በሃዲያ ዞን ግርዛትን ለማስቀረት ተጀምረው የነበሩ የመከላከልና የንቅናቄ ሥራዎች መቀነስ በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ግርዛት ስርጭት እንዲጨምር አስተዋጾ አድርጓል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገልጿል።
ኮሚሽኑ ታህሳስ 25 2016 በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃዲያ ዞን በሻሸጎ፣ ሶሮና ምዕራብ ሶሮ ወረዳዎች በሴቶች ላይ በሚፈጸም ግርዛት ዙሪያ ባከናወነው ምልከታ ተጎጂዎች ለሚያጋጥማቸው የጤና እክል እየተሰጠ ያለው ድጋፍና ክትትል አጥጋቢ አለመሆን ሴቶች ከዘመናዊ ሕክምና ይልቅ ወደ ጎጂ ልማዳዊ አማራጮች እንዲያዘነብሉ ምክንያት እንደሆናቸው አዲስ ማለዳ ኮሚሽኑ ካጋራው ጽሁፍ ተመልክታለች።
በተመሳስይም በሻሸጎ ወረዳ በማኅበረሰቡ ዘንድ ‘ጨበላ’ በመባል የሚታወቅ የተደጋጋሚ ግርዛት ጎጂ ልማድ በአካባቢው በበጋ ወራት በሁሉም ዕድሜ ክልል በሚገኙ ሴቶች ላይ በስፋት እንደሚፈጸም ተገልጿል።
በዚህ ጎጂ ልማድ የሚያልፉ ሴቶች ከጤና እክል ጀምሮ እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት የሚደርስባቸው መሆኑ በክትትሉ ከተለዩ ግኝቶቹ መካከል መሆናቸውን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
የሴትን ልጅ ግርዛት በዞኑ ለማስቆም በተግዳሮትነት ከተነሱት መካከል ድርጊቱ በድብቅ መፈጸሙ፣ ማኅበረሰቡ ሴትን ልጅ የሚገርዙ ግለሰቦችን መደበቁ፣ በአካባቢው በቂና ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥ የሕክምና አገልግሎት አለመኖሩ አበይት ምክንያቶች መሆናቸው ተጠቅሷል።
እንዲሁም የሚመለከታቸው የፍትሕና የአስፈጻሚ አካላት ተቀናጅቶ አለመሥራት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ሲቪል ማኅበራት ትኩረት ማነስ ሌላው ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል።
ለዚህም የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሠራ ያለውን ሥራ እንዲሁም ይህን ጉዳይ በሚመለከት አፋጣኝ እርምጃዎችን እንደሚወስድ በተለይም ከዞን እስከ ወረዳ በተቋቋሙ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መዋቅሮች ምላሽ እንደሚሰጥ አብራርቷል።
በተጨማሪም የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ “በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት የሴቶችን ክብር የሚነካ፤ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጉዳት የሚፈጥር ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም የሚፈጸሙ ጥቃቶች ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ሙሉ በሙሉ የመሳተፍ ዐቅማቸውን የሚገድብ መሆኑን አስረድተዋል።
ስለሆነም ባለድርሻ አካላት እንደየድርሻቸው ማኅበረሰቡን በማስተማር፣ የወንጀል ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ ለተጎጂዎች አስፈላጊውን የጤና፣ የማኅበረ ሥነ-ልቦና እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ እና በቅንጅት በመሥራት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ ታህሳስ 25 2016 ሃዲያ ዞን በሻሸጎ፣ ሶሮና ምዕራብ ሶሮ ወረዳዎች በሴቶች ላይ በሚፈጸም ግርዛት ዙሪያ ባከናወነው ክትትል፤ የተለዩ ግኝቶች ላይ ከመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት በሆሳዕና ከተማ ውይይት ማድረጉን አስታውቋል።


