“እኔንም ስሙኝ” መራር የወሲብ ጥቃት ታሪኮች እና መፍትሔዎቻቸው

0
2151

አሁን የምንገኝበት ሳምንት “እኔንም ስሙኝ” በሚል መፈክር የፆታዊ ጥቃት ሰለባዎች ታሪካቸውን እንዲናገሩ ዓለም ዐቀፍ ዘመቻ እየተደረገ ያለበት ሳምንት ነው። ሲያኔ አንለይ እና በፍቃዱ ኃይሉም የበይነመረብ ዳሰሳ በማዘጋጀት፣ የጥናት ሰነዶችን በማገላበጥ እና ባለሙያዎችን እንዲሁም ደግሞ ባለታሪኮችን በመጠየቅ ሐተታ ዘ ማለዳን አዘጋጅተዋል።

ፅናት መንግሥቱ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል እውነተኛ ሥሟ የተሸሸገ፣) በደብረ ብርሃን ከተማ ዳኛ ሁና እየሠራች የምትገኝ ሴት ናት። ይሁን እንጂ ዛሬ ላይ ለመድረስ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጣ ማሸነፍ ነበረባት። ከነዚህ ፈተናዎች ሁሉ የከፋው ግን የተደፈረችበት ቀን ነው። ፅናት የ8ኛ ክፍል ተማሪ እያለች ወዳጆቿ ካስተዋወቋት ሰው ጋር (የፍቅር ያልሆነ) ጓደኝነት ትመሠርታለች። ከዕለታት ባንድ ቀን ከጓደኞቿ ጋር እዚህ ሰው ቤት ሔዳ የእንቅልፍ ኪኒን በለስላሳ መጠጥ አጠጥተዋት እንዳደረች ወደኋላ ተመልሳ ታስታውሳለች። ጠዋት ሰውየው ቤት ከእንቅልፏ ስትነቃ ነበር የሆነውን ሁሉ ያወቀችው። ፅናት ከአባቷ ጋር ብቻ ነው የምትኖረው። በዚህ ሁኔታ ከአራት ወራት በኋላ ማርገዟን ታውቃለች። በዚህም ምክንያት በጣም የተበሳጨው አባቷ ደፋሪዋን ለመክሰስ ቆርጦ ይነሳል። ይሁን እንጂ በሽምግልና ብዛት ሰውዬው በካሣ መልክ የፅናትን የትምህርት ወጪ እና የልጇን ማሳደጊያ ወጪ እንዲሸፍን ተደርጎ ነገሩ ፍርድ ቤት ሳይሔድ ቀርቷል። ሆኖም፣ ፅናት እስከዛሬም ድረስ ለክስተቱ ተወቃሽ የምታደርገው ራሷን ነው። “መጠንቀቅ ነበረብኝ” በማለት ታሪኳን ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች።
ሌላኛዋ በአንድ ወቅት የደረሰባትን የፆታ ጥቃት የተሻገረችው ቦንቱ ባይሳ (እሷም ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ሥሟ ተሸሽጓል፣) የ28 ዓመቷ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናት። ጥቃቱ የደረሰባት ገና የ7 ዓመት ለጋ ሕፃን እያለች በአጎቷ ልጅ፣ በገዛ አልጋዋ ላይ ነበር። ቦንቱ ታሪኳን ስትናገር “ሁሉንም ነገር አስታውሳለሁ፤ እሱ ሲነካካኝ ሰውነቴ እንዴት ይሸማቀቅ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ለማንም መናገር አልቻልኩም፤ ምክንያቱም የሆነ ጥፋት ነገር እንደሆነ ገብቶኛል። በዚያ ላይ ያደረገኝን ነገር ለመናገር የሚያስችል ቃላቱ አልነበሩኝም። የአጎቴ ለጅ አሁንም ድረስ እኛ ቤት ቤተኛ ነው፤ ነገር ግን የቤተሰብ ግንኙነታችንን ላለማበላሸት ስለማልፈልግ ምንም ነገር እንደማላስታውስ ዓይነት ነው የማስመስለው። ይህ የሆነው በወላጆቼ ቸልተኝነት እንደሆነ አውቃለሁ። ሊጠብቁኝ ይችሉ ነበር ግን አልሆነም። የዚህ ገጠመኝ ጠባሳ አሁንም ድረስ ሕይወቴን፣ የፍቅር ግንኙነቴን እና የወሲብ ሕይወቴን ያውክብኛል፤ ድንጉጥ ነኝ፣ እፈራለሁ” ትላለች። የፅናት እና የቦንቱ ታሪክ የብቻቸው አይደለም። በርካታ የኢትዮጵያ እና የቀሪው ዓለም ሴቶች በተለያዩ ደረጃዎች የወሲብ ጥቃቶችን እና ትንኮሳዎችን የኑሯቸው አንድ አካል አድርገው እየኖሩት ነው።
በየዓመቱ ከኅዳር 16 እስከ ታኅሣሥ 1 የሚዘልቅ ዓለም ዐቀፍ፣ የሴቶች ጥቃትን የሚቃወም ዘመቻ አለ። የዘንድሮው ዓለም ዐቀፍ ዘመቻ መሪ መፈክር “እኔንም ስሙኝ” (እኛም ለዚህ ሐተታችን ርዕስ አድርገን መርጠነዋል) የሚል ነው፤ መሪ ቃሉ የተመረጠው እንደ ፅናት ላሉ እና በደላቸውን አፍነው ራሳቸውን እንደጥፋተኛ ሲወቅሱ የኖሩትን ሴቶች እንዲናገሩ ዕድል በመስጠት ነው። አዲስ ማለዳ ጋዜጣም፣ ከዓላማዎቿ አንዱ “የዜጎች ልሳን” መሆን ነውና፥ ይህንን ዘመቻ የበይነመረብ ዳሰሳ (‹ኦንላይን ሰርቬይ›) በማካሔድ ተቀላቅላለች። በዚህ መሠረት፣ ‹የወሲብ ትንኮሳ ምንድን ነው? የችግሩ ጥልቀት ምን ያህል ነው? መንስዔው እና መፍትሔውስ?› ለሚሉት ጥያቄዎች ውይይት ጋባዥ አጀንዳዎችን አንስታለች።
የወሲብ ትንኮሳ ወይም ጥቃት ምንድን ነው?
“ለከፋ” መንገድ ላይ በተለይ ወንዶች ሴቶች ላይ የሚሰነዝሩት የቃላት ትንኮሳ ነው። ይሁን እንጂ እንደመተዋወቂያ መንገድ ወይም እንደፍቅር ጫወታ የሚቆጥሩት ሰዎች በርካታ ናቸው። አዲስ ማለዳ ባዘጋጀችው የበይነመረብ ዳሰሳ ላይ መልስ ከሰጡ ሴቶች መካከል ፆታን መሠረት ያደረገ ትንኮሳ “ለፍቅር ጫወታ ሲባል እንደሚደረግ” የመለሱ አሉ። ለመሆኑ የወሲብ ትንኮሳ ወይም ጥቃት የሚባሉት ምን ዓይነት ድርጊቶች ናቸው? አንድነት እና ልዩነታቸውስ ምንድን ነው?
“ፆታዊ ጥቃት ማለት ፆታን መሠረት አድርጎ የሚፈፀም የአካልም ሆነ የሥነ ልቦና ጥቃት ነው” ይላሉ የሕግ ባለሙያዋ ሜሮን አራጋው (በአዲስ አበባ መስተዳድር የሴቶች እና ሕፃናት ቢሮ ምክትል ኃላፊ)። አክለውም “ወሲባዊ ትንኮሳ የምንለው ከፆታዊ ጥቃቶች መካከል አንዱን ነው። ወሲባዊ ጥቃት እስከ አስገድዶ መድፈር የሚደርስ አንዱ ነገር ግን ብቸኛው ያልሆነ አካላዊ የፆታ ጥቃት ዓይነት ነው፤ ነገር ግን የወሲብ ብዝበዛ፣ በሴትነታቸው በወሲብ ሥራ እንዲሰማሩ መነገድን ይጨምራል። ወሲባዊ ጥቃት ስንል አንድ ጊዜ ሊፈፀም የሚችል አስገድዶ መድፈር ነው። የወሲብ ትንኮሳን ግን ስናየው ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሆኖ የግድ አስገድዶ መድፈር ላይፈፀም ይችላል።”
የስርዓተ ፆታ ጉዳዮች ባለሙያዋ እና የእኩል ኢትዮጵያ አጋር መሥራች የሆኑት አብነት ጣሰውም በተመሳሳይ በትንኮሳ እና ጥቃት መካከል የጎላ ልዩነት እንደሌለ ይናገራሉ። “መተንኮስ እና መጠቃት የሚያመሳስላቸውም የሚለያቸውም ነገር አላቸው። አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ያልተፈለጉ ድርጊቶች መሆናቸው ሲሆን፣ የሚለያቸው የድርጊት ደረጃቸው ነው” ይላሉ። “ትንኮሳ ገና ወደ ተግባር ያልተሻገረ ሲሆን፣ ጥቃት የሚባለው ግን አካላዊ ሆኖ ሲገኝ ነው።”
ሜሮን “ወሲባዊ ትንኮሳ ስንል የፍቅርን፣ የትዳርን፣ ወይም የወሲብን ጥያቄ ተከትሎ (ሴት ልጅ ላይ ስለሆነ በብዛት የሚፈፀመው) ‹እምቢ› ወይም ‹አልፈልግም› በማለቷ የሚደርስባት ጥቃት ወይም ትንኮሳ ነው። ይህም መከታተል ሊሆን ይችላል፣ ማስጨነቅ፣ ማስፈራራት፣ መደብደብ፣ መከታተል፣ መጎንተል፣ ከዚያ ደግሞ ጥግ ሲደርስ ነፍሷን ማጥፋት፣ አካሏን ማጉደል፣ አስገድዶ መድፈርም ይከተላል። ነገር ግን መነሻው ከ“ፍቅር”፣ “ትዳር ”፣ “ወሲብ ” ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው” ይላሉ።
በጥቅሉ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት በቃል፣ በምልክት፣ በድርጊት የሚገለጽ፣ ፆታን መሠረት ያደረገ፣ በቤት ውስጥ፣ በመንገድ ላይ፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በመዝናኛ ሥፍራ ወይም ሌሎች ቤቶች የሚፈፀም ያልተፈቀደ የሥነ ልቦናዊም ይሁን አካላዊ ጫና እንደሆነ ሁለቱም ባለሙያዎች ይስማማሉ።
ወሲባዊ ትንኮሳ “በንግግር፣ በማስፈራራት፣ ‹እወድሻለሁ፤ የኔ ሁኚ› ወይም ‹ከኔ ጋር ግንኙነት ፈፅሚ፣ የትምህርት ‹ግሬድ› እሰጥሻለሁ›፣ ወይም ‹የሥራ ዕድገት እሰጥሻለሁ› የሚል አስጨናቂ ሁኔታ የሚፈጥር ባሕሪም አለው። በተጨማሪም፣ ወሲባዊ ትንኮሳ በምልክትም ይገለጻል፤ አፍጥጦ ማየት፣ መጥቀስ፣ አካላዊ ምልክት በማሳየት ማስጨነቅ። ደብዳቤ ደብተሯ ውስጥ ጽፎ ማስቀመጥ፣ ባጥር ወይም በበር ሥር መልዕክት ማስቀመጥ… አስጨናቂ ሁኔታ በሚፈጥር ሁኔታ እሷ እምቢ ማለት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የሚቀጥል ክትትል እና ውትወታ፣ እስከሞት እና አካል መጉደል እንዲሁም ደግሞ አስገድዶ መድፈር የሚደርስ መነሻው ግን ‹እንዲህ ካደረግሽ፣ እንዲህ አደርግልሻለሁ› ወይም ‹እንዲህ ካላደረግሽ፣ እንዲህ አደርግሻለሁ› ብሎ በማስፈራራት የሚጀምር ነው።”
አብነትም በተመሳሳይ የወሲብ ጥቃትን “ትንንሽ” እና “ትልልቅ” እያሉ መለየት የተለመደ እንደሆነ ይናገራሉ። እንደባለሙያዋ “ትንንሽ” የሚባሉት ጥቃቶች ናቸው “ለትልልቆቹ” መሠረት የሚጥሉት።
ለሴቶች “አደገኛ”
የተባበሩት መንግሥታት በሚያወጣው የፆታዊ አለመመጣጠን መለኪያ ኢትዮጵያን ከ164 አገራት 121ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ይህንን እና ሌሎችም ከስርዓተ ፆታ ጋር የተያያዙ አድልዖዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ከኅዳር 18 እስከ 20፣ 2011 ድረስ ለሁለት ቀናት የቆየ የበይነመረብ ዳሰሳ አድርጋ ነበር። ለዳሰሳው የቀረበውን መጠይቅ 252 መላሾች ሞልተውታል። መጠይቁ ላይ እንዲሳተፉ የተጋበዙት ሴቶች ብቻ በመሆናቸው መላሾቹም ሴቶች ናቸው ተብሎ ይታመናል፤ በውጤቱም 56.8% የሚሆኑት መላሾች የሚኖሩበትን አካባቢ ወይም ከተማ ከፆታዊ ደኅንነት አኳያ “ባመዛኙ አደገኛ” ወይም “በጣም አደገኛ” ነው ሲሉ መልሰዋል።
የችግሩን ጥልቀት ለማሳየት በቃል ወይም በአካል፤ በመንገድ ላይ ወይም በሥራ ቦታ እና በመዝናኛ ሥፍራ እንዲሁም በሳይበር ላይ የሚገጥማቸውን ትንኮሳ በምን ያህል ዕድሜያቸው እንደሚጀምር እና ስንቶቻቸውን እንደሚገጥማቸው ለማወቅ በመጠይቁ ላይ ለቀረቡ ጥያቄዎች ሲመልሱ፣ 90.5 በመቶ የሚሆኑት መላሾች ፆታን መሠረት ያደረገ ትንኮሳ ከዚህ በፊት ደርሶባቸው እንደሚያውቅ ተናግረዋል። ከነዚህ ውስጥ 61.7 በመቶዎቹ ከ15 ዓመት ዕድሜ በታች እያሉ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የፆታ ትንኮሳ የደረሰባቸው። በድምሩ 89.5 በመቶ የሚሆኑት መላሾች ከ19 ዓመት ዕድሜ በታች ሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ የፆታ ትንኮሳ እንዳስተናገዱ ተናግረዋል። መሰል ትንኮሳ “ለመጨረሻ ጊዜ ያስተናገድሽው መቼ ነበር?” በሚል ላቀርብነው ጥያቄ ምላሽ ከሰጡ 223 መላሾች ውስጥ 16 በመቶዎቹ “ዛሬ” በማለት መልሰዋል፤ በዚህ ሳምንት፣ በዚህ ወር፣ ወይም በዚህ ዓመት በማለት የመለሱት ደግሞ በቅደም ተከተል 17.5፣ 14.3 እና 14.3 በመቶ ናቸው።
ከዚህም በላይ “ተደፍረሽ ታውቂያለሽ?” በሚል ላቀረብነው ጥያቄ ከጠቅላላ (252) መላሾቹ ውስጥ 20.2 በመቶ የሚሆኑት “አዎ” ሲሉ መልሰዋል፤ ምንም እንኳን ቁጥሩ የተጋነነ ቢመስልም እኛ ግን እውነታውን ያሳያል ብለን እናምናለን።
ከቤት ወዴት ይሸሻል?
የተባበሩት መንግሥታት መግለጫን ጠቅሶ ታይም መጽሔት በዚህ ሳምንት እንደዘገበው በዓለማችን “ቤት” ለሴቶች በጣም አደገኛው ሥፍራ እንደሆነ ጠቅሷል። መግለጫው እንደሚያትተው በዓለማችን ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ከተገደሉ 87 ሺሕ ሴቶች ውስጥ 58 በመቶዎቹ የተገደሉት በቤታቸው ውስጥ፣ በፍቅር አጋራቸው ወይም የቤተሰብ አባላቸው ነው። ይህ ደግሞ በአፍሪካ የበለጠ የከፋ እንደሆነ ተገልጿል።
ታሪኳን ያጫወተችን ቦንቱ መሰል ሕፃናት እና አዋቂ ሴቶች ጥቃት የሚደርስባቸው የቤተሰብ አባል በሆኑ ወይም የቅርብ ሰዎች በሚባሉ ነው። ቦንቱ ስለዚህ ጉዳይ ስትናገር ማኅበረሰቡም ይሁን ትምህርት ቤቶች ፈቃድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያስተምሩም። “አይሆንም ማለት፣ አይሆንም ማለት ነው”። ነገር ግን በባሕላችን “ሴት ልጅ አልፈልግም ስትል እየተግደረደረች እንደሆነ ነው የሚታመነው”።
በኢትዮጵያ ለምሳሌ ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ የሚፈፀሙት አካላዊ፣ ስሜታዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ደረጃ ከፍተኛ እንደሆነ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በ2008 ያደረገው ጥናት ያሳያል። ዕድሜያቸው ከ40 እስከ 49 በሆኑ ሴቶች ላይ የተደረገው ይኸው ጥናት እንደሚያሳየው 38 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ከነዚህ ጥቃቶች አንዱ ተፈፅሞባቸዋል። በተመሳሳይ 45 በመቶ የሚሆኑ ቀድሞ ትዳር ውስጥ የነበሩ እና 36 በመቶ የሚሆኑ አሁንም ትዳር ውስጥ ያሉ ሴቶች እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል። ጥቃቱ በኦሮሚያ 39 በመቶ፣ በሐራሪ 38 በመቶ እና በአማራ ደግሞ 37 በመቶ ደረጃ አለው።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሴቶች መብት ተሟጋቿ እና የሕክምና ባለሙያዋ ዶ/ር ሠላማዊት አድማሱ በቀብሪዳሃር (ሶማሊ ክልል) ለሁለት ዓመታት ሲሠሩ የገጠማቸውን ባጭሩ ተናግረዋል። “ሴቶች እና ልጃገረዶች በፆታዊ ጥቃት ወለድ በሽታዎች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂ ናቸው። እንደ መደፈር ያሉ ጥቃቶች የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ አካላዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች ያስከትላሉ። ፊስቱላ፣ ኤች አይ ቪ እና ሌሎችም በወሲብ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች የተደፈሩ እና የተገረዙ ሴቶችን ተጋላጭ ያደርጓቸዋል። ተደፍረው ላልታቀደ እርግዝና የተዳረጉም ብዙ ናቸው። የሥነ ልቦና ቀውሱም ቢሆን ቀላል አይደለም፤ በሰብኣዊነት ላይ እምነት ማጣት እና ራስን ወደ ማጥፋት የሚያደርስ ጭንቀት የመፍጠር አቅም አለው።”
“ምስክር የለኝም”
በበይነመረብ ዳሰሳችን ተሳትፈው “ተደፍሬ” ወይም “ያለፈቃዴ ተገድጄ ወሲብ እንድፈፅም ተደርጌ አውቃለሁ” ሲሉ መልስ ከሰጡት መካከል ስለደረሰባቸው በደል ለፖሊስ ወይም ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተናግረው እንደሆነ ላቀረብንላቸው ጥያቄ የተሰጠው ትልቁ (54%) መልስ “ለማንም አልተናገርኩም” የሚል ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ለፖሊስ ተናግረናል ያሉት መላሾች ሁለት ብቻ ናቸው። የወሲብ ጥቃት ደርሶባቸው ለነበሩት እነዚህ መላሾች ወደ ፖሊስ የማይሔዱበትን ምክንያት ስንጠይቅ “ፍርሐት” እና “ሐፍረት” የሚሉት መልሶች ተደጋጋሚ ምላሾች ነበሩ።
ስለዚህ ጉዳይ እንዲያብራሩልን የጠየቅናቸው የስርዓተ ፆታ ባለሙያዋ አብነት “ተጠቂዋን መልሶ የመውቀስ (‹ቪክቲም ብሌሚንግ›) ባሕል የተንሰራፋ እንደሆነ በዩንቨርሲቲ የስርዓተ ፆታ ጉዳዮች ሥራ ሲሠሩ ማስተዋላቸውን እየጠቀሱ ይናገራሉ። “በአንድ በኩል የሕግ ከለላ ስለሌለ፣ በሌላ በኩል የሕግ ከለላ በሚኖርበት ጊዜ ደግሞ የጥቃቱ ባሕሪ ሰው በሌለበት የሚፈፀም በመሆኑ ማስረጃ ማቅረብ ስለሚቸግር፣ እንዲሁም የማኅበረሰቡ ንቃተ ኅሊና ተጠቂዋን የሚወቅስ ስለሆነ ‹ይቅርብኝ› ብላ ሴቷ ጥቃቷን ችላ ትቀመጣለች” ብለዋል። የበይነመረብ ዳሰሳው ላይ ከተሳተፉ መላሾች አንዷ “ምስክር የለኝም” ስትል የገለጸችውም ይህንኑ ነው። ሌላዋ መላሽም በተመሳሳይ “ማንም እንደማያምነኝ እርግጠኛ ስለሆንኩ፣ እሱ ብዙ ሰው የሚያከብረው ሰው ስለሆነ፣ ማስረጃም ስለሌለኝ፣ እሱ ሥልጣን ያለው ሰው ስለሆነ፥ ብናገር የባሰ ይመጣብኛል ብዬ ዝም አልኩ” ትላለች።
ብዙዎቹ ምላሾች “ፈርቼ”፣ “አፍሬ”፣ “የሚያምነኝ ሰው አላገኝም ብዬ” የሚሉ መሆናቸው ባሕላችን የወሲባዊ ትንኮሳ ሰለባዎችን እንደጥፋተኛ የሚቆጥር፣ የሚያሽቅቅ እና እነርሱኑ መልሶ የሚወቅስ መሆኑን ከማመላከቱም በላይ ለዚህ ባሕላዊ ድክመት በቂ ከለላ እንደሌለው የሚያሳይ ነው።
“እሸት እና ቆንጆ አይታለፍም”
እሸቱ ድባቡ “ተባእታይ አገዛዝ በኢትዮጵያ፤ ችግሩና የመፍትሔው መንገድ” በሚል ርዕስ ጽፈው ሰኔ 1997 ባሳተሙት መጽሐፋቸው በስርዓተ ፆታ አድሎዓዊነቱ ስለሚታወቀው የኢትዮጵያ ስርዓተ ማኅበር ብዙ ሐተታዎችን አስቀምጠዋል። በተባእታይ አገዛዝ ውስጥ ባለው ወሲባዊ እና ሥነ ተዋልዷዊ ግንኙነቶች ሴቶች ለወንዶች ፍላጎት ማሟያ ተደርገው እንደሚታዩ በተነተኑበት ምዕራፍ የወሲብ መብት ምን እንደሆነ ገልጸዋል። እንደእሸቱ አገላለጽ “የወሲብ መብት ሲባል መጀመሪያ በገዛ አካል ላይ ባለሙሉ ሥልጣን የመሆን ሰብኣዊ መብትን ይጠይቃል፤ ቀጥሎም ከማን ጋር፥ መቼና እንዴት ተራክቦ መፈፀም እንዳለበት በራስ ብቻ የመወሰን ነጻነት ማለት ነው።” ይሁን እንጂ “እሸት እና ቆንጆ አይታለፍም” የሚለው ተረትና ምሳሌን የፈጠረው ባሕል እንደሚያስረዳው ሴቶች የራሳቸውን የወሲብ መብቶች በራሳቸው መወሰን አይችሉም።
እሸቱ አክለው ሲያስረዱም “የኢትዮጵያ ወንድ ሴቷን ለእርሱ የተፈጠረች እንስሳ ወይም መሣሪያው፣ የግል ንብረቱ ወይም እንዳሻው ሊጠቀምባት የሚችል አገልጋዩ አድርጎ ይወስዳታል።” ይህንን መሰል አስተሳሰብ ባለበት ባሕላዊ ሥሪት ውስጥ ሆኖ ወሲባዊ ጥቃትን መከላከል አስቸጋሪ ይሆናል።
“ሕጉም፣ አፈፃፀሙም ችግር አለው”
በኢትዮጵያ ሴት ጠበቆች ማኅበር ለዓመታት ከሠሩ በኋላ በቅርቡ የአዲስ አበባ ሴቶች እና ሕፃናት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው የተሾሙት ሜሮን አራጋው “ወሲባዊ ትንኮሳ (‹ሴክሹዋል ሀራስመንት›) በሥም ተጠቅሶ ሕጋችን ላይ የለም” ይላሉ። “ስለዚህ ጥቃቱ በስፋት ይፈፀማል፣ ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውም አመለካከት በጣም የተዛባ ነው። ወሲባዊ ትንኮሳ የፍቅር ወይም የትዳር አጋር ጋር ግንኙነት ለመመሥረት የመግባቢያ መንገድ ተደርጎ ነው እንጂ የሚታሰበው ሴቷ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ፣ የሚያደርሰው አስከፊ ጉዳት ፈፅሞ አይታይም። ወሲባዊ ትንኮሳ በተለምዶ ‹ለከፋ› ከሚባለው ጋር ብቻ ተዛምዶ እና ቀላል ተደርጎ ነው የሚታየው” በማለት የተዛባ አመለካከት እንዳለ ያስረዳሉ።
“ወሲባዊ ትንኮሳን የሚመለከት ራሱን የቻለ ሕግ እስኪወጣ ድረስ፣ ሴት ልጅ ‹ተመታሁ፣ ተጎነተልኩ፣ የፍቅር ጥያቄ ባለመመለሴ ቤቴ ድረስ ክትትል ተደረገብኝ› ብላ ለፖሊስ በምታመለክትበት ጊዜ የወንጀል ሕጉ ላይ ሰውን መከታተል፣ የግል ነጻነቱን ማወክ፣ መስደብ፣ መዛት፣ መጎንተል እንደማይቻል የሚያስቀምጥ ቢሆንም ፖሊሶች ወይም የሕግ ሰዎች ሴት በመሆኗ ብቻ ድርጊቱን እንደወንጀል አይመለከቱትም። ግዴታ ወሲባዊ ትንኮሳ ተብሎ ባይቀመጥም እንኳ ወንጀል ሕጉ ላይ ባሉት አንቀፆች መክሰስ ይቻላል። ነገር ግን የአፈፃፀም ችግር አለ። የፍትሕ አካላቱ ውስጥ ያሉት ሰዎች ሴቷ እነዚህን ወንጀሎች ስታመለክት ‹ታዲያ ምን ችግር አለው? ወደደሽ እና የፍቅር ጥያቄ አቀረበልሽ እንጂ ምን አደረገሽ?›ነው የሚሏት፡” በማለት የወንጀል ሕጉ ውስጥ የተቀመጡ የወንጀል አንቀፆች ሳይቀሩ ሴቷ ጥቃት ሲደርስባት ጥርሳቸው እንደሚለግም ኃላፊዋ ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል በወንጀል ሕጉ ላይ በየትኛውም መልኩ ያልተካተቱ ነገር ግን የፆታ ትንኮሳ ውስጥ ወይም የወሲብ ትንኮሳ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ድርጊቶች እንዳሉ ሜሮን ያስታውሳሉ። “የወንጀል ሕጉ የፆታ ጥቃትን ታሳቢ በማድረግ ስላልወጣ ሁሉንም የጥቃት ዓይነቶች አላካተተም። አስገድዶ መድፈር ለብቻው፣ ድብደባ ለብቻው፣ መግደል ለብቻው ነው የተዘረዘሩት። የሠራተኛ ሕጉ ላይም ቢሆን በሥራ ቦታ የሚፈፀም ጥቃት በትንሽ በትንሹ ነው እንጂ የገባው ራሱን የቻለ ሕግ አይደለም ያለው፤ ነገር ግን ሁሉንም ፆታዊ ጥቃቶች ለመከላከል የሚያስችል እና የሚያካትት ራሱን የቻለ ሕግ ያስፈልጋል።”
ኃላፊዋ ከሚጠቅሷቸው የወሲብ ጥቃቶች ውስጥ “በጋብቻ ውስጥ የሚፈፀም አስገድዶ መድፈር” አንዱ ነው። ይህ ዓይነቱ አስገድዶ መድፈር በኢትዮጵያ ሕግ ወንጀል ውስጥ አልተካተተም፤ ስለሆነም እንደጥፋት አይቆጠርም። በዚህ ጉዳይ ብዙ ሰዎች አይስማሙም። በትዳር ውስጥ አስገድዶ መድፈር ሊኖር አይችልም ይላሉ። ይሁን እንጂ የስርዓተ ፆታ ጉዳዮች ባለሙያዋ አብነት በዚህ አይስማሙም። “ጋብቻ ከሁኔታዎች የፀዳ አይደለም። የትዳር አጋሮች ሥራ ሲሠሩ ውለው ይደክማቸዋል፣ ጤንነት ላይሰማቸው ወይም ጥሩ ‹ሙድ› ላይ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ከዚህም በላይ ላይፈልጉ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ አስገድዶ ወሲብ መፈፀም አስገድዶ ከመድፈር አይለይም” ይላሉ።
ኢትዮጵያ ብዙ መብቶችን የሚያጎናፅፉ ዓለማቀፍ ሥምምነቶችን ትፈርማለች፤ ይሁን እንጂ በተለይ የሴቶች መብቶች ላይ ትኩረት የሚያደርገውን የአፍሪካ ኅብረቱን የማፑቶ ሥምምነት አልፈረመችም። ሜሮን ኢትዮጵያ ይህንን ሥምምነት ያልተቀበለችበት ምክንያት ይህንን “በጋብቻ ውስጥ የሚፈፀምን አስገድዶ መድፈር ጨምሮ ሌሎችም ከባሕላችን ጋር የማይሥማሙ ነገሮች አሉበት” በሚል መሆኑን ይገልጻሉ።
በሕግ እና አፈፃፀም ረገድ ያሉ ክፍተቶችን በተመለከተ ሜሮን እና አብነት ተመጋጋቢ መልስ ነው የሚሰጡት። አብነት “መብቶች መብትነታቸው ተቀባይነት አግኝቶ በሕግ ከለላ እንዲደረግላቸው መጀመሪያ ማኅበረሰቡ ሊያምንባቸው ይገባል” ይላሉ። ሜሮንም በተመሳሳይ የአፈፃፀም ክፍተቱ የመጣው “ማኅበረሰቡ ውስጥ የፆታ ጥቃትን እንደ ትልቅ ችግር መመልከት ባለመቻሉ ነው” ይላሉ። ለዚህም ነው ጉዳዩ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት ራሱን የቻለ አዋጅ ወጥቶለት፣ አፈፃፀሙን በትኩረት መመልከት ያስፈልጋል የሚሉት።
ኃላፊዋ እንደሚሉት“ማኅበረሰቡ ራሱ የግንዛቤ ለውጥ እንዲያመጣ መሥራት ያስፈልጋል። ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚው፣ ሕግ አስፈፃሚው ከዚሁ ማኅበረሰብ የወጡ እና በማኅበረሰቡ አስተሳሰብ የተቃኙ እንደመሆናቸው መጠን፥ የፆታ ጥቃትን የሚያዩበት ዓይን የተዛባ ነው። በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎች እንኳን ለማስፈፀም ይቸግራል። አንደኛ ሕጉን ማውጣት፣ አፈፃፀሙን መከታተል እና ተጠያቂነትን ማጠናከር፣ የማኅበረሰብን አመለካከት መቀየር ዋና ዋና ሥራዎች ናቸው።”
ሜሮን አክለውም ሲያስረዱ “የሴቶች ጉዳይ ትልቅ የልማት አጀንዳ ነው፤ የማካተቱ ሥራ ወረቀት እና መዋቅር ላይ መቅረት የለበትም። እነዚህን ነገሮች የሚያስፈፅሙ ሰዎች የስርዓተ ፆታ ጉዳይ የገባቸው (‹ጀንደር ሴንሲቲቭ›) እንዲሆኑ ማድረግ አለብን፣ ተጠያቂነት እና ቁርጥኝነት ያላቸው እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ግን ደግሞ እነዚህ ሁሉ ኖረው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ከሌለ በበጀት፣ በፖሊሲ፣ በአፈፃፀም ረገድ ችግር ይፈጠራል።”
“ከእንግዲህማ ማን ይናገራቸዋል?”
ሕጉን ማጥበቅ እና አፈፃፀሙን ማጠናከር ውጤቱን ማከሚያ መፍትሔ ነው። አብነት ጣሰው ከመነሻው ጀምሮ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ‹የኃይል ሚዛኑ ያልተመጣጠነ ወይም የተዛባ መሆኑ ነው የችግሩ ሁሉ ሥረ መሠረት ነው› ይላሉ፤ “ከአስተዳደግ ብንጀምር፣ ሕፃናት ከሚገዛላቸው መጫወቻና ከሚመረጥላቸው የአልባሳት ቀለሞች ጀምሮ ሁሉ ነገር ወንዶች እና ሴቶች ልጆችን በተለየ ዓይን የሚመለከት ነው። ሴቶች ለስላሳ መሆን እንዳለባቸው፣ ኃይለኛ መሆን እንደሌለባቸው እየተነገራቸው እና ለትዳር የተመቻቹ አጎንባሾች (‹ሰብሚሲቭ›) ተደርገው እንዲያድጉ ሲኮተኮቱ፣ ወንዶች ግን በተቃራኒው ለስኬት ብቁ የሆነ ስብዕና እንዲገነቡ እየተደረጉ ነው የሚያድጉት። ይሄ ራሱ የኃይል ሚዛን መዛባት ከመነሻው ይፈጥራል፤ ችግሩንም መዋቅራዊ ያደርገዋል።” አብነት የኃይል ሚዛን መዛባት የችግሩ ሥር መሆኑን ብዙኃን እንደሚረዱ የሚያመላክት የቅርብ ጊዜ ይፋ ገጠመኝም አለ ይላሉ።
“የካቢኔ አባል ሴቶች እና ወንዶች እኩል፣ እኩል ተደርገው ሲሰየሙ እና የመከላከያ ሚኒስትሩን ቦታ ሴት ስትይዘው የተቀለደው ቀልድ ብዙ ነገሮች ይናገራል። “ከእንግዲህማ ማን ይናገራቸዋል? መከላከያውን ይዘውታል” ተብሏል፤ ማለትም ቀልዱን ተናጋሪዎቹ ጉዳዩ የኃይል ሚዛን መዛባት ጉዳይ መሆኑን በውስጣቸው ያውቃሉ ማለት ነው። ይህ እንግዲህ በውስጡ ቀልድ ያዘለ ትልቅ ቁም ነገር ነው፤ የኃይል ሚዛኑ የተዛባ መሆን ለፆታዊ ጥቃት መንስዔ መሆኑን ይናገራል” በማለት ባለሙያዋ ያብራራሉ።
መከላከል እና ማከም
የወሲብ ትንኮሳ እና ጥቃት በተለይ ሴቶችን ሰለባ እያደረገ ያለ፤ ጥቃት ከደረሰባቸውም በኋላ ራሳቸውን እንደጥፋተኛ እየቆጠሩ በምሥጢር አፍነውት እየኖሩ ለሥነ ልቦና ስቃይ የሚዳርግ ጥቃት ነው። የችግሩ መንስዔ እሸቱ ድባቡ “ተባእታዊ አገዛዝ” ሲሉ የሚጠሩት አድሏዊ ስርዓተ ማኅበር ሲሆን መፍትሔውም ማኅበራዊ የአመለካከት ለውጥ ነው። በመጠይቃችን የወሲብ ትንኮሳን ለማቆም ምን ይደረግ በሚል ላቀረብነው ጥያቄ አብዛኛዎቹ (78.6%) መላሾች እንደመፍትሔ የጠቆሙት “ኅብረተሰቡን ማስተማር” በሚል ነው። በተመሳሳይ፣ “ሕጉን ማጥበቅ” የሚል ጥቆማ 58 በመቶዎቹ ሲሰጡ፣ 55 በመቶዎቹ ደግሞ “ያለውን ሕግ አተገባበር ማጠናከር” ያስፈልጋል ብለዋል።
ማኅበረሰቡን ማስተማር የፆታዊ ጥቃቶችም ይሁኑ የወሲብ ትንኮሳዎች ከመከሰታቸው በፊት ለማስቀረት ሁነኛ ዘዴ ነው። ይሁን እንጂ ጥብቅ ሕግ እና ጠንካራ አፈፃፀምም የደረሱ ጥቃቶችን ለማስተማሪያነት ለማዋል አስፈላጊዎች ናቸው።

 

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here