ሐሙስ ታህሳስ 04 ቀን 2016(አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የመጀመሪያው የቲንክ ታንክ (Think Tank Group) ቡድን ተቋቁሟል።
የቲንክ ታንክ ቡድኑ የኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሀሳብ አመንጪዎች ከመላው ዓለም በተሰባሰቡ ከፍተኛ ልምድና ዕውቀት ያለቸው ሰዎች ማካተቱም ተገልጿል።
ቡድኑ በዘርፉ የፖሊሲ አተገባበር ሂደት ኃሳብ በመስጠት፣ ልምዶችን በማካፈል፣ የውይይት ባህል በማዳበርና በዘርፉ ቅንጅታዊ አሠራር ለመተግበር ያስችላል ሲሉ የኢፌዲሪ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ይህም የአገሪቱን የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ጥራት ለማስጠበቅ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንደገለጹት ዘርፉ በአሁኑ ሰዓት በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚጠቅም ቢሆንም በሙሉ አቅም ለመስራት የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ያነሳሉ።
ከነዚህም ጥራት ያለው ስልጠና፣ ተደራሽነት፣ የመማሪያ ቁሳቁሶች እጥረት እንዲሁም በቅንጅት የመስራት ሁኔታ ላይ ክፈተት እንደሚታይ አመልክተዋል።
በተጨማሪም በማህበረሰቡ ውስጥ ለቴክኒክና ሙያ ዘርፉ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፤ ያለውን ምልከታ ከፍ ለማድረግ መሰራት እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
እንዲሁም አምራች ዜጋን ለማፍራት ብቁ የሆኑ መምህራን እና ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና ወሳኝ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለአገር ግንባታ የሚያበረክተውን አስተዋጾ በሚገባ ባገናዘበ ሁኔታ ዘርፉ በየትኛው መንገድ ቢመራ ይሻላል የሚለውን የሚጠቁምና፤ በጠቅላላው በዘርፉ ለኢትዮጵያ ሀሳብ የሚያመነጩ ወገኖች እነማን ናቸው የሚለውን የመለየት ስራ ሲሰራ መቆየቱም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የመንግስት፣ የግሉን እና የአጫጭር ስልጠና ሰጪ ተቋማትን ጨምሮ ከ2 ሺህ በላይ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ይገኛሉ።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በኢትዮጵያ በመንግስት እውቅና ተሰጥቶት ፖሊሲ የተቀረጸው 1987 ሲሆን የኢፌዲሪ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት በ2005 መቋቋሙ ይታወቃል።
በፍርቱና ወልደአብ


