የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ መቶ ሚሊየን ብር የሚያወጣና ለአገሪቷ የመጀመሪያ የሆነ የተበላሹና ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ መድኃኒትና ያገለገሉ የሕክምና ዕቃዎች ማስወገጃ ሥፍራ በአዳማ ገንብቶ ለማጠናቀቅ መቃረቡ ተገለጸ።
የማሽን ተከላና የቢሮ ግንባታ መጠናቀቁን የገለጹት የኤጀንሲው የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አድና በሬ በዓይነቱ ልዩና በመጠንም ትልቅ የተባለው ዘመናዊ ማስወገጃ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ጠቁመዋል። መንግሥትም ከጤና ተቋማት እንዴት መሰብሰብ አለበት የሚለውን በግልጽ ለማስቀመጥ መመሪያ ማዘጋጀት መጀመሩን ገልጸዋል።
በአገሪቷ በተለያዩ ቦታዎች ከሚገነቡ ስምንት ዘመናዊ ማስወገጃዎች አንዱ የሆነው ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ግንባታው ባለፈው ዓመት የተጀመረ ሲሆን በሰአት ዐሥር ኩንታል የሚሆኑ የተበላሹና ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ መድኃኒትና ያገለገሉ የሕክምና ዕቃዎች የማስወገድ አቅም አለው።
ግንባታው ግሎባል ፈንድ በተባለ ዓለም ዐቀፍ የተራድኦ ድርጅት የሚሸፈን ሲሆን ኢንሲኒድ በተባለ የእንግሊዝ ድርጅት ማሽኖችን አቅርቧል። ክትትሉን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ሲሆን ግንባታውን ጃምቦ በተባለ አገር በቀል ድርጅት ይካሔዳል።
በተለምዷዊ መንገድ መድኃኒት ማስወገድን ለማስቀረት ስፍራው ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። “ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ አደገኛ ጨረር ያላቸውን የሕክምና መገልገያዎችንና ክልሊካል ዕቃዎችን ለማስወገድ ይጠቅማል”።
አገሪቷ ከፍተኛ በሆነ የውጭ ምንዛሬ አደገኛ ጨረር ያላቸውን ለማስወገድ እንደምታወጣ የጠቆሙት አድና፣ ገንዘቡን ለሌላ አስፈላጊ ግዢዎች ለመጠቀም ይረዳል ብለዋል።
በዓመት በአገሪቷ ሩብ ቢሊዮን ብር የሚያወጣ መድኃኒት ይወገዳል ተብሎ ይገመታል። ቁጥሩ ኤጀንሲው በየዓመቱ ከሚያሰራጨው 16 ቢሊየን ብር አንፃር የአለም የጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው የሁለት በመቶ ጣሪያ ያነሰ ቢሆንም ዘመናዊ ማስወገጃ አለመኖሩ ከአካባቢ ጥበቃ አንፃር ችግሩን የበለጠ አስከፊ አድርጎታል።
የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፈው ዓመት በተደረገ ጥናት 94 በመቶ በአገሪቷ የሚገኙ ጤና ተቋማት ማቃጠልን ተመራጭ ማስወገጃ መንገድ ይጠቀማሉ፡፡
ይህንን ችግር ለመቅረፍ፣ 16 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ማስወገጃ ሥፍራዎች በአዳማ፣ ሐዋሳ፣ ባሕር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ ጅማ፣ መቀሌ፣ ደሴና ነቀምት መገንባታቸው ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011