‘ፌሚኒዝም’ ምንድን ነው?

0
1076

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

[ይህ ጽሑፍ በሲቲና ኑሪ የተተረጎመው በአሜሪካ የሴቶች መብት ተሟጋችና ደራሲ ግሎሪያ ዋትኪንስ በብዕር ሥሟ ቤል ሑክስ እ.ኤ.አ. በ2000 “Feminism is for EVERYBODY: Passionate Politics” በሚል ርዕስ ከጻፈችው መጽሐፍ ላይ ነው፤ ጽሑፉ ለዚህ አምድ እንዲመች የተቀነሰ ሲሆን ርዕሱም የተመረጠለት በአዲስ ማለዳ ዝግጅት ክፍል ነው።]

በቀላሉ ስንተረጉመው ‹ፌሚኒዝም› ፆተኝነትን፣ የፆታ ብዝበዛን እና ጭቆናን ለማስቆም የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። ይህም ትርጉም ከዚህ ቀደም ከዐሥር ዓመት በፊት “Feminist Theory: From Margin to Center” በማለት ካሳተምኩት መጽሐፌ ላይ ያቀረብኩት ነው። [ፆተኝነት ‹sexism› የሚለው እና ስርዓተ-ፆታዊ መድልዖን የሚገልጽ ቃል ነው።] ይህንን ትርጉም የወደድኩበት ምክንያት ወንዶችን በጠላትነት ስለማይፈርጅም ነበር። ይሄ ትርጉም ፆተኝነትን በማካተት የችግሩን ሥረ መሠረት ለመንካት ያስችላል። ስለሆነም በወንድም ሆነ በሴት አልያም በሕፃናትም ሆነ በሌሎች ላይ ፆተኛ አስተሳሰብና ተግባር እስከፈፀሙ ድረስ ሁሉም የችግሩ አካላት ናቸው። … በአጭሩ፣ ፌሚንዝምን ለመረዳት አንዲት ሰው ፆተኝነትን መረዳት ይጠበቅባታል።
አብዛኛዋቹ ሰዎች ፆተኝነትን በቅጡ አይረዱትም፤ ቢረዱትም ችግር ነው ብለው አያስቡትም። […] የማኅበረሰባችን ባሕል ሃይማኖት የሚጫነው እንደመሆኑ መጠን፥ አብዛኞቹ የማኅበረሰባችን አባላት ሴቶች በፈጣሪ ወንዶችን በቤት ውስጥ ለማገልገል የተሰጡ ስጦታዋች አድርገው ያስቧቸዋል። ምንም እንኳን ሴቶች እንደ ወንዶች ሁሉ ሥራ ላይ የተሠማሩ ቢሆንም እንዲሁም ምንም እንኳን ብዙ ቤተሰቦች በእማወራ የሚመሩ ቢሆንም፣ የወንድ የበላይነት በቤት ውስጥ ወይም ከቤት ውጭ ፀንቶ ይታያል።
[…] በቀደመው የፌሚኒዝም ዘመን የወንዶች የበላይነት በእጅጉ የሚያስቆጣቸው ሴቶች ዘንድ ወንድ-ጠል የሆኑ ስሜቶች ነበሩ። ነገር ግን ያ ኢፍትሓዊነት ላይ የነበረ ቁጣ ነው የሴቶች ነጻነት እንቅስቃሴን የወለደው። በቀደመው ዘመን ብዙ ፌሚኒስት አራማጆች (ብዝኃኑ ነጮች) በፀረ-መደብና በፀረ-ዘረኝነት እንቅስቃሴዎች ሲሳተፉ ስለአርነት አውርተው የማይጠግቡ ወንድ የትግል አጋሮቻቸው በእንቅስቃሴዎቹ ውስጥ ሴቶችን ሲጨቁኑ ታዝበዋል። […] ዘመናዊው የሴቶች እንቅስቃሴ ሲጎለብት የእንቅስቃሴው አባላት በማኅበረሰባችን ውስጥ ፆተኛ የሆኑ አስተሳሰብ አራማጆች ወንዶች ብቻ እንዳይደሉ እና ሴቶች ራሳቸው የዚሁ አስተሳሰብ ተጠቂ እንደሆኑ ሲገነዘቡ፣ ፀረ-ወንድ የሆኑ ስሜቶች እንቅስቃሴው ላይ ያላቸው አስተዋፅኦ ትንሽ እንደሆነ ተረድተዋል። … ሴቶች አብሮ የኖረውን ፆተኝነት ሳይጋፈጡ ወደ ተሻለ የፌሚኒዝም እንቅስቃሴ መሻገር አልቻሉም። […] በአጠቃላይ ፌሚኒዝም ማለት የፆተኝነት ጭቆናን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው። ትግላችን ከዚሁ እንጀመር!

ሲቲና ኑሪ sisnuri@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 3 ኅዳር 22 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here