ከመመሪያ በታች ያሉ ሕጎች እንዳይኖሩ የሚከለክል አዋጅ ተረቀቀ

0
753

የአስተዳደር መመሪያዎችና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት በመሔድ የሚከሰሱበትን ሥነስርዓት ይደነግጋል

የፌዴራል የአስተዳደር ተቋማት ማኑዋል፤ ጋይድላይን፤ ሰርኩላር እና ደብዳቤን እንዳይጠቀሙ የሚያደርገው አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲጸድቅ ቀረበ።
መመሪያ ማለት ሕግ አውጪው አካል በሚሰጠው የውክልና ሥልጣን መሰረት በአስተዳደር ተቋም የሚወጣና በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትል የሕግ ሰነድ ሲሆን፣ በሥራ ያለ መመሪያን የሚያሻሽል ወይም የሚሽር የሕግ ሰነድንም እንደሚጨምር ረቂቁ ያስረዳል።

የአስተዳደር ተቋም መመሪያ የሚያወጣው በዚህ አዋጅ በተደነገገው ሥነ-ሥርዓት መሠረት ብቻ ነው የሚለው ሕጉ፣ ማንኛውም ተቋም መመሪያ አላወጣሁም በሚል ምክንያት በሕግ ሊሰጥ የተጣለበትን አገልግሎት አለመስጠት እንደማይችልም ሕጉ ደንግጓል።

ማንኛውም በፌዴራል የአስተዳደር ተቋማት ስር የሚወጣ መተዳደሪያ፣ ውይይት ተካሒዶበት እና የመመሪያ ሥነ ስርዓትን ተከትሎ እስካልወጣ ድረስ፣ ሕጋዊ ውጤት እንዳይኖረው የሚያደርገው ይህ ረቂቅ አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤቱ ለቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

አዋጁ መንግሥታዊ አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና ማንኛውም የመንግሥት አካል ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚደረግ ያስቀምጣል። የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትሉትን ጣልቃ ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ለማረጋገጥ መዘጋጀቱም ነው የተገለፀው።

የአስተዳደር ተቋም የሚለው ቃል በፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካል ስር የተደራጁ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን እና ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ የሆኑትን የከተማ አስተዳደሮች አስፈጻሚ አካላትን ነው።

የአስተዳደር ሥነ ስርዓት ሕግ ዋነኛ ከሚባሉት ዓላማዎች አንዱ መንግሥት ከመደበኛው የሕግ አስከባሪነት ሥልጣኑ በተጨማሪ ገበያ እና ማኅበራዊ ሕይወትን የመቆጣጠር ሥልጣኖችንም ያካተተ በመሆኑኅ ለዚህ የመቆጣጠር ሥልጣን ገደብ ለማበጀት የታለመ ነው።

ረቂቅ አዋጁ የክልል አስተዳደር ተቋሞችን እንዲሸፍን ያልተደረገው አዋጁን ክልሎች በራሳቸው እንደ መነሻ በመውሰድ ሊተገብሩት እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ መሆኑም ተገልጿል። የተፈጻሚነት ወሰኑን በፌዴራል አስተዳደር ተቋሞችና በአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች የተወሰነ አድርጎታል።

በሕገ መንግሥቱ የሥልጣን ክፍፍል መሰረት የፌዴራሉ ሕግ አውጪ አካል ለፌዴራል አስተዳደር ተቋማት የሚያገለግል፤ የክልል ሕግ አውጪ አካላት ደግሞ ለየክልላቸው አስተዳደር ተቋሞች የሚያገለግል ሕግ ማውጣት እንደሚችሉም ያስቀምጣል።

የአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ መርሆችን ሥነ ስርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰው የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ስርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትህን ማስፈን አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የወጣው አዋጅ መሆኑን ተገልጿል።

ከአስተዳደር ሥነ ስርዓት አዋጅ ተፈጻሚነት በፊት የአስተዳደር ተቋማት ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ነባር መመሪያዎች በ90 ቀናት ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተልከው መመዝገብ እንደሚኖባቸው ያስቀምጣል።

በአስተዳደር ተቋሙ ድረ ገጽ ላይ ያልተጫነ መመሪያ ተፈጻሚነት የማይኖረው ሲሆን፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም መመሪያዎቹን ከመዘገበ በኋላ በድረ ገጹ ላይ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 56 ኅዳር 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here