ያለአግባብ ተሰቅሎ የቆየው የሰሊጥ ዋጋ በግማሽ ቀነሰ

0
1026

በአገር ውስጥ ገበያ የሰሊጥ ዋጋ በግማሽ የቀነሰ ሲሆን በግብይት ሰንሰለቱ የመንግሥት የመቆጣጠር ብቃት ማነስ ዋጋው ባልተገባ ሁኔታ ንሮ ለመቆየቱ በዋነኛ ምክንያትነት ተጠቅሷል።

ላኪዎች የሰሊጥ ምርትን ከአገር ውስጥ ገበያ ዋጋ በላይ በመግዛት ለዓለም አቀፉ ገበያ ባነሰ ዋጋ የሚያቀርቡበት ከስርዓት የወጣ ግብይት፣ ለዋጋ ጭማሪው ምክንያት መሆኑን ተከትሎ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስርዓት በመዘርጋቱ የዋጋ ልዩነቱ መስተካከሉን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፤ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አሰፋ ዮሐንስ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የዋጋ ጭማሪው በላኪዎች ያልተገባ የዋጋ ድርድር የተፈጠረ በመሆኑ የአሁኑ የሰሊጥ ዋጋ ማስተካከያ ቅናሽን የሚያመለክት ሳይሆን ከዓለም ዐቀፉ ገበያ የሰሊጥ ዋጋ መሸጫ ጋር የሚናበብ እንዳደረገው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሰሊጥ ምርት ከዓለም ገበያ በተሻለ ጥራት እንደሚቀርብ የገለጹት ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጥራጥሬ፤ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ዘርፍ ባለሙያ፤ መንግሥት የመቆጣጠር አቅም ስላልነበረው ገበያው ለአገሪቱ ማበርከት የነበረበትን ያህል ሳያበረክት ቀርቷል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ላኪዎች ከአገር ውስጥ የሚገዙትን የሰሊጥ ምርት ከዓለም ዐቀፉ ገበያ በቶን 200 እና 300 ዶላር ዋጋ ከፍ አድርገው በመግዛት ለዓለም አቀፉ ገበያ በዝቅተኛ ዋጋ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የመንግሥትን የመቆጣጠር አቅም ማነስ በመጠቀም ከሚልኩት ምርት በኪሳራ መልክ የሚያገኙትን ዶላር ለሌሎች ሸቀጦች ማስገቢያ አድርገው ስለሚጠቀሙት መሆኑን ባለሙያው አብራርተዋል።

በዓለም ዐቀፉ ገበያ የሚያጋጥማቸውን ኪሳራ ወደ አገር ውስጥ በሚያስገቧቸው ሸቀጦች ላይ ዋጋ በመጨመር ትርፍ የሚያገኙበት ስርዓት የሚከተሉ ነበሩ ሲሉም አሠራሩን አስረድተዋል። ከዓለም ዐቀፉ ገበያ ጋር የተደረገው ማስተካከያ አገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ቀጥተኛ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋትም ጠቁመዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማንኛውም ላኪ ከዓለም ዐቀፉ ዋጋ አስበልጦ መግዛት እንደሌለበት መመሪያ ማውጣቱ ለዋጋ መውረዱ እንደ ምክንያት ሊቀርብ እንደሚችል በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ነጻነት ተስፋዬ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

የመንግሥት የአቅም ውስንነት ለካፒታል ሽሽት በር መክፈቱን የገለጹት በንግድና ኢንዱስትሩ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወንድሙ ፍላቴ ናቸው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወጪ ንግዱ ስርዓት ማስያዣ እንዲሆን ከጥቅምት 2012 ጀምሮ የወጪ ምርቶች ውል ምዝገባና አፈጻጸም መመሪያን ተግባራዊ ማደረጉ ሕገ ወጥ የንግድ ስርዓቱን ለመቆጣጠር አስችሏልም ብለዋል።

ምርት ገበያው ከሐምሌ 2011 እስከ ጥቅምት 2012 ያገበያየው የሰሊጥ ምርት መጠን ከ24 ሺሕ ቶን በላይ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቅባት እህሎች ውስጥ የሚመደበው የሰሊጥ ምርት፣ ከፍተኛ አምራችና አቅራቢ አገራት ሕንድና ቻይና ሲሆኑ እንደ በርማ፣ ሱዳን፣ ሜክሲኮ፣ ናይጄሪያ፣ ቬኒዝዌላ፣ ቱርክ፣ ኡጋንዳና ኢትዮጵያ ሌሎች ተጠቃሽ አቅራቢ አገራት ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here