ጥላቻ ላይ በቻልነው ሁሉ እንረባረብ!

0
418

የጥላቻ ንግግር ከቴክኖሎጂ ጋር አዲስ የመጣ ችግር ሳይሆን በሰው ልጆች ማኅበራዊ ግንኙነት ውስጥ የቆየ ችግር ነው። በሰው ልጆች መካከል ያሉ ግንኙነቶች እንደ ዘንድሮው የጊዜና የቦታን ጫና በቀላሉ መጣስ በማይችሉበት ዘመን እንኳን የጥላቻ ንግግሮች በኹለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የተካሔደውን የአይሁዶች ጭፍጨፋ (ሆሎኮስት) በማስነሳትም ሆነ በማፋፋም ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።

የመረጃ እና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስፋፋት ከታየበት ካለፈው ምዕተ ዓመት መጨረሻ አንስቶ ደግሞ የሰው ልጆች ከአንዱ የዓለም ክፍል ሆነው ሌላ የዓለም ክፍል ያለን ሰው በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት እድል ተፈጥሯል።

እነዚህ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመሩ ዓለም ዐቀፋዊ ግንኙነቶች ቀና የሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ትስስሮችን ለማጠንከር የጠቀሙትን ያህል በማህበረሰቦችና በቡድኖች መካከል የኖሩ ችግሮችንም የማስነሳት እድልን ጨምረዋል። የተባበሩት መንግሥታት የጥላቻ ንግግርን ለመታገል ከስድስት ወራት በፊት ባወጣው ስትራቴጂ እና የተግባር እቅድ ላይ “በዓለም ዙሪያ የሚረብሽ መጠን ያለውና ከፍ እያለ የሔደ የመጤ ጠልነት፣ ዘረኝነት እና ያለመቻቻል ወጀብ እያየን ነው” ብሎ ነበር።

በዚሁ ሰነድ ላይ ድርጅቱ ይህ የተናጠል ክስተት ወይም የጥቂት ሰዎች ከፍተኛ ድምፅ ሳይሆን ጥላቻ በዴሞክራሲያዊም ሆነ አምባገነን ስርዓቶች ውስጥ መደበኛ እየሆነ እንደመጣ ይገልፃል። በኢትዮጵያም የጥላቻ ንግግር ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ በሚጠቁም ሁኔታ የመገናኛ ብዙኀን፣ የመንግሥት ተቋማትንና የኅብረተሰቡን ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሆኗል።

አዲስ ማለዳ ለማህበራዊ ድረ-ገጿ ተከታዮች “በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች ዘንድ የጥላቻ ንግግር ሕጋዊ ክልከላ ሊደረግበት የሚገባ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለው ያስባሉ? በሚል ላቀረበችው ጥያቄ ከ1812 መልስ ሰጪዎች መካከል 92 በመቶዎቹ ‹‹አዎን፣ በሕግ መከልከል አለበት›› የሚል መልስ ሰጥተው ነበር። የመላሾቹን አስተያየት የአገሪቱ ሕግ አውጪዎችም ሳይጋሩት እንዳልቀሩ። በዚህ ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የተደረገው ውይይት ይህን ያሳያል።

የሕዝብ ተወካዮቹ ለፀረ-የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ረቂቅ አዋጁ ያላቸውን ድጋፍ በማያጠያይቅ መንገድ ያሳዩት የሕጉ ውስንነት እንዲሰፋ እና የቅጣቱም መጠን እንዲጨምር በመጠየቅ ነበር። ረቂቅ አዋጁም ዝርዝር ውይይት እንዲደረግበት ለሕግ፣ ፍትኅ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
በብልጽግና ፓርቲ እየተተካ ያለው ኢሕአዴግ ራሱን ሲገመግም በብሔሮች መካከል ያለው አንድነት ላይ ተገቢውን ያህል እንዳልሠራ በተደጋጋሚ ጠቁሟል።

በብሔሮች መካከል ‹‹ይህ ብሔር እንዲህ ይላችኋል!›› በሚል የሥልጣን ዘመንን ለማርዘም የመንግሥት ሥልጣንን በያዘ ቡድን የተደረገውን ፕሮፖጋንዳ ብቻ እንኳን ብናይ፣ ዛሬ በትውልድ አመለካካት ላይ ያመጣው ወጤት አስደንጋጭ ነው። በብዙ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሌሎች ዜጎች ለብሔር ፖለቲካው ተጠያቂ የሚደረገው ህውሐት ከገዢ ጥምር ፓርቲ አባልነት ከነአካቴው ሊወጣ በራፍ ላይ ባለበት በአሁን ወቅት እንኳን፣ የዘር ፖለቲካ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና አለው።

ቀድሞ የተዘሩ የጥላቻ ዘሮች ዘንድሮ የዜጎችን ብሎም የአገርን ህልውና እየተፈታተኑ ይገኛሉ። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች በአንድ አካባቢ ውስጥ አናሳ ቁጥር ያላቸው የጎሳ አባላት ማስፈራሪያ ይገጥማቸዋል፣ ከአካባቢው ለቅቀው እንዲሔዱ ይነገራቸዋል፤ እንዲሁም ቀጥተኛ ጥቃቶችም ይፈፀምባቸዋል። ዛሬ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች የጎሳና ሃይማኖት ጥላቻ ከስሜትነት አልፎ በተግባር የሰውን ልጅ ውድ ሕይወት የሚቀጥፍ መሆኑ የሚታይባቸው ቦታዎች ሆነዋል። የፖለቲከኞች የጥላቻና ሐሰተኛ ንግግሮች ‹‹የእኔ ነው›› ብለው የሚያስቡትን የኅብረተሰብ ክፍል ቁጭት ከመቀስቀስ አልፈው የአገሪቷን መረጋጋት በእጅጉ እየተፈታተኑት ነው።

በወጭ አገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያዊያን የራሳቸው የሚሉት ቡድን ሌላው ላይ ጥቃት እንዲያደርስ መወትወታቸው የተለመደ ተግባር ከሆነ ቆየ። ማኅበራዊ ሚዲያዎች በገሀዱ ዓለም የሚከሰቱ እርስ በእርስ ግጭቶች ቀደም ብለው ልምምድ የሚደረግባቸው ቦታዎች ሆነዋል።

የጉዳዩ አሳሳቢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲጨምር እንጂ ጋብ ሲል አልታየም። በመሆኑም ሁሉም የማኅብረሰብ ክፍሎችም ሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ችግሩን ለመቅረፍ ተባብረው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ከላይ የተጠቀሰው የተባበሩት መንግሥታት ሰነድ እንደሚለው ዝምታ ያለመቻቻልንና ስድብን ማበረታታት ይሆናል። በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት ከሚጠቅሙት መንገዶች መካከል አንዱ የሆነውን የሕግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ሒደት ለመጨረስ መቃረባችን ይበል የሚያሰኝ ነው።

ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣው የተለያዩ ዓይነት መፍትሔዎችን አቀናጅቶ በመጠቀም ስለሚሆን፣ በዚህ ረገድ የሕግ ማዕቀፉ መኖር ችግሩን ለመዋጋት ትልቅ መሣሪያ ነው።

የጥላቻ ንግግርን በሕግ መከልከል የመናገር መብትን እንደሚጥስ እና ሕጎቹም በተደጋጋሚ ሁኔታውን ሲቀይሩ እንዳልታየ አንስተው የሚሞግቱ መኖራቸው ይታወቃል። ነገር ግን የችግሩን ከባድነት ተገንዝቦ በአዋጅ የሚያስቀጣ ማድረጉ ራሱ ጥቂቶችንም ቢሆን ጠንቀቅ እንዲሉ ሊያደርግ ይችላል። ‹‹የለከት ያለህ!›› እያለ ለሚጮኸውና የአገራችንን ህልውና እየፈተነ ለሚገኘው የጥላቻ ንግግር ወቅታዊ ሁኔታ የሕጉ መኖር ጠቃሚ መሆኑን አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች።

የመናገር መብቶች በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ገደብ የሚጣልባቸው መሆኑ ይታወቃል። የጥላቻ ንግግሮች አንዱ ለሌላው ጥሩ ስሜት እንዳይኖረው ከማድረግ አልፈው የሕይወትን ማለፍ፣ የንብረት ውድመት እና የአገርን እጣ ፋንታ አደጋ ውስጥ የሚከቱ እየሆኑ ስለሆነ፤ በዚህ ደረጃ ሊፈረጁ የሚችሉ ንግግሮች ገደብ ሊጣልባቸው ይገባል። ለአፈራረጁም ግልጽ የሆኑ መስፈርቶች አስቀምጦ በአፈጻጸማቸው ላይ የፖለቲካ መሣሪያ እንዳይሆኑ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

የፀጥታና የመረጋጋት ችግሮችን ለመቅረፍ በቂ እና ጠንከር ያሉ እርምጃዎችን አይወስድም በመባል ተደጋጋሚ ትችት የሚደርስበትን ይህን መንግሥት ግምት ውስጥ ከተን ሊያሳስበን የሚችለው ችግር የአዋጁ አፈፃፀም ሁኔታ ነው። አዋጁ ወጥቶ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ የማይሆን ከሆነ አጥፊዎችን የልብ ልብ የሚሰጥ የጊዜ ብክነት ሆኖ ይቀራል። በመሆኑም ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተገቢ ነው።

በተለይ ችግሩ ከቴክኖሎጂ፣ ከድብቅ ማንነት እና ከማጭበርበር ጋር የተያያዘ በመሆኑ አስፈጻሚ አካላት ይህንን ውስብስብ ጉዳይ ለመፍታትና ተጠያቂዎችን ሕግ ፊት ለማቅረብ የሚያስፈልጉ ነገሮች ሁሉ እንዲሟላላቸው ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። እየታየ ያለው ማንም በድርጊቱ እና ማድረግ እየነበረበት ባላደረገው ነገር በኃላፊነት የማይጠየቅበትን አካሔድ ለመዋጋት ይህ አዋጅ ሁነኛ መሣሪያ መሆን ስለሚችል፣ አተገባበሩ ላይ ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ አጽንኦት ትሰጣለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here