የሴቶች ጥቃት የዕለት ልማድ መሆኑ ቢበቃስ? (ክፍል አንድ)

0
1322

የሴቶች ጥቃት ምንድን ነው? ጥቃቱን የሚያደርሱትስ እነማን ናቸው – የሩቅ ሰዎች ወይስ የቅርብ ወዳጆች? እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት እና መልስ በመስጠት የሴቶች ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ መሆኑን በዚህ መጣጥፋቸው የሚያስነብቡን ቤተልሔም ነጋሽ ለዚህ መንስዔው የሕግ አፈፃፀም ክፍተት ነው ይላሉ።

 

 

የጋንዲ ሆስፒታል ነርሶች አንድ ቀን መደበኛ ሥራቸውን ለማከናወን እየተሰናዱ ሳለ፣ አንድ ጎልማሳ አንዲት ታዳጊ ይዞ የሕክምና አገልግሎት ፍለጋ እንደመጡ ይነግራቸዋል። የሚፈልጉት አገልግሎት ፅንስ ማቋረጥ ነበር። እንዳጋጣሚ የፅንሱ የዕድገት ደረጃ ለማቋረጥ የሚቻልበትን ወቅት አልፏል። ፅንሱን ለማቋረጥ ከወሰኑ ለምን ቀኑ እስኪገፋ ቆዩ የሚለው ጥያቄ ለነርሶቹ ግራ ቢያጋባቸው፣ በዚያ ላይ የልጅቷን ዕድሜ ለጋነት፣ ጭንቀትና አጠቃላይ ሁኔታዋን ስለተጠራጠሩ፥ ለብቻዋ ወደ ውስጥ አስገብተው ለማነጋገር ወሰኑ። በብዙ ማግባባት ተገዳ መደፈሯን ትነግራቸዋለች። ታዳጊዋ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ብሩክታዊት እያልን እንጥራት) ወደ ሆስፒታሉ በሔደችበት ወቅት የ16 ዓመት ወጣት ነበረች።
ብሩክታዊት ከሦስት ዓመት በፊት ገበሬ ቤተሰቦችዋን ጥላ፣ ትማርበት ከነበረው የጉራጌ ዞን የገጠር ከተማ ወደ አዲስ አበባ ስትሰደድ ምኞቷ በድኅነት የሚሰቃዩ ወላጆቿን ለማገዝ፣ ትምህርቷን አጠናቃ አለኝታቸው ለመሆን ነበር። ወዲያውም ቀድማት አዲስ አበባ ገብታ ትዳር መሥርታ የምትኖር፣ ታላቅ እህቷን ተቀላቅላ ወደፊቷን ያማረ ለማድረግ ጭምር ዓልማ ነበር። እህቷ በበኩሏ የሷ አለመማር ያመጣባትን ጉዳት ስላየች ታናሽዋ እንድትማር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል ከጠዋት እስከማታ ስትለፋ አመሻሽታ ትገባለች።
ታናሽየው ከትምህርት መልስ እህቷ በሌለችበት የእህቷን የጓዳ ክፍተት ልትሞላ ትጥራለች። ከዕለታት ባንዱ ቀን በተለመደ ሥራዋ ላይ ሳለች የእህቷ ባል ድንገት ከኋላዋ ደርሶ እንዳትጮህ አፏን አፍኖ ይደፍራታል። ለእህቷ ብትናገር እንደሚገድላት ይዝትና ያስፈራራታል። ድርጊቱ ባንድ ቀን አልቆመም። ዝም እንዳለች ሰውነቷ ለውጥ ማምጣቱን ያየው የእህት ባል፣ ጋንዲ ወስዶ ፅንሱን እንድታቋርጥ ለማድረግ ሲሞክር በጋንዲ ሆስፒታል ነርሶች ተጠራጣሪነት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል።
ብሩክታዊት መደፈሯና ከሕይወት ግቧ መሰናከሏ ሳያንስ፣ ባላሰበችው ሁኔታ የደፋሪዋን፣ የእህቷን ባል ልጅ የማሳደግ ዕጣ ወድቆባታል። ተምራ ጥሩ ቦታ የመድረስ ሕልሟ ባጭሩ ተቀጭቷል። ይባስ ብሎ ለደረሰባት ግፍ ማኅበረሰቡ ከጋብቻ ውጭ የወለደች ብሎ ራሷን ይቀጣት ይሆናል።
የብሩክታዊት ታሪክ የብዙ ታዳጊ ሴቶች ታሪክ ነው። ከወንጀሉ ባሕርይ፣ በማኅበረሰባችን አስገድዶ መድፈር ነውር ከመሆኑና ምናልባትም ወደ ሕግ መሔድ ውጤት ለማግኘት ከሚፈጀው ጊዜ አንፃር ታሪካቸው ተሸፋፍኖ፣ ከነጉዳታቸው በየቤታቸው የቀሩ ብዙ እንደሚሆኑ ለመገመት ቀላል ነው።
የብሩክታዊትን ታሪክ ያገኘነው የተለያዩ ጥቃቶች ለደረሰባቸው ሴቶች መጠለያና መልሰው ራሳቸውን እንዲችሉ የሥልጠና ድጋፍ ከሚያደርገው የሴቶች ማረፊያና ልማት ማኅበር ነው። ለመሆኑ የጥቃት አድራሾች እነማን ናቸው?
የጥቃት ዓይነቶች እና አድራሾች
የጥቃት ዓይነቶች ብዙ ናቸው። ከላይ ያነሳነው ከባድና የከፋ የሚባለው ዓይነት የወሲብ ጥቃትና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ሥነ ልቡናዊ ጉዳቶችን የሚያስከትሉ ስድብ፣ ማንቋሸሽ፣ ማስፈራራት፣ ገንዘብ መከልከል፣ ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር እንዳይገናኙ መከልከል እስከ አካላዊ ጉዳት ማለትም ግርዛት፣ አስገድዶ ወሲብ መፈፀም፣ ድብደባ (የቤት ውስጥ ጥቃት)፣ አሲድ መድፋት፣ የግድያ ሙከራ እና ግድያ ከእነኝህ ጥቃቶች መካከል ይገኙበታል።
የሚያሳዝነው እንደ ዓለም የጤና ድርጅት ምደባ እነኝህ ጥቃቶች የቅርባችን በሆኑ ሰዎች የሚደርሱ (Intimate partner violence) ናቸው። በአገራችን በቅርብ ጊዜያት የደረሱ የአሲድ ጥቃቶችና ሌሎች ወንጀሎች የሚመሰክሩትም ይህንኑ ነው።
የሕዝብና የጤና ጥናት ከጠየቃቸው ኢትዮጵያዊያን ሴቶች መካከል ለምሳሌ 59 በመቶው አጠገባቸው ባለ በሚያምኑትና በሚወዱት ሰው የወሲብ ጥቃት ገጥሟቸው እንደሚያውቅ ሲጠቅስ 49 በመቶው አካላዊ ጥቃት እንደገጠማቸው 29 በመቶው ደግሞ ጥናቱ ከተደረገበት ወቅት በፊት በነበረው አንድ ዓመት ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ሪፖርት ማድረጋቸውን ይጠቅሳል።
በማኅበረሰባችን አተያይ ግን ጥቃት አድራሾች ወይም ደፋሪዎች የማይታወቁ ሰዎች፣ አውሬዎች፣ ከስንት አንድ ዓይነት የሚባሉ ሆነው ሲቀረፁ ይታያል። ሰዎች በአብዛኛው ስለአስገድዶ መድፈር ሲያስቡ አንዲት ሴት በጨለማ ስትጓዝ ወይም ጭር ባለ አካባቢ ብቻዋን ስትሔድ አልያም በጣም አጭር ቀሚስ ለብሳ መንገድ ላይ ስትጓዝ፣ ወንዱ ድንገት ስሜቱ ተነሳስቶ የደፈራት አድርጎ ያስቡታል። ይሄ ግን ብዙ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች የሚፈፀሙበት እውነታ አይደለም። ይህ አስተሳሰብ ወንዱን እንደ እንሰሳ የሚያስቆጥር ብቻ ሳይሆን ያደግንበትን ባሕል፣ ሃይማኖትና ሞራል ወሲብ በአገራችን የተለጠፈበትን ውስብስብ አተያይ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው።
ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ወሲባዊ ጥቃት በራሱ መፈፀሙ ብቻ ሳይሆን የሚያስከትላቸው ሌሎች ጎጂ ውጤቶችም አሉት። ከሚጠቀሱትም መካከል አካላዊ ጉዳት፣ ሥነ ልቦናዊ መንቋሸሽ፣ በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች፣ ተስፋ መቁረጥና መረበሽ፣ ያሳለፉትን ስቃይ በማስታወስ የሚፈጠሩ ሌሎች ጉዳቶች የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል።
ሥነ ልቦናዊ እና ሥነ አዕምሯዊ ሕክምና፣ የምክርና ችግራቸውን በመረዳት ልባዊ ተቆርቋሪነት ርሕራሔ የማሳየት ድጋፍ መስጠት ባልተለመደበት እንደኛ ባለ አገር ተጠቂዎቹ ሕይወታቸውን እንደገና ለማቋቋምና በማኅበራዊ ሙሉነት ለመንቀሳቀስ እና አዕምሯዊና አካላዊ ብቃት ያላቸው ዜጎች ለመሆን በእጅጉ ይቸገራሉ።
አስገድዶ መድፈር የከፋ ወንጀልና ጉዳት መሆኑን ማሳያው አንድ መንገድ በጦርነትና በሕዝቦች መካከል በሚኖር ጠብ አንደኛው በሌላው ላይ የሚፈፅመው ከፍተኛ ንቀትና ክህደት ማሳያ መሆኑንም ታሪክ ያስረዳናል። በቦስኒያ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ተደፍረው የጠላት ወታደሮችን ልጆች እንዲወልዱ ተደርገዋል። በኢራቅ ተነስቶ ተስፋፍቶ ለሶርያ ጦርነት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል አንድ ሚና የተጫወተው አይ ኤስ አይ ኤስ የተሰኘው ፅንፈኛ ሚሊሻ አንድ ግፍና ወንጀል የጠላት ወገን ያለውን አካል ልጆችና ሚስቶች መድፈር፣ በወሲብ ባርያነት መጠቀም በግድ ልጆች እንዲወልዱ ማድረግ ይጠቀሳል።
የሚያሳዝነው ይኸው ድርጊት በአገራችንም መፈፀሙ ነው። ቀደም ብሎ በሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ ቦታዎችና አንዳንድ አካባቢዎች በቅርቡ ደግሞ በጅጅጋ የተከሰተው ቀውስ ወቅት የነበረው አስነዋሪ ሴቶችን በቡድን የመድፈር ልማድ፣ በቡራዩም እንዲሁ የታየው ሕፃናትን የመድፈር ድርጊት ተጠቃሽ ነው።
ጥቃቱ ጨምሯል
በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የኃይል ጥቃቶች ከድብደባ እስከ አስገድዶ መድፈርና አሲድ መድፋት እንዲሁም ግድያ በተደጋጋሚ ከሚዲያ ዘገባዎችና ዜናዎች አይጠፉም። አንዳንዶች ጥቃት አልበዛም፤ የቀጠለው ድሮም በነበረበት መጠን ነው። የበዛ የመሰለን ወደ ብዙኃን መገናኛዎች መምጣትና መሰማት ስለጀመረ እንጂ ሲሉ ይደመጣሉ። እውነቱ ግን ጉዳዩ ያገባናል ብለው በሚሠሩ በተለያዩ አካላት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የጥቃት ዓይነቱ ብዙ ሆኖ፣ በመጠንም እየጨመረ መምጣቱን ነው።
ከላይ የተጠቀሰው በሕዝቦች መካከል ግጭት ሲኖር ሴቶችን የበቀልና የጉዳት ማሳያ አድርጎ፥ በቡድን ሳይቀር ጭካኔ በመላበት ሁኔታ ሴቶችን መድፈር አዲስ ልማድ እየሆነ መምጣቱ፣ ይህንንም ጉዳይ ተፀይፎ ቀጣይ ምርመራ እንዲደረግና በደል አድራሾች ለፍርድ እንዲቀርቡ ተበዳዩችም ፍትህ እንዲያገኙ የሚጠይቅ አካል አለመታየቱ እጅግ አሳሳቢ ነው።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ባላት መረጃ መሠረት ለምሳሌ በሶማሌ ክልል ለተራዘመ ጊዜ በስፋት በሴቶች ላይ ለተፈፀመው ወሲባዊ ጥቃት መረጃም ሆነ ሪፖርት ያቀረበው ብቸኛው አካል የሰብአዊ መብቶች ጉባዔ ነው። የጉባዔው ልዩ መግለጫ ቁጥር 144፣ ከጥር 2009 እስከ ጥር 2010 በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን በሚመለከት መረጃ አሰባስቦ ያወጣው ሪፖርት አስገድዶ መድፈርን እንደ አንድ የወንጀል ዓይነት መዝግቦ የነበረውን ሁኔታ መርምሮ ሪፖርት አድርጓል።
የጥቃቶች መንስዔ
ሴቶች ላይ ለሚደርሰው ጥቃት እንደ መንስዔ በአብዛኛው የሚሰጠው አስተያየት ለጥቃት አድራሾቹ የሚሰጠው ቅጣት ወይንም ፍርድ አነስተኛ መሆኑ እንደሆነ ተደርጎ ነው።
ጥቃቶች በመገናኛ ብዙኃን የሚዘገቡባቸው መንገዶችም አንድ ዓይነትና በአብዛኛው ይህንኑ ቅጣት አነሰ የሚል ምክንያት ማስተጋባት ነው። በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት ግን የማኅበረሰቡ ወግና ልማድ አስተሳሰብ እንዲሁም ለሴቶች የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛና የወረደ መሆኑ በዋነኛነት ለጥቃቶቹ ምክንያት ነው።
በተጨማሪም በዚህ ጽሑፍ ቀጣይ ክፍሎች የተጠቀሱት የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀፆችና ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ አገሪቱ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ሥምምነቶች የሴቶችን መብቶች በሚመለከት በቂና አስተማማኝ የሚባል (ሁሉም የጥቃት ዓይነቶች ለምሳሌ የቤት ውስጥ ድብደባ (Domestic violence) በወንጀለኛ መቅጫ አለመካተታቸውና ሌላም ክፍተት መኖሩ እንዳለ ሆኖ) መልኩ መብቶች የሚያጎናፅፉ ቢሆንም አፈፃፀማቸው ችግር ያለበት ሆኖ ይታያል። ይኸውም በሕግ ከተደነገገው መብት ይልቅ ማኅበረሰቡ ለሴቶች የሰጠው ቦታና መብት የበለጠ ሆኖ የሚታይበት እውነታ በመኖሩ ነው። ለዚህም ነው ቅጣቱ ብቻውን ለውጥ ለማምጣት ያልቻለው።
(ሳምንት ይቀጥላል)

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here