የመኪና ማስዋቢያ ምርቶችን አመሳስሎ ያስመጣው ድርጅት ተቀጣ

0
658

የመኪና ውስጣዊ አካላትን ማስዋቢያ የቅባት ምርቶችን አመሳስሎ ወደ አገር ውስጥ ያስገባው አዲስ አሊ መኪና ዕቃዎች አስመጪ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር በመፈፀም በሸማቾች ጥበቃ እና የንግድ ውድድር ባለሥልጣን በተመሠረተበት ክስ የባለሥልጣኑ አስተዳደራዊ ችሎት ከዓመታዊ ገቢው ላይ ዐስር በመቶ ቅጣት ጣለበት።

በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የሚመረተውን ስታር ኦቨርሲስ ትሬዲንግ የተሰኘ ድርጅት አውቶ ዞን የተሰኘውን የመኪኖችን ቅባት የሚያመርት ሲሆን፣ አዲስ አሊ መኪና ዕቃዎች አስመጪ አውዞ ዞን በሚል ስያሜ ከማሸጊያው ቀለም ጋር እንዲሁም በቅርፅ በማመሳሰል በውጪ አገራት በማምረት ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገባ በማስረጃ አረጋግጫለሁ ሲል የባለሥልጣኑ ዐቃቤ ሕግ በክስ መዝገቡ ላይ አስፍሯል።

ከሳሾችም አውቶ ዞን ከ 2009 ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ የነበረ እና በተጠቃሚዎች ዘንድም ሰፊ ገበያ ያለው መሆኑን ከግምት ውስጥ በመክተት፣ ምርቱን አመሳስሎ በማሠራት እና ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ተፈፅሞብናል ሲሉ ለባለሥልጣኑ አመልክተዋል። በተጨማሪም ደንበኞቼ ላይ መደናገር እንዲፈጠር አድርገዋል ያሉት የግል ተበዳዮች፣ ለሸማቾች መብት ጥበቃ እና ንግድ ውድድር ባለሥልጣን ነሐሴ 22/ 2011 ባስገቡት አቤቱታ መሠረት ነበር ባለሥልጣኑ ምርመራውን አጠናቅቆ ክስ የመሰረተው።

ተከሳሽ በበኩሉ ከ2009 በፊትም ወደ አገር ውስጥ በማስገባት በገበያ ላይ ሲቀርብ የነበረ ምርት ነው ‹‹አወዞ ዞን›› ‹‹ከ አውቶ ዞን›› ጋር ልዩነት ስላለው ሸማቾችን የሚያደናግር ምንም ዓይነት መመሳሰል የለም በሚል ሲከላከል ቆይቶ፤ በመጨረሻ ድርጊቱን መፈፀሙን አምኖ መከራከሩን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የባለሥልጣኑ አስተዳደራዊ ችሎትም ከኢትዮጵያ አዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት አውቶ ዞን የሚለው የምርት ስያሜ በባለቤትነት መመዝገቡን አረጋግጦ ‹‹አውዞ ዞን›› የተሰኘው ምርት ከ ‹‹አውቶ ዞን›› ጋር በሥያሜ እንዲሁም በማሸጊያው ቀለም መመሳሰላቸውን በቀረቡለት ማስረጃዎች ማረጋገጡን ጠቅሶ ፍርድ ሰጥቷል።
ተከሳሽ የምርቶቹን መመሳሰል እያወቁ በውጪ አገራት እንዲመረት በማድረግ ወደ አገር ውስጥ ማስገባታቸው ጥፋት ነው ያለው ችሎቱ፣ ድርጊቱ ሸማቾችን የሚያደናግር ነው ያለ ሲሆን፣ እንዲሁም ከዚህ በተጨማሪም በከሳሽ ላይ ተገቢ ያልሆነ የንግድ ውድድር ተፈፅሟል ብሏል። የተከሳሽን ድርጊቱን መፈፀሙን ማመን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ 2011 ዓመታዊ ገቢው ላይ ዐስር በመቶ እንዲቀጣ ወስኖበታል።

ከዚህ በተጨማሪም ከውሳኔው በኋላ ምርቱን እንዳያከፋፍሉ የታዘዘ ሲሆን፣ አሁን በገበያ ላይ ስለተሰራጨው ምርት ግን ውሳኔው ያለው ነገር የለም። ፍርድ ቤቱ ውሳኔው ከተሰጠበት ኅዳር 12/2012 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ 30 ቀናት ውስጥ ይግባኝ የማለት መብት እንዳላቸውም ገልጿል።

የሸማቾች መብት ጥበቃ እና ንግድ ውድድር ባለሥልጣን የንግዱን ማኅብረሰብ ከፀረ-ውድድርና ተገቢ ካልሆኑ፣ ሕገ ወጥ የገበያ ተግባራት፣ አሳሳች ከሆኑ የገበያ ሁኔታዎች የሚከላከል እንዲሁም ለነፃ ገበያ ውድድር አመቺነት ያለው ድርጊት የማስፈን ዓላማን ይዞ በ2006 የተቋቋመ ተቋም ነው።

በባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት ማንኛውም ሸማች ስለሚገዛው ዕቃ ወይም አገልግሎት ጥራትና አይነት በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት፤ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት፣ የዕቃዎችን ወይም የአገልግሎቶችን ጥራት እና አማራጮች ማየት መብት እንዳለው ይደነግጋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here