የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት ሥድስት ወራት ለጎረቤት አገራት 47 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ያስገኘ የኃይል ሽያጭ ማከናወኑን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሽያጭና ደንበኞች አስተዳደር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ምኒልክ ጌታሁን ነግረውኛል ብሎ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደዘገበው ደግሞ ሱዳን በኤሌክትሪክ ሽያጭ ለኢትዮጵያ ያልከፈለችው 70 ሚልየን ዶላር ዕዳ አለባት ተብሏል።
ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት አቶ ሚኒሊክ በ2016 በጀት ዓመት ለሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ምንም ዓይነት ገቢ አልተሰበሰበም። “በጥቅሉም የ70 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ አለባት” ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዓመቱ ግማሽ ለጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ 1 ሺህ 82 ጊጋ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 66 ነጥብ 27 ሚሊየን ዶላር ሽያጭ ለማከናወን አቅዶ የነበር ሲሆን ከዕቅዱ ውስጥ 762 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሰዓት ኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ 47 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማድረግ መቻሉን ገልጿል።
ለሱዳንና ኬንያ የተከናወነው ሽያጭ ከዕቅዱ ዝቅ ብሏል ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል ድርጅቱ፤ በግማሽ ዓመቱ ለሱዳን 11 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ኃይል ለማቅረብ ቢታቀድም በአገሪቱ ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ 8 ሚሊየን ዶላር ብቻ ገቢ ማግኘት እንደተቻለ አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሽያጭና ደንበኞች አስተዳደር ቢሮ ሥራ አስኪያጁ እንደገልጹት የሱዳንን ጉዳይ በተመለከተ በመንግሥት ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ “ለአገሪቱ የሚቀርበውን የኃይል መጠን 50 በመቶ እንዲቀነስ” ተደርጓል። ሱዳን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያላት ሲሆን ለምሳሌ ያህል ከሁለት ዓመት በፊት በዓመት ጊዜ ውስጥ ለሱዳን ከተሸጠ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ከ54.6 ሚልየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቶ ነበር።
በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሥድስት ወራት ውስጥ ለኬንያ የ33 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ሽያጭ ለማከናወን ዕቅድ ተይዞ መሸጥ የተቻለው 20 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ወይም ከዕቅዱ ከ10 ሚልየን ዶላር በላይ ያነሰ መሆኑ ተመላክቷል። በዚሁ ተመሳሳይ ወቅት ውስጥ ለጅቡቲ 20 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ ታቅዶ የ19 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ሽያጭ መፈጸሙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታቀደውን ኃይል ለማቅረብ “አቅሙና ዝግጁነት ቢኖርም” በሱዳን እና ኬንያ በኩል የታሰበውን ያህል ኃይል አለመውሰዳቸው እና ፍላጎታቸው ወጥ አለመሆኑ ለዕቅዶቹ አለመሳካት ምክንያት ናቸው ተብሏል። ጅቡቲም በተመሳሳይ ትወስዳለች ተብሎ ከታሰበው የኃይል መጠን ፍላጎቷ የቀነሰ መሆኑም ተጽእኖ አሳድሯል።
በቀጣዩ ግማሽ ዓመት በአገር ውስጥ የኃይል አቅርቦትን በዶላር ለመግዛት ፍላጎት ካላቸው ተቋማት ጋር ግብይት ለመፈጸም ስምምነት መደረሱን ያስታወቀው የኃይል አቅራቢ ድርጅቱ፤ ከጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬንያ በተጨማሪ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ዕቅድ መያዙን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ችግሮች ቢኖሩም የውጭ የኃይል አቅርቦት ላይ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት በ15 በመቶ ከፍ ማለቱን እንዲሁም ለሽያጭ የሚቀርበው የኃይል መጠን በ16 በመቶ ያህል መጨመሩን አመልክቷል።


