ጃል ማሮ የተካፈለበት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የሚደረገው ኹለተኛው ዙር የሰላም ውይይት በዳሬሰላም ተጀመረ

0
334

ረቡዕ ጥቅምት 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በፌደራል መንግሥቱ እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል በታንዛንያ ዳሬሰላም ኹለተኛው ዙር የሰላም ውይይት ትላንት ጥቅምት 27/2016 መጀመሩ ተሰምቷል።

በሰላም ውይይቱ ላይ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መሪ ኩምሳ ደሪባ በቅጽል ስሙ ጃል ማሮ በመሳተፍ ላይ እንደሚገኝ አዲስ ስታንዳርድ ጉዳዩን ከሚከታተሉ ኹለት ዲፕሎማቶች አረጋግጫለሁ ሲል ዘግቧል።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት፤ ጃል ማሮ በሦስተኛ ወገን አደራዳሪዎች አመቻችነት በምዕራብ ኦሮምያ ከሚገኝ ጫካ ወደ አቅራቢያው ወደሚገኘው የደንቢዶሎ አየር ማረፊያ እንዲበር መደረጉን ጠቁመው ከዚያም ወደ ድርድሩ ቦታ በተዘጋጀለት ሄሎኮፕተር መጓዙን ተናግረዋል።

በዚህም ሂደት ጃል ማሮ ለመጀመሪያ ግዜ ከፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ፊት ለፊት ለመገናኘት መቻሉም አመላክተዋል።

ባለፉት ሦስት ሳምንታት የፌደራል መንግሥት እና የኦሮምያ ክልል መንግስሥት ከፍተኛ ሃላፊዎች እንዲሁም ኹለት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት ውጤታማ የተባለ የፖለቲካ ውይይቱ መካሄዱንም ዘገባው አመላክቷል።

ውይይቱ ውጤታማ ስለነበር እና በዚህም ምክንያት የፌደራል መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች የተሳተፉበት ውይይት ትላንት ጥቅምት 27/2016 መጀመሩ ተገልጿል።

ከኹለቱም ወገን ከሳምንታት በፊት በተካሄደው በቀደመው የፖለቲካ ውይይት ተካፋይ የነበሩ ከፍተኛ አመራሮች ድርድሩ በስኬት ከተከናወነ ለፊርማ ሥነ ስርአቱ ተካፋይ እንደሚሆኑ ሥማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የዲፕሎማቲክ ምንጭ ጠቁመዋል።ውይይቱን በማመቻቸት ረገድ ኢጋድ ትልቁን ሚና መጫወቱን የጠቆሙት ምንጮች፤ የኢጋዱ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ዋና አወያይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ሚያዚያ 15/2015 የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በተዘጋጀ የሽልማት እና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር፤ መንግሥት ከ“ኦነግ ሸኔ” ጋር በዛንዚባር ከሚያዚያ 17/2015 ጀምሮ ድርድር እንደሚያደርጉ ማስታወቃቸውን ተከትሎ የመጀመሪያው የድርድሩ ሂደት መጀመሩ ይታወሳል።

በመንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል በታንዛኒያ የተካሄደው ድርድር ሳምንት ያክል ከፈጀ በኋላ፤ ከስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉን መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በየፊናቸው ባወጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here