ለ 30 ሺሕ ሰዎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ሊሰጥ ነው

0
528

ከኅዳር 22 እስከ 24 በሚሊኒየም አዳራሽ በሚከናወነው ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን እና ኮንፍረንስ ከ 30 ሺሕ ለሚበልጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ነፃ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገለፀ።

የአዲስ አበባ የግል የጤና ተቋማት አሠሪዎች ማኅበር ባዘጋጀው በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ፣ የልብ እና የደም ግፊት ምርመራ፣ የስኳር፣ የዐይን እና የጥርስ ህክመና እንዲሁም የኤ.ች አይ. ቪ ምርመራ ከአገር ውስጥ የግል የጤና ተቋማት እና ከተለያዩ የውጪ አገራት በመጡ ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ከነፃ ህክምናው በተጨማሪ ለኅብረተሰቡ የጤና ትምህርቶች ይሰጣሉ የተባለ ሲሆን፣ በሦስቱ የኤግዚቢሽን ቀናትም 50 ሺሕ ሰዎች ኤግዚቢሽኑን ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል። ከ 200 በላይ የአገር ውስጥ እና የውጪ የጤና ተቋማት እንደሚገኙም ማኅበሩ አስታውቋል።

የህክምና አገልግሎቱን በከተማዋ በሁሉም አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ሁሉም ወረዳዎች 300 ሰዎች እንዲልኩ ተደርጓል የተባለ ሲሆን፣ ከተጠበቀው ቁጥር በላይ ታካሚ የሚመጣ ከሆነ ከኤግዚቢሽኑ መጠናቅቅ በኋላ ህክምናው የሚሰጥበት መንገድ እንደሚመቻች ማኅበሩ ገልጿል። ከዚሁ ጎን ለጎንም ከህንድ አገር በመጡ የህክምና ባለሙያዎች ለአምስት የልብ ታማሚዎች ነፃ የቀዶ ህክምና እንደሚሰጥ አስታወቋል።

በመንግሥት እና በግል የጤና ተቋማት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ይጠቅማል የተባለለት ኤግዚቢሽኑ፣ ኢትዮጵያን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እና በአገር ውስጥ ያሉ የጤና ተቋማት አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበት እንደሚሆን ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ብቻ ከ 2 ሺሕ 300 በላይ የግል የጤና ተቋማት ያሉ ሲሆን፣ በኤግዚቢሽኑ ላይ አገልግሎታቸውን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን እንደሚወጡ እና ኤግዚቢሽኑ ለተከታታይ አምስት ዓመታት በእየ ዓመቱ እንደሚከናወን ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here