የአስፋው መሸሻ የህይወት ታሪክ በጥቂቱ (1959 – 2016)

0
2527

አስፋው መሸሻ ሐምሌ 19፤ 1959 ዓ.ም ከእናቱ ዘነቡወርቅ አሻግሬ እና ከአባቱ አምባሳደር መሸሻ አስፋው በአዲስ አበባ ነው የተወለደው።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በሐረር ከተማ በሚገኘው ቤተልሔም/ ማልቲስ አዳሪ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አስፋው፣ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ አባቱ አምባሳደር መሸሻ አስፋው በሚያገለግሉበት አፍሪካ ህብረት ተልእኮ ወደ ታንዛንያ በመሄዳቸው ከ1972 ዓ.ም  ጀምሮ ቤተሰቡ ኑሮውን በዚያው አድርጎ ነበር። 

አስፋው መሸሻ በታንዛንያ የሁለተኛ ደረጃ እና የኮሌጅ ትምህርቱን በመማር በኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ሊመረቅ ችሏል። በመቀጠል አስፋው ከቤተሰቡ ጋር ኑሮውን በናይሮቢ ኬንያ አድርጎ ከቆየ በኋላ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በሐረር ለተወሰኑ ጊዜያት ቆይቷል። 

አዲስ አበባ በመምጣት ‘ፕሬስ ዳይጀስት’ መጽሄት ላይ ለተወሰኑ ጊዜያት ሰርቷል። በ1992 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኤፋ ኤም ራዲዮ በሆነው ኤፍ ኤም 97.1 “አይሬ” የተሰኘ የመዝናኛ ፕሮግራም ከጓደኛው ከዳንኤል ግዛው ጋር በማቅረብ አንጋፋነትን አትርፏል። 

የዚህ ዝግጅቱ ተደራሽነት ምናልባትም የአስፋው ስም ከተነሳ አይሬን የማያስታውስ ባለማግኘት የተገለጸ ነው። አስፋው መሸሻ በአይሬ የመዝናኛ ፕሮግራም ለ6 ዓመታት ቆይታ ካደረገ በኋላ ለተወሰኑ ጊዜያት በዛሚ ኤፍ ኤም ሲሰራ ቆይቷል። 

ጥር 8 ቀን 1999 ዓ.ም በአንድ ቀን የሚወዳቸው አባቱን መሸሻ አስፋው እና ባለቤቱን ሱዛን አስመላሽን በሞት ያጣበት ቀን ነበር። የአስፋው መሸሻ የህይወቱ ከባድ እና ፈታኝ ጊዜ ይህ ነበር። ከመቀበል ውጭ አማራጭ ያልነበረው አስፋው በወቅቱ የ12 ዓመት ታዳጊ የነበረውን ልጁን ሳምሶን አስፋው (ጃፒ)ን በጥንቃቄ ለማሳደግ የተቻለውን አድርጓል። 

የሚያውቁት ሰዎች የወላጅ አባቱ መሸሻ ስም ከአፉ እንደማይጠፋ ያውቃሉ። እውነት ሲመሰክር “መሸሻ ይሙት” ሲል፤ ሲገረም ደግሞ “በመሸሻ ሞት” ይል ነበር። የልጁን ጃፒ ስምም ሳያነሳ አይውልም።

አስፋው መሸሻ ከ30 ዓመታት በፊት አሁን በህይወት የሌለችው ባለቤቱን ሱዛን አስመላሽ ጋር ጋብቻ መስርቶ የጃፒ አባት ሆኗል። ጃፒ በአሁኑ ሰአት የ29 አመት ወጣት እና ኑሮውንም በአሜሪካ አድርጎ ይገኛል።

አስፋው ወደ አሜሪካ አገር የተጓዘው የ14 ዓመታት በፊት ነበር። በአሜሪካም የኢቢኤስ ቴሌቭዥን ሲመሰረት ከነበሩ መስራች የሚድያ ሰዎች አንዱ ነበር። በወቅቱ “ኑሮ በአሜሪካ” በተሰኘው በተለይ በባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የህይወት ውጣ ውረድ ላይ ባተኮረው መሰናዶው በተመልካቾች ዘንድ ክብር እና ዝና አግኝቷል።  

አስፋው ሙሉ ለሙሉ ኑሮውን አዲስ አበባ ካደረገ በኋላ በእሁድን በኢቢኤስ ፕሮግራም ሲያገለግል የቆየ ባለሙያ ነበር። አስፋው መሸሻ በመዝናኛው ዓለም በጠቅላላ ከ27 ዓመታት በላይ በኢቢኤስ ቴሌቭዥን ደግሞ ለ14 ዓመታት በአገልግሎት ቆይቷል። 

ለሙያው ጥራት ምንም ከማድረግ ወደኋላ አይምልም ሲሉ በህመም ላይ ሆኖም ጭምር በኢቢኤስ ስቱዲዮ ተገኝቶ የባልደረቦቹን ስራ ይከታተልና ያግዝ እንደነበር ይገልጻሉ። የሚያውቁት ሰዎች በበጎነቱ የሚያነሱት አስፋው፤ በቅርቡ ከሚወዳቸው አባቱ የተሰጠውን መኪና ለበጎ አድራጎት ስራ እንዲውል ያበረከተ መሆኑ አይዘነጋም።

አስፋው መሸሻ በጥቅምት ወር 2016 ዓ.ም በገጠመው የጤና እክል በሀገር ውስጥ የተወሰነ ህክምና ከተከታተለ በኋላ ለተሻለ ህክምና ወደ ባህር ማዶ አቅንቶ በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እስከ ቅዳሜ ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ክትትል ሲደረግለት ቆይቶ ከዚህ ዓለም ድካም አርፏል። ሰኞ ጥር 13 ቀን 2016 በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስትያን እንዲያርፍ ሆኗል።

ለዚህ ጽሁፍ ኤቢኤስ ቴሌቭዥን እና ተወዳጅ ሚዲያን በምንጭነት ተጠቅመናል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here