል እንደማይቻል የገለጹት ሲስተር ፈለቁ፤ የበርካታ ተቋማትን እና አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅም አስረድተዋል፡፡
የወልድያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አዲሴ ሰይድ በበኩላቸው፤ የኮሌራ በሽታ የተገኘባቸውን ሰዎች በመለየትና ድንኳን በማዘጋጀት የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
ሆስፒታሉ ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ ችግሮችን ያሳለፈ በመሆኑ የኮሌራ በሽታ ታካሚዎች ቁጥር የሚጨምር ከሆነ፤ የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን ዶክተር አዲሴ መግለጻቸውን ከዞኑ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡



