አጓትን ከሌሎች ምግቦች ጋር በመቀላቀል የምግብ ይዘትን ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ

0
1293

የወተት ተረፈ ምርት የሆነውን አጓት ከተለያዩ ምግቦች ጋር በመቀላቀል ኅብረተሰቡ የተሻለ የፕሮቲን ይዘት ያላቸውን ምግቦች እንዲያዘወትር ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስጋና ወተት አንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የወተት ተረፈ ምርት የሆነው አጓት፣ አይብ ከተመረተ በኋላ የሚቀር ሲሆን በኅብረተሰቡ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ የወተት ምርቶች በሚያቀነባብሩ ፋብሪካዎች እንደ ተረፈ ምርት ሲወገድ እንደነበር ተጠቁሟል። ይህም ከሚያስከትለው ብክነት በተጨማሪ ተረፈ ምርቱ በሚደፋባቸው አካባቢዎች ላይ ሥነ ምኅዳራዊ ብክለት ያስከትላል ተብሏል። በአዲሱ ጥናት መሰረት በቀጣይ ጊዜያት በምግብ ማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ሳይቀር እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ሥልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነ ተገልጿል።

አጓትን ከዳቦ፣ ከጭማቂ እና ከኬክ ምርቶች እንዲሁም ከተለያዩ ጣፋጭ ብስኩቶች ጋር መቀላቀል የምግቦቹን የፕሮቲን ይዘት ለመጨመር እንደሚረዳ ማብራሪያ ተሰጥቷል። እነዚህን ምግቦች ለማዘጋጀት በይበልጥም ለዳቦ፤ ከውሃ ይልቅ አጓትን መጠቀም በዳቦ ውስጥ ከሚገኘው ካርቦሃይድሬት በተጨማሪ ፕሮቲን ይዘት እንዲኖረው በማድረግ በብዛት ለሚጠቀም ማኅበረሰብ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቁሟል።

በአዲስ አበባ ከተማ በዳቦና ጭማቂ ምርት ለተሠማሩ አነስተኛና መካከለኛ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና በወተት ልማት ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ ግንዛቤን ለመፍጠር ሥልጠናዎች እየተሰጡ ሲሆን፣ ኢንስቲትዩቱ ከአጓት የተመረቱ ዳቦዎችን በማቅረብ ከኅብረተሰቡ ጋር ለማስተዋወቅ እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስጋ እና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ወተት እና የወተት ተዋፅኦ ተመራማሪ ሙሉጌታ ተስፋዬ ተናግረዋል።
የሆለታ እንስሳት ምርምር ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ፍሬው በላይ (ዶ/ር) በወተት ውስጥ ካሉት ኹለት ዓይነት ፕሮቲኖች አይብ በሚመረትበት ወቅት የሚሟሟው የፕሮቲን ዓይነት በአጓት ወስጥ እንደሚገኝ እና ይህም 20 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይገልፃሉ። አይብ በማምረት ሒደት ውስጥ ከዐስር ሊትር ወተት ውስጥ አንድ ኪሎግራም አይብ ብቻ የሚገኝ እና ሌላው የሚደፋ መሆኑን ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የማማ ወተት እና የወተት ተዋፅኦ ማምረቻ ዋና ሥራ አስኪያጅ መላኩ ዘሪሁን፣ አይብ ከተመረተ በኋላ የሚገኘውን አጓት በዘመናዊ መንገድ ወደ ምግብነት ለመቀየር ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ በመሆኑ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በቀላሉ ሊተገብሩት አይችሉም ሲሉ ይገልፃሉ። በአደጉት አገራትም አጓትን ወደ ዱቄት በመቀየር ለተለዩ የምግብ ምርቶች በግብአትነት እንዲያገለግል እንደሚደረግ የገለጹ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ግን እስከ አሁን መጠቀም አልተቻለም ይላሉ። ማማ ወተትም ከምርት በኋላ የሚገኘው አጓት ለአበባ እርሻዎች ባለው ተፈላጊነት ምክንያት ለሽያጭ እንደሚያቀርብ ገልፀዋል።
አሁን የታሰበውን ምርት በሚመለከትም ወተት እና የወተት ተዋፅኦ ውጤቶች በቶሎ ለብክለት የሚዳረጉ በመሆናቸው ከንፅህና እና ከምግብ መመረዝ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። ሥራውም በትልልቅ የወተት ኢንዱስትሪዎች የሚሠራ ሥራ ነው ያሉ ሲሆን፣ በአቀራረቡ ላይ እንዲሁም በተቀባይነቱ ላይ ትልቅ ሥራን የሚጠይቅ ነውም ብለዋል።

አክለውም ሐሳቡ መልካም የሚባል ቢሆንም የሚጠይቀው ከፍተኛ እውቀት እና ኢንቨስትመንት ሥራውን ከባድ ያደርገዋል እንዲሁም ከአቀራረብ፣ ከንፅህና እና ከጥራት ደረጃዎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ጥናቶች ሊደረጉ ይገባል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዓለም ዐቀፉ የጤና ድርጅት መለኪያ መሰረት አንድ ሰው በዓመት እስከ 200 ሊትር ወተት ማግኘት ይገባዋል። በኢትዮጵያ በአማካይ አንድ ሰው 19 ሊትር ወተት በዓመት ያገኛል ተብሎ ይታሰባል። በዓለም ዐቀፍ የጤና ድርጅት መለኪያ መሰረት የተቀመጠውን የወተት አጠቃቀም ለማሳካት ኢትዮጵያ 44 ቢሊዮን ሊትር ወተት በዓመት ማምረት ሲጠበቅባት፣ በአሁን ጊዜ የሚመረተው ግን 4 ቢሊዮን ሊትር ወተት ብቻ ነው።

በኢትዮጵያ ከ61 ሚሊዮን በላይ የወተት ላሞች ቢኖሩም፣ በዘረመል፣ በመኖ ጥራት እና መሰል ችግሮች ምክንያት የሚፈለገውን ምርት መስጠት እንዳልቻሉ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በአሁኑ ወቅትም 20 ወተትን በዘመናዊ መንገድ የሚያቀነባብሩ ድርጅቶች በሥራ ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here