ግድቦች በቂ ዉሃ በመያዛቸዉ ወደ ኤሌክትሪክ ፈረቃ ስርዓት እንደማይገባ ተገለፅ

0
592

በያዝነው ዓመት የኃይል ማመንጫ ግድቦች በቂ ዉሃ በመያዘቸው ወደ ፈረቃ ስርዓት እንደማይገባ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ባለፈዉ ዓመት ተከስቶ በነበረዉ የግድቦች ዉሃ መጠን መቀነስ ምክንያት ወደ ፈረቃ ስርዓት መግባቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በዘንድሮ የዝናብ ወቅት ግድቦች በቂ ዉሃ መያዛቸዉን ተከትሎ የፈረቃ ስርዓት እንደማይኖር ተገልጿል። ቆቃ፣ ፊንጫ፣ መልከዋከና፣ ግልገል ጊቤ እና አመርቲ ነሽ ያሉ ግድቦች ከዚህ በፊት ከነበረዉ የዉሃ መጠን የተሻለ ከፍታ በማሳየታቸዉ እጥረት እንደማይከሰት እና የኤሌክትሪክ ፈረቃ ስርዓት እንደማይኖር የኤሌክትሪክ ኃይል አስታዉቋል።

ግድቦቹ በ2012 ከነበረበት ከፍታ ጨምሯል የተባለ ሲሆን፤ ግልገል ጊቤ 3 ከ830 ሜትር ከፍታ ወደ 882 ሜትር ከፍ ብሏል። መልከዋከና ግድብም ከነበረዉ አማካይ ከፍታ በሰማንያ ሴንቲ ሜትር ከፍ ብሏል። እንዲሁም ፊንጫም በተመሳሳይ በቂ የዉሃ መጠን መያዙ ተገልጿል።

በተጨማሪም ኹለት መቶ ሃምሳ ሜጋ ዋት ኀይል ማመንጨት የሚችል ገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ ለማሟላት ሲባል ግንባታ ተጠናቆ በሙከራና ፍተሻ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ኢትዮጲያ በዓመት አራት ሺሕ ኹለት መቶ ሰባ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ቢኖራትም፣ በየዓመቱ እያመነጨች ያለችዉ ኹለት ሺሕ አምስት መቶ ሜጋ ዋት በመሆኑ በሂደት የሚጠናቀቁ አዳዲስ ግድቦች እና የንፋስ ኃይል ማመንጫዎችን ተጠቅማ ኃይል ለማመንጨት እየተጋች መሆኑን እና ዘንድሮ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዓመታት የተሻለ አጠቃቀም ይኖራታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ መኮንን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በዓመት ከዘጠኝ እስከ አስራ ሦስት በመቶ እያደገ የሚሔድ የኃይል ፍላጎት ሲኖር፣ በዓመት 4ሺሕ200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለ።

ቅጽ 2 ቁጥር 57 ኅዳር 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here