“በጦርነት ባለመሳተፋችን ከሥራም ከደሞዝም ታግደናል” የትግራይ ክልል ፖሊሶች

0
236

ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት መካከል በተደረገው ጦርነት አልተሳተፋችሁም በሚል ከሰኔ 21/2013 በኋላ ከሥራም ከደሞዝም ታግደናል ሲሉ 240 የሚሆኑ የትግራይ ክልል ፖሊሶች ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡

የፖሊስ አባላቱ “የፌደራል መንግሥቱ ትግራይ ክልልን ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት በሞያችን ኅብረተሰቡን ስናገለግል ቆይተን፤ ህወሓት መቀሌ በገባ ግዜ ተለይተን ከሥራችን ታግደናል” ሲሉ መናገራቸውን አራዳ ኤፍኤም ዘግቧል፡፡

አባላቱ የተቋረጠው ሥራም ሆነ ደሞዝ እንዲመለስልን ለትግራይ ክልል ጊዜዊ አስተዳደርና ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም ከቀጠሮ ያለፈ ምላሽ አላገኘንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ የመቀሌ ቅርንጫፍ በበኩሉ፤ 240 የሚደርሱ የፖሊስ አባላት ያቀረቡት ቅሬታ ትክክል መሆኑን አረጋግጧል፡፡

የቅርንጫፉ ሀላፊ ፀጋየ እምባየ “ጊዜዊ አስተዳደሩም ሆነ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንን በአካልና በደብዳቤ ብንጠይቅም፤ በቂ ምላሽ ባለማግኘታችን የፌደራል እምባ ጠባቂ ጉዳዩን እንዲከታተል አስተላልፈናል” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም በበኩሉ፤ “ቅሬታው በፌደራል ደረጃ እንዲፈታ ከቅርንጫፍ ቢሮው ጋር ተነጋግረናል፤ ነገር ግን መዝገባቸው ተሟልቶ ባለመቅረቡ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን መጠየቅ አልቻንም” የሚል ምላሽ መስጠቱን ሰጥቷል፡፡

ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮሚሽኑ አማካሪና ልዩ ፅሀፊ ኮማንደር መብርሀቱ በበኩላቸው፤ “ምላሽ የሚሰጡት የበላይ ሀላፊዎች ናቸው” በማለት መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውንም ዘገባው አመላክቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here