ዩኒቨርሳል ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ድርጅት እና ቲክቶክ ሲስማሙ ሙዚቃዎቹ ይመለሳሉ- ሮፍናን

0
715

የሙዚቃ ባለሞያው ሮፍናን አዲስ ከሚያወጣው ‘ዘጠኝ’ የተሰኘው አልበሙ ላይ እንደቅምሻ የተለቀቀው ‘ዶርዜዴሊክስ’ ነጠላ ዜማን ጨምሮ ከዚህ ቀደም የለቀቃቸውን ሙዚቃዎች ከቲክቶክ መተግበሪያ ላይ መውረዳቸው ይታወቃል።

የዜማ ደራሲ፣ ድምጻዊ እና አቀናባሪ ሮፍናን ኑሪ ከዓለም አቀፉ የሙዚቃ ድርጅት ዩኒቨርሳል ጋር ለመስራት መስማማቱ እና ወደስራ ቢገባም የሙዚቃ ድርጅቱ ከቲክቶክ መተግበሪያ ጋር ያለው ስምምነት መቋረጥን ተከትሎ በድርጅቱ ስር ያሉ ማንኛውም ሙዚቃዎች በመተግበሪያው ላይ እንዳይጫወቱ ታግዷል። 

የሙዚቀኛ ሮፍናን ስራዎችም በድርጅቱ ስር መሆናቸውን ተከትሎ ከቲክቶክ መተግበሪያ መውጣታቸውን ያስታወሰው ባለሞያው “ድርጅቱ ከቲክቶክ ጋር ያለውን ስምምነት ሲያስተካከል ሙዚቃው እንደሚመለስ” ዛሬ ጥር 30 ቀን 2016 በማርዮት ኤግዚክዩቲቭ ሆቴል ሮፍናን እና ሄይኒከን ኢትዮጵያ የአጋርነት ሥምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ገልጿል። 

ሙዚቃን ከማስተዋወቅ እና ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ቲክቶክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑ በመተግበሪያ የተለቀቀው ሙዚቃ በጥሩ ሁኔታ አድማጭ ጋር እንደደረሰለት ሮፍናን ተናግሯል።

አዲስ ማለዳ በታደመችው መርሃ ግብር የሙዚቃ ባለሞያው ሮፍናን ኑሪ እና የሄይኒከን ኢትዮጵያ ዋልያ ቢራ በድምጻዊው አዲስ የአልበም ሥራ የአጋርነት ፊርማ ተፈራርመዋል። 

በተመሳሳይ የሮፍናን ‘ስድስት’ የተሰኘው የቀደመ የሙዚቃ አልበም አጋሩ ከነበረው የሄይኒከን ኢትዮጵያ ዋልያ ቢራ ጋር ‘ዘጠኝ’ ለተሰኘው አዲስ አልበምም መቀጠሉን አረጋግጠዋል። 

ሮፍናን በቅርቡ በሚወጣው ዘጠኝ አልበሙ ሥር የያዛቸው “ሐራንቤ” እና “ኖር” የተሰኙ የሙዚቃ አልበሞች በአንድ ቀን የሚወጡ መሆኑን አዲስ ማለዳ በታደመችው የፊርማ ሥነ ስርዓት ላይ ተገልጿል። 

በዚህ ሳምንት ከጥር 27 እስከ ጥር 29 2016 በተካሄደ የማስተር ክላስ መርሃ ግብር ድምጻዊዉ ያለውን ልምድ እና ዕውቀት ለጀማሪ እና ወጣት ሙዚቀኞች ማጋራቱ አይዘነጋም።

መርሃ ግብሩ በክልል ከተሞችም እንደሚቀጥል እና በስራው ላይ ያሉ ጀማሪ የሙዚቃ ባለሞያዎች የስራው ሁኔታን እና የራስን የሙዚቃ መንገድ የመፍጠር ስልጠና በዋናነት እንደሚሰጥ ማወቅ ተችሏል። 

በተጨማሪም በሙዚቃው ዘርፍ ላይ ልምድ እና ችሎታ ያላቸው ሌሎች ባለሞያዎችም ልምዳቸውን የሚያጋሩበት መድረክ እንደሚሆን ሮፍናን ገልጿል።

ሁለት የሙዚቃ አልበሞችን በአንድ ላይ መልቀቁን ተከትሎ “አዲስ ነገሮችን ከራሱ የሙዚቃ ስልት ጋር አዋህዶ ማቅረቡን፣ በተጨማሪም ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅ ስራዎችን ይዞ መምጣቱን” ባልሞያው አመላክቷል።

ቀደም ሲል ሮፍናን ኑሪ በለቀቀው ‘ስድስት’ የተሰኘ አልበሙ ሥድስት የሚሆኑ የሙዚቃ ድግስ (ኮንሰርት) የተዘጋጀ ሲሆን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የሙዚቃ ስራዎቹን አቅርቦ ነበር። ሮፍናን በአዲሱ አልበሙ 10 ያህል የሙዚቃ ድግሶችን በተሻለ መልኩ ለማካሄድ ማቀዱን አስታውቋል። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here