ረቡዕ ጥቅምት 28 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስቀድመው መጥራት አልቻሉም፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን መጥራት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ግን ለተማሪዎቻቸው የደኅንነት ዋስትና እስኪሰጥ ድረስ ከመጥራት ተቆጥበዋል፡፡
በክልሉ የጤና ሳይንስ ተማሪዎችን እያስተማሩ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም አሉ፡፡
የዩኒቨርሲቲውን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር)፤ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ ምክንያት የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱ ተዛብቶበት እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡
በዚህ ዓመት ሦስት ወሰነ ትምህርቶችን ለማስተማር አቅደው እንደነበር የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የተጓተተውን ትምህርት ለማካካስ አስቀድመው በመጥራት ትምህርት ለመጀመር አቅደው እንደነበርም አንስተዋል፡፡
በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በእቅዳቸው መሠረት ተማሪዎችን መቀበል አለመቻላቸውንም ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎችን ከመስከረም 11/2016 ጀምረው ጠርተው እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተማሪዎችን የመቀበያ ጊዜ ማራዘማቸውንም ተናግረዋል፡፡ በቅርብ የተደረገ ጥሪ አለመኖሩንም አስታውቀዋል፡፡
ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ለመምጣት የሚያስችል መንገድ እንደማያገኙ በመረዳት እና ተማሪዎቹም ለመምጣት እንደሚቸገሩ ባስታወቁት መሠረት ጥሪውን ማራዘማቸውን ነው የገለጹት፡፡
በጸጥታው ምክንያት በተፈጠረው የመንገድ መዘጋጋት ተማሪዎችን ለመጥራትም ሆነ የግብዓት አቅርቦት ለማግኘት ፈተና ሆኖባቸው እንደቆየም አስታውሰዋል፡፡ የግብዓት አቅራቢ ነጋዴዎች ግብዓት ለማግኘት ሲቸገሩ መቆየታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተለይም የጤፍ ግብዓት ፈትኗቸው እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ ለገጠማቸው ችግር መፍትሔዎችን በመውሰድ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑንም የገለጹ ሲሆን፤ ሌሎች ችግሮች ተፈጥረው መደናቀፍ ካልተፈጠረ በስተቀር ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ ነንም ብለዋል፡፡
የጸጥታ ኹኔታው አስተማማኝ ከሆነ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዩኒቨርሲቲው ኹሉንም አይነት ዝግጅት አድርጓል ነው ያሉት፡፡
“ተማሪዎች በጉዞም ላይ ሆነ ከገቡ በኋላ የጸጥታ ችግር እንዳይገጥም የሚመለከተው አካል እውቅና እስከሚሰጥ ድረስ እየጠበቅን ነውም” ብለዋል፡፡ የጸጥታ ሁኔታውን የሚመራው አካል እውቅና የሚሰጥ ከሆነ ተማሪዎችን እንቀበላለን ነው ያሉት፡፡
የሰላም ኹኔታው አስተማማኝ ባለመሆኑ የዓመቱን የምግብ ግብዓት በአንድ ጊዜ ማስገባት እንደማያስችልም አንስተዋል፡፡ የገበያ መስመሩ እስካልተደነቃቀፈ ድረስ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉትን ኹሉንም ዝግጅት አድርገናል ብለዋል፡፡ ተማሪዎች በትዕግሥት እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከሰሞኑ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን አይቀበሉም በሚል የተሰራጨው መረጃ ተማሪዎችን ማስደንገጡን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን የማስተማር ፍላጎት እና በቂ ዝግጅት ያደረገ መሆኑን ሊያውቁት ይገባልም ብለዋል፡፡
የመቅደላ አምባ ዪኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ካሳ ሻውል (ዶ.ር) መቅደላ አምባ ዪኒቨርሲቲ ከበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከመስከረም 2016 ጀምሮ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ማዘጋጀት ያለበትን ኹሉ ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
የጸጥታ ችግር ካልሆነ በስተቀር እንደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስቸግር ነገር የለምም ብለዋል፡፡ የሰላም ኹኔታው ከተስተካከለ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ይቀበላል ነው ያሉት፡፡
ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይፈጠር አስቀድመው ሰርተው እንደነበር ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ “የጸጥታ ኹኔታውን አስተማማኝነት ማረጋገጫ ካገኘን ተማሪዎችን ለመጥራት የሚያስቸግረን ነገር የለምም” ብለዋል፡፡
ተማሪዎች በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አይቀበሉም የሚለውን ሀሰተኛ መረጃ በመተው ራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
የሰላሙ ኹኔታ መስተካከል ካሳየ ተቀብለው እንደሚያስተምሯቸው በመረዳት ዝግጅት እያደረጉ እንዲጠብቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡