ከጨርቃ ጨርቅ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ የ 17 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳየ

0
526

የጨርቃ ጨርቅ እና የስፌት ምርቶችን ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ ባለፉት ሦስት ወራት ከ 52 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ 17 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ ማሳየቱ ይፋ ተደረገ።

የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች፣ ያለቀላቸው አልባሳት፣ ድር እና ማግ በዋነኝነት ለውጪ ገበያ የቀረቡ ምርቶች ሲሆኑ ጀርመን፣ ጣልያን፣ የአፍሪካ ገበያ (ኮሜሳ)፣ አውሮፓ እና የእስያ አገራት የምርቶቹ ዋነኛ መዳረሻ ነበሩ።

በሩብ ዓመቱ 55 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘት እቅድ የነበረ ሲሆን፣ 52 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ በማግኘት የእቅዱን 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት የስፌት ኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

ለገቢው መጨመርም በተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያሉ አምራቾች እንደ ግንባታ እና መሣሪያ ተከላ ያሉ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ማምረት መግባታቸው እንደ ምክንያት የተነሳ ሲሆን፣ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ያለውን ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት መሰረት በማድረግ ወደ እነዚህ የገበያ መዳረሻዎች ምርቶች በስፋት እንዲላኩ መደረጉ ውጤቱ ከፍ እንዲል ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።

የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ በአገሪቱ ከሚገኙ የአምራች ዘርፎች ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቶት ከፍተኛ ማበረታቻዎች የሚቀርቡበት ነው።
ኢትዮጵያ በዘርፉ እየሠለጠነ ያለ ሰፊ የተማረ የሰው ኃይል ያለባት፣ እየተሻሻለ ያለው መሠረተ ልማት ለኢንቬስትመንት ምቹና ሳቢ መሆኑ፣ በዓለም ተወዳዳሪ የሆነ የኤሌክትሪክ ዋጋ፣ የፋይናንስ ብድርና የተለያዩ ሳቢ ማበረታቻዎች እንዲሁም ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ባንቲሁን ገሠሠ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል እንዳያድግም የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና በአንዳንድ ቦታዎች ላይም የኤሌክትሪክ አገልግሎት አለመቅረቡ እንዲሁም የመሰረተ ልማቶች በሚፈለገው ደረጃ አለመሟላት ማነቆ መሆናቸውን ባንቲሁን ተናግረዋል።

ችግሮቹንም ለመቅረፍ ከፋብሪካዎቹ ጋር በመተባበር ለሠራተኞች እና ለሥራ ኀላፊዎች ሥልጠናዎችን በማዘጋጀት እየተሰጠ ነው ያሉት ባንቲሁን፣ በዘርፉ ረዥም ዓመታት ልምድ ካላቸው እንደ ሕንድ ካሉ አገራት ባለሙያዎችን በማምጣት በፋብሪካዎች እንዲሁም በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት አጫጭር ሥልጠና በመስጠት፣ ልምድ በማካፈል፣ የፋብሪካ የሥራ ባህልን እንዲላመዱት በማድረግ ክህሎታቸውን እና እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ የማድረግ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ከ200 በላይ መካከለኛ እና ከፍተኛ የጨርቃ ጨርቅ እና ስፌት ኢንዱስትሪዎች በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በእነዚህ ፋብሪካዎችም ከ100 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ድርሻን ለማሳደግና በ2012 በጀት ዓመት ከውጭ ንግድ 254 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፣ ይህንንም ለማሳካት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here