ስርዓተ ፆታ እና ዴሞክራሲ

0
361

እሸቱ ድባቡ “ተባእታይ አገዛዝ በኢትዮጵያ፤ ችግሩና የመፍትሔው መንገድ” በሚል ርዕስ በ1997 ባሳተሙት መጽሐፋቸው “የሴቶች ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው” ሲሉ ጽፈዋል። “ዴሞክራሲ ታዳጊ ነው። ልማት ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት፤ የስርዓተ ፆታ ጉዳይ ወይም ችግርም የልማት ጉዳይ ነው” ብለዋል።
ብዙዎቹ ዴሞክራሲዎች ሲጀምሩ ሴቶችን ለምርጫ (መራጭ ወይም ተመራጭነት) ማዕረግ እንኳን ብቁ አያደርጓቸውም ነበር። እሌኒ መኩሪያ እና ዓለም ሰገድ ኅሩይ ባቀረቡት አንድ መጣጥፍ ላይ ይህ ዓይነቱ ፍላጎት እንደነበር ጽፈዋል። ታሪኩ እንዲህ ነው። ከመጀመሪያዎቹ ሴት የፓርላማ አባላት አንዷ ስንዱ ገብሩ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ነበር። በዚህ ጊዜ አንዱ ጠያቂ “‹እንዴት ነው እናንተ ሴቶች ሳትለፉበት የመመረጥ መብት ያገኛችሁት?› ብሎ ሲጠይቃቸው፥ ‹ለመሆኑ እናንተ ወንዶች ምን ሠርታችሁ ነው መብቱን ያገኛችሁት?› በማለት ጥያቄውን በጥያቄ” መልሰውለታል። ይህ የሚያሳየን እውነታ ‹ሴቶች ከወንዶች እኩል መብቶችን ማግኘት የለባቸውም፤ ቢኖርባቸውም ተጨማሪ ትግል አድርገው ነው› ብለው የሚያስቡ ሰዎች መኖራቸውን ነው። ዴሞክራሲ መብቶችን ለሁሉም የታገለ፣ ያልታገለ ሳይል ያለአድልዖ የሚያከብር እና የሚያስከብር ስርዓት ነው።
ዴሞክራሲ የሚያድግ ስርዓት እንጂ ቆሞ ቀር አይደለም። ከነጉድለቱ ተቀባይነት ያለው ስርዓት የሚያደርገውም ይህ ለመሻሻል ክፍት የመሆን ባሕሪው ነው። እሸቱ ድባቡ ዴሞክራሲ “ማኅበራዊ ልዩነቶችን (የተዋረድ ወይም የመበላለጥ [እርከን]) ማስወገድ ይችላል” ይላሉ። ለእርሳቸው የሴቶችን ሁለ ገብ ጥያቄ መመለስ የሚችለው ዴሞክራሲያዊ ልማት ነው። ልማት “ለጭቁን ወገኖች” ወደ ነጻነት እና እኩልነት የሚደረግ ግስጋሴ ሲሆን ይህም ከጭቆና፣ ከብዝበዛ፣ ከድለላ ነጻ መሆን ማለት ነው”።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የስርዓተ ፆታ መድልዖ ከግምት ውስጥ በማስገባት፥ ራሱን የቻለ የሴቶች መብቶችን ማስከበሪያ አንቀፅ (35) አስቀምጧል። አንቀፁ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው፣ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው የማድረግ እና ሌሎችንም ይደንግጋል። ስለዚህ የሴቶች እኩልነት እንዲረጋገጥ መሥራት፣ የመንግሥት ግዴታ እና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ይሆናል።
የስርዓተ ፆታ ልዩነቶች አግባብም፣ ተፈጥሯዊም አይደሉም ተብሎ ይታመናል፤ በመሆኑም የስርዓተ ፆታን የማስተካከል አስተዳደራዊ እርምጃ የስርዓተ ፆታ (‹ጀንደር ዴሞክራሲ›) የሚል ሥያሜ ተሰጥቶት የተለያዩ ጥናቶች እየተደረጉበት ነው። ‹የስርዓተ ፆታ ዴሞክራሲ› አስተሳሰብ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ልዩነት የማይፈጥር ስርዓት እሳቤ ሲሆን፣ ዋና ትኩረቱ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ እኩል ውክልናን ማረጋገጥ ቢሆንም በንግድ ድርጅቶች እና ሌሎችም ውስጥ ሴቶች እና ወንዶች የማይለዩበት አስተዳደራዊ ባሕል ማዳበር ነው።

 

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here