በኢትዮጵያ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ54 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ተገለጸ

10 ሚሊዮን የሚሆኑት ዓመታዊ መዋጯቸው በመንግሥት ተሸፍኖላቸዋል ተብሏል

0
145

ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ54 ሚሊዮን በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና ውይይት እየተካሄደ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በዚሁ ወቅት፤ በጤናው ዘርፍ ውጤታማ የለውጥ ሥራ መከናወኑን የተናገሩ ሲሆን፤ በተለይም የጤና ተደራሽነትና ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡

አካታችና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳካት ከተቀረጹ ሪፎርሞች መካከል አንዱ የጤና መድህን ስርዓት መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና መድህን ስርዓት በጤናው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እያስገኘ መሆኑንም አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ በበኩላቸው፤ የጤና መድህን ስርዓት ዓላማ ዜጎች አስቀድመው በሚከፍሉት መዋጮ የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ወቅት ያለምንም የክፍያ ስጋት የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻል መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ54 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ 10 ሚሊዮን የሚሆኑት የመክፈል አቅም የሌላቸውና ዓመታዊ መዋጯቸው በመንግሥት የተሸፈነላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ስርዓቱ እንዲጠናከር የመምራትና የመደገፍ ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም ጨምረው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here