ዓለማየሁ ገዳ(ዶ/ር) ባለፉት ሁለት መጣጥፋቸው የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ “መንግሥት እና ሕዝብ አስተዳደር” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ተመሥርተው፣ የገብረሕይወት ምጣኔ ሀብታዊ ኀቲት ግንባር ቀደም መሆኑን እንዲሁም የጀመርናዊው ሔንሪ ቻርለስ ኬሪ ትንታኔ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው በተጨማሪም ገብረሕይወት ውስጣዊ የምጣኔ ሀብት ተግዳሮቶች አድርገው ያሰፈሯቸውን አትተዋል። በዚህ መጣጥፍ ቀጣዩን ያስነብቡናል።
የገንዘብና የቀረጥነክ ፖሊሲ ሁኔታ
በገብረሕይወት ምስለ ኢኮኖሚ (‹ሞዴል›) ቀረጥ ለመዋዕለ ንዋይ የሚያስፈልግ ገቢ ማሰባሰቢያ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውን በተፈለገበት አቅጣጫ ለመምራት የሚያገለግል የፖሊስ መሣሪያም ጭምር ነው። ለዚህም ይመስላል የተለያዩ የቀረጥ ዓይነቶች ላይ (ለምሳሌ የአገር ውስጥ ዕቃ ላይ፣ የወጪ ዕቃ ላይ፣ የቅንጦት ዕቃ ላይ፣ የፍጆታ ዕቃ ላይ ወዘተ.) ትንተናቸው ያተኮረው።
በገብረሕይወት የቀረጥ ቀመር ምርት ሲያድግ የአገር ውስጥ የቀረጥ ገቢ እንደሚያድግ የሚያሳይ ሲሆን በአንፃሩ የአገር ውስጥ ቀረጥ ምጣኔ ሲያድግ ምርት ሊቀንስ እንደሚችል ተቀምጧል፤ ይህ ሁለተኛው ሁኔታ ግን የገበሬውን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እንደሚያባብስ ገብረሕይወት አትተዋል። የኢንቨስትመንት መጠናከር ደግሞ ምርታማነትን በመጨመር የመንግሥት ገቢን ያዳብራል። በመጨረሻ በወጭ ንግድ ላይ ሊኖር የሚችለውን የቀረጥ ገቢ ሁኔታ አሁንም ካልስኪን በመቅደም የገብረሕይወት ሞዴል ያሳያል። ይህ ቀመር ከውጪ ንግድ የሚገኘው ቀረጥ በቅንጦትና በኢንቨስትመንት እቃዎች ላይ ሊጣል እንደሚችል ቢያሳይም በቅንጦት ዕቃ ላይ ቢሆን እንደሚመረጥ ገብረሕይወት አሳስበዋል። ኢንቨስትመንትን በተመለከተ እንዲያውም ይህን ቀረጥ ከዜሮ በታች በማድረግ (ድጎማ በመስጠት) ኢንቨስትመትን ማበረታታት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ከዚህ የቀረጥነክ ፖሊስ በተጨማሪ ገብረሕይወት የገንዘብነክ ፖሊሲንም ትንትና ሰጥተውበታል። በዚህ ትንተናቸው ማንኛውም ልማት፣ ባንክና ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ጨምሮ፣ በዕውቀት ላይ ካልተመሠረተ ጉዳቱ እንደሚያይል በተደጋጋሚ ማስገንዘቡን ቀጥለውበታል። ታዳጊ አገሮች የሠለጠነ የሰው ኃይል ከሌላቸው በባንኮች የተሰበሰበውን ገንዘብ ተጠቃሚ አይሆንም። በአንፃሩ የሠለጠነ የሰው ኃይል ያላቸው ያደጉ አገሮች የዚህ ባንክ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህንንም ግንዛቤ በሚከተለው ሁኔታ ምሳሌ በመስጠት አጠናክረውታል።
“በኢትዮጵያ የቆመው የእንግሊዝ ባንክ ከታኅሣሥ 22 ቀን 1904 እስከ ታኅሣሥ 22 ቀን 1905 ድረስ ያበደረውን ገንዘብ ብናስበው 1,220,850 ብር ይሆናል። ከዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተበደረው 50,000 ብር በላይ አይሆንም ይሆናል። የቀረው ግን 1,170,850 ብር የውጪ አገር ሰዎች ተበድረው ሠሩበት።” (ገፅ 126)
ገብረሕይወት ስለ ገንዘብ ፖሊሲዎች ሲተነትኑ እንደ አንድ ጥሩ የፖሊሲ መሣሪያ አድርገው የሚገልጹት ባንኮች የሚያስከፍሉትን የወለድ መጠን ነው። ለገብረሕይወት ልማት/ዕድገት የባንክና የመገናኛ አውታሮችን ስለሚያስፋፋ፣ መበደር ከባድ አይሆንም፤ (ምክንያቱም ንግድ ይስፋፋል፣ ሰዎች ገንዘባቸውን ከማስቀመጥ ይሠሩበታል በመሆኑም የገንዘብ መጠን ኢኮኖሚው ውስጥ ይጨምራል)። በዚህም ምክንያት ባንኮች የሚያስከፍሉት የወለድ መጠን ዝቅ ይላል። ስለሆነም ለገብረሕይወት የወለድ መጠንና የአገር ዕድገት ተቃራኒ የጉዞ መሥመር ይከተለሉ። ይህም ማለት ያደጉ አገሮች የባንኮች የወለድ መጠን ዝቅ ያለ ሲሆን ያላደገ አገር ባንኮች የወለደ መጠን ግን ከፍ ያለ ነው።
ሌላው ገብረሕይወት ያነሱት ገንዘብ ነክ ጉዳይ የባንኮችን ገንዘብ የመፍጠር አቅምና መንግሥት ግሽበትን ተጠቅሞ ሕዝቡን በተዘዋዋሪ ቀረጥ ማስከፈል እንደሚችል መተንተናቸው ነው። ይህንንም ሁኔታ በጊዜው የነበረውን የአቢሲንያ ባንክ አሐዝ በመጠቀም አብራርተውታል። ዕውቅት ለሌለው ሕዝብ ባንኮች የሚፈጥሩት ገንዘብ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ከዚህ ጋር አያይዘው ከማተታቸውም በላይ፣ መንግሥትም ግሽበትን ተጠቅሞ ገንዘብ መሰብሰቡ ምንም እንኳን ለመንግሥት ቀላል ግብር የመሰብሰቢያ ዘዴ ቢሆንም ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለው አሠራር ስለሆነ ገብረሕይወት ተቃውመውታል (እንዲያውም የውጪ አገር ሰዎች የኢትዮጵያን መንግሥት እንደዚህ መምከር ጀምረዋል ማለትን ባይሰሙ ይህንን ሐሳብ መጻፍ ቀፏቸው ነበር)። ይህ ዓይነቱ የመንግሥት አካሔድ የሠራተኛውን ሕዝብ የመግዛት አቅም እንደሚያመንምንና በዚህም ሠራተኛው እንደሚጎዳ ገልጸውታል።
በመጨረሻም የገብረሕይወት የገንዘብ ነክ ትንታኔ የገንዘብ ፍላጎት ቀመር ላይ ያተኮረ ነበር። በጊዜው በአገሪቱ ኢኮኖሚው ውስጥ የነበረውን የሽርፍራፊ ገንዘቦች እጥረት በመጥቀስ ይህንን ክፍተት ለመዝጋት የገንዘብ አቅርቦቱ ከአውሮፓ በመምጣት ከኢትዮጵያ ትርፍ አጋብሶ ሊሔድ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ይህም የሆነው በጊዜው የነበረው ገንዘብ የብር ወይም ወርቅ በመሆኑ ነው። ይህንን አደጋም ለመቀነስ የሚከተሉትን የፖሊስ አቅጣዎች መንግሥት እንዲከተል ጠቁመዋል። እነዚህም፦
አንደኛ፣ መንግሥት የራሱን ገንዘብ ከበቂ ሽርፍራፊ ጋር እንዲያትም፤ ሁለተኛ፣ የገንዘብ ፍላጎትን በማጥናት ተመጣጣኝ አቅርቦት እንዲያደርግ። ይህንንም ሥራ መንግሥት ብቻ እንዲሠራው፤ ሦስተኛ፣ በተለያዩ ከተሞች መሐል ያለውን የዋጋ ልዩነት ለማጥበብና በትንሽ ገንዘብ ብዙ ንግድ ለማካሔድ እንዲችል (የአንዷን ብር አማካይ ዝውውር እና የምታስተናግደውን የንግድ መጠን በመጨመር) መንግሥት መሠረተ ልማቶችን እንዲያስፋፋ፤ እና አራተኛ፣ የገንዘቡን ሕጋዊ ተቀባይነት በመደንገግ የግድ ብር ወይም ወርቅ መሆኑን በሐደት መቀነስ – የሚሉ ነበሩ።
እነዚህ የገብረሕይወት የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ልዩ የሚያደርጋቸው የገንዘብነክ ፖሊሲዎች ሰፋ ባለልማታዊ ቅኝት ሥር የተወጠኑ መሆናቸው ነው።ለዚህም በጣም ግልጽ ምሳሌ በሦስተኝነትየተሰጠው የፓሊሲ አቅጣጫ ነው።
ውጫዊ የልማት መሰናክሎች
በገብረሕይወት ምስለ ኢኮኖሚ ‘ውጫዊ የልማት መሰናክሎች’ ያልኳቸው ኢትዮጵያ በውጪ ንግድ በኩል ያላትን ግንኙነት መሠረት ያደረገውን ትንታኔያቸውን ነው። ለነገሩ አስተሳሰቡ ባጠቃላይ ላደገና ላላደገ አገር ንግድ ልውውጥ መገለጫ ሊሆን ይችላል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የገብረሕይወት መሠረታዊ ሐሳብ የሚያጠነጥነው በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ ባሉ ሁለት አገሮች መሐከል ነው፤ ለምሳሌ አውሮፓና ኢትዮጵያ ሲነግዱ ያላደገው አገር እንደሚጎዳ ማስረዳቱ ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ መሠረታዊው ምክንያት ያላደገው አገር ምርት ብዙ ዕውቀት የሌለበት ጥሬ ዕቃ እና የትራንስፖርት ወጪው ትልቅ ሲሆን፥ ያደገው አገር ዕቃ ደግሞ የተቃራኒውን ይዘት ይይዛል። ይህ ደግሞ ላልተመጣጠነ የንግድ ልውውጥ ብሎም ላላደገው አገር ድህነት መዳረግ ምክንያት ይሆናል። ይሀንንም ሲያብራሩ፦
“…እንግዲህ ለአንዱ ኮሮጆ አቡጀዲ እስከ ሦስት በሬ ይሰጥበታል። ስለምን በሬው በሽታ እንዳይገለው፣ አውሬ እንደይበላው ከመጠበቅና ወደ ገበያ ከመውሰድ በቀር ሌላ የሰው ድካምና ዕውቀት አላለፈበትም። ያቡጀዲው ጥጥ ግን አቡጀዲ እስከሚሆን ድረስ በብዙ ሰዎች እጅና በብዙ መኪናዎች ውስጥ ገብቶ ተደክሞበታል። በፈረንጅ አገር በሬውም ቢሆን ብዙ ዋጋ ያወጣል። ስለምን ሕዝቡ በዝቶ አገሩ ጠባብ ስለሆነ በሬው በልቶ የሚያድገው ሳር ተዘርቶ፣ ታጭዶ፣ ተከምሮ ነው። ቤቱም የሚሠራ በስንት ድካም ነው።…ስለዚህም ከኤሮጳ አገር ለሚመጣልን ነገር ሁሉ ዋጋ የምንሰጠው ስለ ሥራው ነው እንጂ ስለ ብዛቱ አይደለም። ያቡጀዲ ጥጥ እንጂ ሥራው ወደ አገራችን መጥቶ ፍግ እንዳይሆን የታወቀ ነው። …እንግዲህ ዕወቀት አንሶት የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ በገዛ እጁ ለመሥራት የማይችል ሕዝብ የሚያገኘው ጉዳት ምን እንደሆነ ከተረዳነው ዘንድ፣ ይህንን ጉዳትና ባርነት አጥፍቶ ወደ ሀብትና ወደ አርነት የሚወስደውን መንገድ አንመልከት።” (ገፅ 71)
ያላደገው አገር ጥቅም ካደገው አገር ጥቅም ጋር ሲነፃፀር በጣም የማሽቆልቆል ዝንባሌ ይኖረዋል። የልማት ኢኮኖሚ ተንታኞች ይህን ሐሳብ (ዝንባሌ) ‘የፕሬሸብሽ-ሲንገር’ አስተሳሰብ ወይም ‹ሃይፓተስስ› ይሉታል። እኔ ግን ‘የነጋድራስ ገብረሕይወት አስተሳሰብ’ወይም ‘የገብረሕይወትና የፕሬሸብሽ-ሲንገር’ አስተሳሰብ ብዬዋለሁ፤ ምክንያቱም እሳቸው 50 ዓመት ከፕሬብሽና ከሲንገር በፊት ቀድመው ስላወቁትና ስለጻፉት ነው።
ገብረሕይወት በዚህ ቀመር በኢትዮጵያና በአውሮፓ መሐል ያለው የገቢና ወጪ ንግድ ሚዛን ያልተመጣጠነ እንደሆነ አሐዝ ጠቅሰው ያሳያሉ። በገብረሕይወት ምስለ ምጣኔ ሀብት ኢትዮጵያ ጥሬ ዕቃ፣ አውሮፓ ግን የተፈበረከ ዕቃ ስለሚልኩ፣ ኢትዮጵያ ትጎዳለች። ይህም የሚሆነው ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛው የተፈበረከ ዕቃ የትራንሰፖርት ወጪው ትንሽ ሲሆን ጥሬ ዕቃ ግን የትራንስፖርት ወጪው ከፍ ይላል። በሁለተኛ ደረጃ የተፈበረከ ዕቃ ብዙ ዕወቀት ስለፈሰሰበት ውድ ሲሆን ጥሬ ዕቃ ግን ብዙ ዕውቀት ስላልፈሰሰበት በአንፃራዊነት ሲታይ ርካሽ ይሆናል። ጥሬ ዕቃ ከምድር ስለሚገኝ፤ የኛም ሥራና ንግድ ምድርን ሁሌም ‹ጥሬ ዕቃ አምጪ›ባይ ብቻ ሲሆን በጊዜ ብዛትም ምድሪቱ ለግማብን ጥሬ ዕቃውን ብቻ ሳይሆን የምንበላውንም ማምረት ስለማንችል የእኛም የልጅ ልጆቻችንም ዕጣ ወደ አደጉት አገር መሰደድ እንደሚሆን አትተውት ነበር። ይህ ንድፈ ሐባዊ አካሔድ በመስኩ ቀደምት ከሚባሉት ከነሲንገርና ፕሬብሽ ሐሳብ ቀዳሚ ብቻ ሳይሆን ከነሱ የተለየ የአካባቢ ጥበቃ እና የስደትን (ፈረንጆቹ ‹environmental and Migration issues› የሚሉትን) በማያያዝ ጠለቅ ያለ ጎንም አለው።
(ይቀጥላል)
ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በአ.አ.ዩ. የምጣኔ ሀብት ፕሮፌሰር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው ag112526@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011