የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና ኢትዮ ቴሌኮም  በስደት ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ለማገዝ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

0
450

ረቡዕ ታህሳስ 3 ቀን 2016(አዲስ ማለዳ) የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ውጭ ሀገር ሄደው የሚሰሩ ዜጎች እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩ ወጣቶችን ለማገዝ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

በዛሬው ዕለት በስራና ክህሎት ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው የፊርማ ስነስርዓት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ስለ ስምምነቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ስምምነቱ ከሀገር ውጭ  ሄደው የሚሰሩ ዜጎች በተዘጋጀላቸው ስርዓት(system) የያዙትን የኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርድ ተጠቅመው ገንዘባቸውን ተቀማጭ ማድረግ የሚያስችል እና ካላስፈላጊ እንግልት የሚያድን ነው ተብሏል፡፡

እንዲሁም ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የሚሰጠው ይህ ስምምነት ትልቁ ተግዳሮት የሆነውን፤ የፋይናንስ ችግር የሚፈታ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ስራ ፈጣሪዎችን እንዲሁም ወጣቶችን ለመጥቀም የተዘጋጀው አገልግሎት ለስራ ማስጀመሪያ የሚሆኑ ብድሮችን በቴሌ ብር አማራጮች ለማቅረብ በተጨማሪም የድርጅቶች እና ኤጀንሲዎች የኦንላይን ክፍያን ለማዘመን የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የስራ ፈጠራ ሀሳቦች እንዲጎለብት በወጣት ስራ ፈጣሪዎች የተመረቱ የፈጠራ ስራዎችን በስፋት በመጠቀም ስራ ፈጣሪነትና ኢንቨስትመንት እንዲሳለጥ ያደርጋልም ተብሏል።

በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የዳታ ሴንተር ማዕከላት የማዘመን፣ ቅርንጫፎችን ከማዕከል እርስበእርስ በፈጣን ኢንተርኔት የማስተሳሰር እና የጥሪ የግንኙነት ማዕከል አገልግሎት ለማቋቋም የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን እየደገፈ እንደሆነ እና በቀጣይም የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማበረታታት ድጋፉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ወጣቶችን በማገዝ ለአቅም ግንባታ ስልጠናዎች አስፈላጊ የቴክኖሎጅ ድጋፍ በማድረግ በሀገር ውስጥና በባህር ማዶ ያሉ ዜጎችን እኩል የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻልም ተገልጿል።

በቤተልሄም ይታገሱ

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here