“ደሃው ህብረተሰብ ለዓመታት ከልጆቹ ጉሮሮ ነጥቆ እየቆጠበ መንግስት ቤቶችን ለጨረታ ማቅረቡ ያሳዝናል”- የ1997 ቆጣቢዎች ለአዲስ ማለዳ

0
1592

የአዲስ አበባ ቤቶች ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ እና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ትብብር ከ3 ሺህ የሚበልጡ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን በጨረታ አወዳድሮ ለመሸጥ ያወጣው ማስታወቂያ ለበርካታ ዓመታት ቤት ለማግኘት የቆጠቡ እና እየቆጠቡ የሚገኙ ነዋሪዎችን አስቆጥቷል።

ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ያቀረቡ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች የጨረታ ማስታወቂያው ቤት ለማግኘት ለዓመታት ሲቆጥብ የነበረውን ህብረተሰብ ያላማከለ ነው ብለዋል። 

ሃሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡ አንድ ነዋሪ የ2005 ባለአንድ መኝታ ኮንዶሚንየም መመዝገባቸውን ተናግረው 11 ዓመታትን ቢቆጥቡም እጣው ገና የ1997 የተመዘገቡት እንኳን ባለመዳረሱ ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ይገልጻሉ። “እዚ ላይ መንግስት ቤት እየሰራ በጨረታ ለሽያጭ ማቅረቡ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው” ሲሉም ቅሬታቸውን ነግረውናል። 

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን “ያለበትን የፋይናንስ እጥረት በመፍታት ተጨማሪ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ገንብቶ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲችል” ከዲዛይን ግንባታ ቢሮ ጋር በመሆን በመንግስት በተመደበ ካፒታል በጀት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተገንብተው የተጠናቀቁ 3 ሺህ 452 የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን በጨረታ አወዳድሮ በሽያጭ ለማስተላለፍ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ከቀናት በፊት መግለጹ ይታወቃል።

በማይመለስ 1 ሺህ ብር እየተሸጠ የሚገኘው የጨረታ ሰነዱ ከጥር 27 እስከ የካቲት 20 ቀን 2016 ድረስ እንደሚሸጥም ተገልጿል። 

“ስሜ አይጠቀስ” ብሎ ለአዲስ ማለዳ ሃሳቡን የገለጸ አንድ ግለሰብ “ህብረተሰቡ መኖሪያ አጥቶ በሚንገላታበት ሰዓት ቤቶቹን ለሽያጭ ማቅርቡ አቅም ያለውን ማበረታት እና አቅም የሌለውን ማዳከም ነው” ሲል ይናገራል። ሌላኛዋ የ2005 ባለ አንድ መኝታ ተመዝጋቢ የሆነች የከተማዋ ነዋሪም ከ11 ዓመታት በኋላ በራሷ ቤት ለመስራት ነገሮችን ማመቻቸቷን ተናግራ እየቆጠበች የምትገኝበትን ቤት ለመሸጥ መወሰኗን ገልጻለች።

በተመሳሳይም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቸውና ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የሁለት ልጆች አባት የሆነ ግለሰብ “በ1997 ባለአንድ መኝታ ተመዝግቤ 19 ዓመታትን እየቆጠብኩ ነው። በኪራይ ቤት ለዓመታት እየተንገላታሁ ነው” ብሏል። “በትክክል የተመዘገበውን ትቶ፤ ቤቶችን ገንብቶ ለሽያጭ ማቅረብ ፍትሐዊ አይደለም” ሲልም የጨረታ አዘጋጆቹን ተችቷል።

በ1997 ባለሁለት መኝታ ቤት ተመዝግቦ በድጋሚ ወደ 2005 የቀየረ ሳምሶን የተባለ ግለሰብ “ዕድለ ቢስ እንደሆንኩ ነው የተሰማኝ” ሲል በመንግስት የወጣው ጨረታ የፈጠረበትን ስሜት ገልጿል። ሌላ አስተያየት ሰጪም “ደሃው ህብረተሰብ ለዓመታት ከልጆቹ ጉሮሮ ነጥቆ እየቆጠበ ባለበት መንግስት ኮንዶሚንየም ለመሸጥ ለጨረታ ማቅረቡ የእውነት ያሳዝናል” ብሏል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ ግለሰቦች ለበርካታ ዓመታት የቆጠቡ እንዲሁም ሙሉ ክፍያውን የፈጸሙ ሲሆኑ አሁን መንግስት እያደረገ ያለው ነገር ለረጅም ዓመታት ተስፋ ያደረጉበትን መኖሪያ ቤት “ማግኘት የማይቻል ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የቤት ባለቤት መሆን ያልቻሉ ቆጣቢዎች ጉዳይ ቀድሞ ታሳቢ ስለመደረጉ እንዲሁም ለቅሬታ አቅራቢዎቹ የታሰበ የመፍትሔ ሃሳብ መኖሩን በተመለከተ ለማጣራት ያደረገችው ሙከራ ወደ ኮርፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በተደጋጋሚ ብትደውልም ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን በተደጋጋሚ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጥራታቸውን ጠብቀው ባለመግንባታቸው፤ በዕጣ የቤት ባለቤት የሆኑ ባለዕድለኞኝች ለከፍተኛ ወጪ እየዳረጉ ነው በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here