ዜጎች በደህንነታቸው በመንግስት አለመተማመናቸው ስርዓት አልበኝነት እንዳያነግስ ያሰጋል- ኢዜማ

“በምንም መመዘኛ ቢሆን ንፁሀን ዜጎችን ቤተ እምነት ድረስ ገብቶ መግደል ፖለቲካ ሊሆን አይችልም” ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ጥር 16 2016 በጽህፈት ቤቱ በሰጠው መግለጫ ገልጸ።

እንዲህ አይነቱ ድርጊት “ምንም አይነት ግብ የማያሳካ የተራ ሽፍታ የጭካኔ ተግባር ነው” ያለው ኢዜማ፤ በዚህ መልኩ የንፁሀንን ሰላምና ደኅንነት መንጠቅ ቂም ከማትረፍና የመጠፋፋት አዙሪትን ከማክረር ያለፈ አንዳችም ፋይዳ እንደማይኖረው መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

ፓርቲው የተወሰኑ ማሳያዎችን በመጥቀስ “ብቻቸውን አገሪቷ ስላለችበት የሰላምና ደኅንነት ቀውስ ብዙ ነገሮችን የሚጠቁሙ ናቸው” ሲል አሳስቧል። 

በዚህም ምክንያት በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን “የባሰ አታምጣ” ብለው ወደ ፈጣሪያቸውን ከመጸለይ አልፈው መንግሥት ከዚህ አደጋ ዜጎችን መጠበቅ እንደተሳነው በማመን እንቅስቃሴያቸውን ገትተው እንደሚገኙ ጠቁሟል።

ይህ የዜጎች አረዳድ ውሎ አድሮ “የሚጠብቀኝ መንግሥት የለም” የሚለውን ሥሜት እያሰረጸ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣት እና ሥርዓተ አልበኝነትን የሚያነግስ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚችልም ፓርቲው ስጋቱን ገልጿል።

በንጹሀን ዜጎች ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች መካከል በቄለም ወለጋ ዞን፣ ጊዳሚ ወረዳ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ኅዳር 14 ቀን 2016 የታጠቁ ቡድኖች በፈጸሙት ጥቃት በዘጠኝ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ላይ “የጅምላ ግድያ” መፈጸሙን አንስቷል።

እንዲሁም ኅዳር 13 እና 17 ቀን 2016 በአርሲ ሀገረ ስብከት በሚገኙ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን ላይ በተፈጸመ ጥቃት 36 ሰዎች፤ በተመሳሳይም ታህሳስ 2 ቀን 2016 በሆሮ ጉድሩ ወለጋ አሙሩ ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት 13 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ኢዜማ አስታውሷል።

በተጨማሪም ታኅሳስ 20 ቀን 2016 በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ለገበንቲ በተባለ ሥፍራ የታጠቁ ኃይሎች በአንድ ተሽከርካሪ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ 13 ሰዎች ታፍነው የተወሰዱ ሲሆን በተሸከርካሪው ውስጥ የነበሩት ሰዎች የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓልን ታድመው ሲመለሱ የነበሩ ዜጎች መሆናቸውንም ጠቁሟል።

“መንግሥትን ለማስገደድ ሲባል ንፁሀንን ሰለባ ማድረግ ከህሊናም ከህግም ውጪ የሆነ ከሥልጡን አስተሳሰብ የተፋታ ዘመኑን የማይዋጅ የትግል ስልት ነው” ሲልም የፖለቲካ ድርጅቱ አጽንዖት ሰጥቷል። 

መንግሥት ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑንና በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ብዙ የጦር መሳሪያዎችን በፍተሻ እንደሚያገኝ በተደጋጋሚ የሚነገር ሲሆን፤ የሽብር ሴራዎች መክሸፋቸውም የየዕለት የፖሊስ ተቋማት ዜና ቢሆንም ዛሬም ድረስ የዜጎች ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ መልኩ እየተጠበቀ አለመሆኑን መንግሥት ባይናገርም ከላይ ከፍ ብለው የተጠቀሱት ማሳያዎች እና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች በራሳቸው ማሳያ ናቸው ተብሏል።

መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ “እጅና እግሩን አጣጥፎ ተቀምጧል” ብሎ መደምደም ባይቻልም፤ ዜጎች ዛሬም በሰላም ወጥተው መግባት ያለመቻላቸው እንቆቅልሽ ግን ላለፉት አምስት ዓመታት ሳይፈታ መዝለቁ በእጅጉ አሳሳቢና፤ ደግሞም በርካታ ጥያቄዎችንም የሚፈጥር መሆኑ ፓርቲው በመግለጫው አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ መንግሥት ሰላምና ደኅንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር የተሳነው ለምን ይሆን በማለት የአቅም ማነስ፣ ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አለመስጠት፣ የአመራር (Security Leadership) ችግር፣ የፀጥታ ባለሞያዎች የብቃት ክፍተት፣ የቁርጠኝነት ችግር፣ የአደረጃጀት ችግር አልያም ደግሞ ከሕዝብ ጋር በሚገባ ተቀናጅቶ ያለመሥራት ክፍተት ስለመሆናቸው በመግልለጫው ጠይቋል።

ፓርቲው ምክንያቱ “ከላይ ከተጠቀሱት ጥያቄዎች አንዱ ወይም ሁሉም ሊሆኑ እንደሚችሉ”ገልጾ አሁን ያለው ፖለቲካ የቆመበት መሰረት ሰላም የሚነሳ መሆኑም ተጨማሪ ችግር እንደሆነ አንስቷል።

በየቦታው ከሚታዩ ግጭቶት ጋር ተያይዞ “በዋነኝነት የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ከእውነት ጎን በመቆም ማህበረሰቡን የማገልገል ሙያዊ ግዴታችሁን ችላ ብላችሁ የመንግሥት ልሳን ብቻ በመሆን ዜጎች ትክክለኛውን መረጃ ማግኘት እንዳይችሉ ስላደረጋችሁ ከሽብር ዜና ነጋዴ የማህበራዊ ሚዲያ ሸቃጮች ጋር እየተባበራችሁ መሆኑን ልትገነዘቡት ይገባል” ሲል ኢዜማ ተችቷል። 

በሌላ በኩል በመንግስት በኩል መደበኛ አሠራር መስሎ የቀጠለው ሕገ ወጥ የጅምላ እስርና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው ማለቱን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።

መንግስት የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎችን ጨምሮ የሌሎች ፓርቲዎችም በተለያዩ ጊዜያት አባላቶቻቸው እየታሰሩ፣ ንብረቶቻቸው እየተዘረፈ እና አፈና እየተፈጸመባቸው መሆኑንም መግለጫው አመላክቶ ይህ አካሄድ “መድብለ ፓርቲ ሥርዓትን ለመገንባት እንቅፋት የሆነ እና በሀገራችን መግባባትን ሳይሆን መቃቃርንና መካረርን ሊያባብስ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል” በማለት አሳስቧል።

ፓርቲው በመግለጫው በትግራይ ክልል ስለተከሰተው ድርቅና ረሀብ በተመለከተ የፌደራሉ መንግሥት ለችግሩ እውቅና ሰጥቶ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ጉዳዩን ቁጥሮች ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በማድረግ ከክልሉ አስተዳደር ጋር እሰጣ እገባ መግባቱን በመግለጽ፤ ጉዳዩን የቁጥር ጨዋታና የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ ከማድረግ ይልቅ ለረሀብ አደጋና ለሞት የተጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ አስቸኳይ ሀገርአቀፍ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥቷል። 

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል እየተደረገ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በሚከናወኑ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች በተለይም በድሮን የሚደረጉ የአየር ላይ ጥቃቶች ንፁሀን ዜጎች ሰለባ እየሆኑ መሆኑንም ገልጿል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል “የድሮን አውሮፕላኖች የመርዝ ጋዝን በመጠቀም” በሠላማዊ ሰዎች ሰፈሮች ላይ የመንግስት ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት የበርካታ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ የሠላማዊ ዜጎች ንብረት ወድሟል ሲል ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከቀናት በፊት ባወጣው  መግለጫ መግለጹ አይዘነጋም።

ኢዜማ መንግሥት በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ በሚገባ እንዲመረምር፣ የዜጎች ሰላምና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ሊጠበቁ ያልቻሉበትን ምክንያቶች በአስቸኳይ እንዲለይና እርምጃዎችን እንዲወስድ ጠይቋል።

መንግሥትም ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን አክብሮ ሊያስከብር ይገባል ያለው የፖለቲካ ፓርቲው “በተለይም የፖሊስ አባላት ሕግን በማክበር ብቻ እንድትንቀሳቀሱ እንዲሁም ምንጊዜም ቢኾን ኃላፊነታቸው የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ እንጂ ማስፈራራትና ማስደንበር አለመኾኑን” በአጽንዖት ገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here